የመነሻ ሃሳብ
የእኛ ሰው ልጆች ትክክለኛ ማንነት በልዑል እግዚአብሔር አምሳል የተፈጠርን፣ ገደብ አልባ አቅም እና ችሎታ ያለን ፍጡር ነን:: አእምሮሯችንን ተጠቅመን ስኬትማ ህይወት መኖርን የታደልን ልዩ ፍጡር ነን።
ነገር ግን በልጅነታችን ስለዚህ መሰረታዊ እና ህይወት ለዋጭ ድንቅ እውነታ አልተማርንም፡፡ ይባስም ብሎ አብዛኞቻችን ገና ማገናዘብ በማንችልበት በልጅነት ዕድሜያችን (በዋናነት 0-8 ዓመታት ዕድሜ እንዲሁም ከ8-12 ዓመታት ዕድሜ ውስጥ) በነበርንበት ወቅት በቅርብ ከነበሩት ሰዎች (ወላጅ፣ አሳዳጊ እንዲሁም ሌሎች የቤተሰብ አባላት እና ከመገናና ብዙሃኖች) በአብዛኛው ስለ ህይወት አስቸጋሪነት እና ውጣውረድ፣ ስለ በሽታ፣ ስለ ድህነት፣ ስለ ስደት እና ስለ ሌሎች አሉታዊ ነገሮች እየሰማን እና እያየን እናድጋለን።
ይህም የህይወት አስቸጋሪነት እና ውጣውረድ፣ በሽታ፣ ድህነት፣ ስደት እና ሌሎች አሉታዊ ነገሮች የሰው ልጅ በምድር ላይ ሲኖር የማይቀርለት እና ተቀብሏቸው ሊኖር የሚገቡ የህይወት እውነታዎች እንደሆኑም እየተነገረን እናድጋለን:: በስተመጨረሻም እኒህ እና ከመሳሰሉት በቅርባችን ከነበሩ ሰዎች የተደጋገሙልንን ነገሮች በድብቁ አእምሯችን ልክ ምንም የማይሻሩ እውነታዎች ይሆናሉ፡፡ በህይወታችን በሙሉም ውጤታቸውን እያጨድን እንድንኖር እንገደዳለን፡፡
የማገናዘብ ዕድሜ (ከ12 ዓመት በላይ) ስንደርስ በንቁ አእምሯችን የምናስበው ስኬታማ ህይወትን መኖር ይሆናል:: ነገር ግን በተጨባጭ መሬት ላይ የምንኖረው ህይወት ደግሞ ያኔ በድብቁ አእምሯችን በተቀመጠው እውነታ መሰረት አስቸጋሪነት እና ውጣውረድ፣ በሽታ፣ ድህነት፣ ስደት እና ሌሎች አሉታዊ ነገሮች የበዛበት የውድቀት ህይወት ይሆናል:: በዚህም ምክንያት መሆን፣ ማግኘት እና መስራት ከምንፈልገው ነገር ጋር ተፋትተን የትግል ኑሮ እንኖራለን::
በመሆኑም ከዚች አጭር ጽሁፍ አንድ ትልቅ ህይወት ቀያሪ ጽንሰ-ሀሳብ ውሰድ፡፡ እሱም ብናውቀውም ባናውቀውም፣ ብናምነውም ባናምነውም አሁን ያለን ብዙው (ከ95% በላይ) ውስጣዊ ማንነታችን እኔ የምንለው ማንነት ምንነቱን የማናውቀው በደመነፍስ ከስተጀርባ ሆኖ የሚነዳን ያኔ በህጻንነታችን በቅርባችን ከነበሩ ሰዎች የቀዳነው ማንነት (ስዕብና፣ የልቦና ውቅር፣ እምነት እና ልማድ ወዘተ) ነው፡፡
ውድ አንባቢዎች ከላይ ካለው ሀተታ በመነሳት እስኪ ጥቂት ቀላል የሚመስሉ ግን ጠጠር ያሉ ጥያቄዎች እናንሳ፡-
1. አንተ ማነኝ ብለህ ታስባለህ?
2. ከአእምሮህ የሚመነጩ ሃሳቦች በእውኑ ያንተው ሃሳቦች ናቸውን?
3. ታዲያ ከአእምሮህ የምታመነጫቸውን ሀሳቦችስ እንዴት ታምናቸዋለህ?
በእኔ እምነት እኔ የምትለው ይህ ሰው ትክክለኛ ማንነትህ አይመስለኝም፡፡
ለጊዜውም ቢሆን በእርግጠኝነት እኔ ብለህ ደረትክን ነፍተህ የምትናገርለት ማንነት
ያለህ አይልመሰለኝም፡፡
በመሆኑም ራስህንና ከውስጥህ የምታመነጫቸወን ሃሳቦች ለጊዜው በጥርጣሬ እና በጥንቃቄ
እያቸው እላለሁ፡፡
እኔ በግሌ ይህንን እውነታ ከተረዳሁበት ጊዜ ጀምሮ ራሴን እና ከአእምሮየ የሚመነጩትን ሃሳቦች በጥርጣሬ እና በጥንቃቄ ነው የማያቸው፡፡
በመሆኑም በህይወታችን እውነተኛ ስኬታማ ሰው ለመሆን የመጀመሪያው እና ብቸኛው የቤት ስራችን ያኔ በህፃንነታችን ሳናውቅ በድብቁ አእምሯችን ከሌሎች የቀዳነውን የሌሎች ሰዎች ማንነት (ስዕብና፣ የልቦና ውቅር፣ እምነት እና ልማድ ወዘተ) የራሳችን በሆነ አዲስ ማንነት (ስዕብና፣ የልቦና ውቅር፣ እምነት እና ልማድ ወዘተ) መተካት ነው፡፡
አንዴ ቆም ብለህ አስብ፡-
o ዛሬ አሁንኑ ልትተገብረው የምትችለው ከዚህ ጽሁፍ የተማርከው አንድ … ሁለት … ሶስት … ወዘተ ሃሳብ ምንድን ነው?
o ስላንድ ነገር ብዙ መረጃ መኖር ዕውቀት ነው፤ መረጃውን በተግባር መጠቀም ደግሞ ጥበብ ነው እና አሁንኑ በተግባር ግባ!
ጥያቄ፣ አስተያየት፣ ተጨማሪ ሃሳብ ካለ በዚህ ድህረ-ገጽ ፃፉልን!
መልካም አዲስ የስኬታማ ማንነት ግንባታ ጊዜ እመኛለሁ!
0 አስተያየቶች