ከዳዊት ገ/እግዚአብሔር ትልቅ ህልም አለኝ ከተሰኘው ድንቅ መጽሐፍ ሳነብ ያገኘውትን እና የብዙዎቻችንን ታሪክ የሚወክል እጅግ በጣም አስተማሪ የሆነ አንድ ደንቅ ታሪክ ላቅርብልህ፡፡ 

ከዕለታት ባንድ ቀን አንድ የንስር እንቁላል ከብዙ ዶሮ እንቁላሎች ጋር ይቀላቀል እና ሁሉም እንቁላሎች ወደ ጫጩት ይፈለፈላሉ፡፡ የንስር ጫጩቱም አብረውት ከተፈለፈሉት የዶሮ ጫጩቶች ጋር ዶሮዎች ያገኙትን ነገር በመለቃቀም እና በመመገብ መኖር ጀመረ፡፡ ከዶሮ ጫጩቶች ጋር በማደጉ እጅግ በጣም በከፍተኛ ከፍታ መብረር እና ምግቡንም በኩራት እና በብቃት ማደን የሚችል መሆኑን ረስቶታል፡፡ 

ከዕለታት አንድ ቀን የእርሱው ዘር የሆነው አንድ ንስር አሞራ በላያቸው ላይ በምጥቀት፣ በብቃት እና በፍጥነት ሲበር በማየት በዚህ ውብ የንስር አሞራ መብረር ብቃት እጅግ በጣም ተገረመ፣ ተደመመም፣ መብረርን ተመኘም፤ ነገር ግን ራሱ ማን እንደሆነ ስላላወቀ እና ከዶሮ ጫጩቶች ጋር ስለኖረ እና የዶሮ ጫጩትነት ማንነት (ስዕብና፣ የልቦና ውቅር፣ እምነት እና ልማድ ወዘተ) ስለቀዳ እና ስለተላበሰ ኑሮውን እንደ ዶሮ ጫጩት ያገኘውን ነገር ከመሬት በመለቃቀም ዕድሜውን ጨርሶ ሞተ ይላል፡፡

በእኛ በሰዎችም እየሆነ ያለው እንዲሁ ነው፡፡ በአጠቃላይ እንደ ሰው፣ እኛ ሰዎች በክርስቶስ አምሳል መፈጠራችንን ረስተን፣ ማን እንደሆን እና ምን ማድረግ እንደምንችል፤ እንዲሁም እያንዳንዳችን እንደ ሰው እና እንደ ግለሰብ የራሳችን የሆነ ተሰጥኦ፣ ክህሎት፣ ችሎታ እና መልካም አጋጣሚ መረዳት እና መገንዘብ ብሎም መጠቀም አቅቶን በአሁኑ ሰዓት እየከፈልን ያለውን ተገቢ ያልሆነ በምድር ላይ አለ የተባለ የአሉታዊ ነገሮችን እና ክስተቶችን ገፈት እየተጎነጨን እንገኛለን፡፡ 

ዳዊት ገ/እግዚአብሔር ትልቅ ህልም አለኝ መጽሐፍ የሽፋን ገጽ 



ገና ከጅምሩ በመሰረታዊነት ሁሌም እና በእያንዳንዱ ቅጽበት ልናስበው እና ልብ ልንለው የሚገባው ሀቅ ሰው ሁሉን በሚችለው በኃያሉ እግዚአብሔር አምሳል መፈጠሩን ነው፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ለስኬታችን የሚሆን እና ከዚያም በላይ ሆኑ አስፈላጊ ነገሮች እኛው ራሳችን ውስጥ መሆናቸውን እና ንቃተ-ህሊናችን ጨምሮ እስክንጠቀማቸው እየጠበቁን መሆኑንም እንዲሁ፡፡ 

ይሁን እንጅ ያኔ ህፃን እያለን በቅርባችን በነበሩት ሰዎች ስለነዚህ ህይወትን ቀያሪ ስለሆኑ መሰረታዊ እውነታዎች ባለመማራችን ይባስም ብሎ ስለ ህይወት አስቸጋሪነት፣ ውጣውረድ፣ ስለጤና መጥፋት፣ ስለገንዘብ እጥረት እና ሌሎችም አሉ ስለተባሉ አሉታዊ ነገሮች ሲወራ እየሰማን እና ሲተገበር እያየን በማደጋችን ይህንን እውነታ መረዳት አልቻልንም፡፡

በመሆኑም የሰው ልጅ በምድር ላይ ሲኖር በህወቱ በጤና ማጣት፣ በገንዘብ እጥረት፣ በግንኙነት መበላሸት፣ በትዳር መፍረስ … በመሳሰሉት ውጣውረዶች ውስጥ መኖርን እንደ አምላክ ፍርድ አድርገን እንኖራለን፡፡

ሁሉን ቻይ በሆነው በኃያሉ እግዚአብሔር አምሳል መፈጠራችንን ረስተን ይልቁንም ራሳችንን በዙሪያችን ባለው ሁኔታ፣ ሰው፣ ክስተት፣ በምንኖርበት አገር የኢኮኖሚ ደረጃ እና በነዚህ ውጫዊ ሁኔታዎች ተመስርተን ንቁ አዕምሯን የውጭውን ዓለም በማየት ሚነግረን መረጃ ራሳችንን በመወሰን ለህይወት ስኬታችን እና ከዛም በላይ የሚሆኑ አምላካችን በነፃ የሰጠንን እጅግ ገደብ የለሽ አቅምና ችሎታ፣ እንደ እንቁ እጅግ ውድ የሆኑ ረቂቅ ስጦታዎቹን ማለትም አዕምሮ፣ ሃሳብ፣ ስሜት፣ ፍቅር፣ ምስጋና፣ ደስታ፣ ነፃነት፣  ልባዊነት … ወዘተ እንዲሁም ግዙፍ ስጦታዎቻችንን ማለትም የአካል ክፍሎቻችን ከትንሹ ከህዋሳት እስከ ትልቁ ጭንቅላት፣ ፀሐይ፣ አየር፣ ውሃ … ወዘተ የመሳሰሉትን በህይወት ዘመናችን በየዕለቱ እና በየቅጽበቱ ከማመስገንና ከማድነቅ ይልቅ እንደ ተራ ነገር በመቁጠር በቀለሉ በክፍያ ስለሚገኙት ነገሮች ማለትም ስለ ገንዘብ፣ ቤት፣ መኪና፣ ልብስ … በህይወት ዘመናችን በየዕለቱ እና በየቅጽበቱ በማሰብ እና በመጨነቅ የዚቸችን ዓለም ህወት አንድም ቀን እና ቅጽበት ሳናመሰግን፣ ሳናደንቅ እና ሳንረካ ወደ ማያልፈው ወደ ወዲያኛው ዓለም እንሄዳለን፡፡ የወዲያኛውን ዓለም ህይወታችን ምንነት እረሱ አምላካችን ይወቀው፡፡

በስተመጨረሻ ውድ አንባቢየ ንተስ ይህንን ታሪክ ስታነብ ምን ተሰማህ? ከዚች ቅጽበት ጀምሮ ምንስ ለማድረግ ተነሳሳህ? ምንስ ለማድረግ ወሰንህ? የሚሆነንን እናስብ፣ እንገነዘብ፣ እንወስን እና አንተገብር ዘንድ በዚህም ጉዟችን ለሚገጥመን ፈተናና እና ውድቀት መስዕትነት እንከፍልም ዘንድ፤ ፈተናው ከመስዋዕትነታችን በልጦ ከጣለን አሁንም ከውድቀታችን ምህርት በመውሰድ አካሂዳችንን በመገምገም እና አስፈላጊ ማስተካከያ በማድረግ ደግመን ደጋግምን ከወደቅንበት በመነሳት ለምንሻው የህይወት ስኬት እንደምንበቃ በእምነት እንና፡፡

ምናልባት ይህንን ስታነብ ይህ ለእኔ የሚሆን አይደለም፡፡ ካለሁበት ፈተና እና ከምኖርበት ሀገር፣ አካባቢ፣ የስራ ቦታ እና የመሳሰሉት አንፃር ለእኔ ስለስኬት ማውራ ቅንጦት ነው፡፡ ጽድቁ ቀርቶ በቅጥ በኮነነኝ ልትል ትችላለህ፡፡ 

ስኬት እንደሚገባህ እና ስኬታማ መሆን እንደምትችል እምነት ለመገንባት እና ዛሬ ካለህብት ማንኛውም ሁኔታ ተነስተህ ስኬታማ ለመሆን ሰው ማን እንደሆነ እና ምን ማድረግ እንደሚችል እንደ ሃይማኖትህ ቅዱሳን መፃሕፍትን እና የዳዊት ገ/እግዚአብሔርን ትልቅ ህልም አለኝ እና ሌሎችንም መጻሕፍት አንብብ፡፡


ጥያቄ፣ አስተያየት፣ ተጨማሪ ሃሳብ ካለ በዚህ ድህረ-ገጽ ፃፉልን!


መልካም ንባብ