በተመስጦ ውስጥ ሆኘ የራሴን ህይወት ወደ ኋላ ተመልሸ ስዳስስ ካገኘዋቸው ትልቅ ዋጋ ያስከፈሉኝ (በራስ ያለመተማመን መንስኤዎች) የልጅነት ህይወት ገጠመኞች መካከል ለዛሬው አንዱን ታሪክ ልንገርህ አንተም እንዲሁ ታደርግ ዘንድ፡፡

ይህንን ታሪክ ስነግርህ ዋናው ዓለማየ አንተም በልጅነት ህይወትህ ወቅት ተመሳሳይ እና ሌሎች የህይወት ገጠመኞች ገጥመውህ ከሆነ እና ባላወከው መንገድ እስካሁን በህይትህ ዋጋ እያስከፈሉህ ያሉ ገጠመኞች ካሉ በተመስጦ ውስጥ ሆነህ ወደ ኋላ ህይወትህ ጠልቀህ በመግባት እንድትረዳቸው እና ወዲያውኑ አስፈላጊ የአመለካከት ማስተካከይ እንድታረግ ነው፡፡

ከዚህ ውጭ ወላጆቸን እና ቤተሰቦቸን በታሪኩ የጠቀስኬትን ወንድሜም ጨምሮ በሚችሉት ሁሉ ላደረጉልኝ ያላሰለሰ እንክብካቤ እና ከትትል፣ ሳይማሩም ስላስተማሩኝ እጅግ በጣም ነው የምወዳቸው እና የማከብራቸው፡፡

እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ በቤተሰባችን ውስጥ በተነፃፃሪ ከቤተሰብ አባላቱ እኔ በቆዳ ቀለም ጠቆር ያልኩ ነኝ፡፡ በዘህም ምክንያት ልጅ እያለሁ ምናልባትም 8-10 ዓመት ዕድሜዬ በዚህ የቆዳ ቀለም ልዩነት ምክንያት በመጀመሪያ በቤተሰቡ አባላት ባሪያ የሚል የቤት ስም ተሰጠኝ፡፡ ስም ይወጣ ከቤት ይቀበል ጎረቤት እንዲሉ በመቀጠል ነገሩ ወደ ጎረቤት አልፎ የጎረቢቱ መጠሪያ ስሜ ሆነ፡፡ እኔም በዚያ ልጅነት ዕድሜዬ ይህን ስሰማ ቀልድ መሆኑ ስለማይገባኝ እጅግ በጣም አዝን፣ እናደድ እና አንዳንዴም የማንነት ጥያቄ ይነሳብኝ ነበር፡፡

የሁለት ጊዜ ታላቅ ወንድሜ፣ ተዋበ ታዴ በቤቱ እጅግ በጣም ቀልደኛ እና አስቂኝ ነበር፡፡ በየዕለቱ የተለያዩ እውነትም ሆኑ ሀሰት ትርክቶችን እያቀነባበረ ለቤተሰቡ በማቅረብ በቤተሰቡ የቡና መጠጥ ሰዓት ሳቅ እና ጨዋታ በመፍጠር ይታወቃል፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ እውነትነት የሌለው ለእርሱ በቤተሰቡ በቡና ሰዓት ሳቅ እና ጨዋታ መፍጠሪያ፤ ለእኔ ለታዳጊው ግን እጅግ በጣም ልብ ሰባሪ እና ከባድ እውነት የሚመስል ትርክት አቀነባብሮ ነገረኝ፡፡ የውሽት ትርክቱም እንዲህ ነበር፡፡ አንተ እኮ ከቤተሰቡ በተለየ ጥቁር የሆንከው የእኛ ልጅ ስላልሆንክ ነው ሲል ነገረኝ፡፡ በነገሩ ግራ ስጋባ በማየት ጉዳዩን የበለጠ ሲያብራራው እንዲህ አለኝ፡፡ ከዕለታት ባንድ ቀን አባታችን ታዴ ሰውሁሉ ወደ ሆነ ቦታ ጉዞ ሲሄድ ከድንጋይ ስር ተጥለህ አግኝቶህ ነው አንስቶ ይዞህ መጥቶ እኛ በበጎ ፈቃደኝነት እያሳደግንህ ያለነው ሲል ነገረኝ፡፡

ይህንንም የበለጠ አሳማኝ ለማድረግ እና ስሜቴን በጥልቀት ለመንካት በወቅቱ አባታችን ወድቄ አግኝቶኝ ይዞኝ ሲመጣ ምን ያህል በጣም ቀጭን እና ጥቁር እንደነበርኩ እንዴት በስዕላዊ መንገድ የነገረኝን ዛሬ ላይ ሳስበው ለእንድ 8-10 ዓመት ለሆነው ታዳጊ ህፃን እንኳን የራሱ ታሪክ ነው ተብሎ ተነግሮት ቀርቶ የሌሎች ሰዎች ታሪክ ነው ተብሎ ቢነገረው እንኳን ምን ያህል ልቡን ሊሰብረው እንደሚችል ገምቱ፡፡

በመሆኑም ይህን ታሪክ በተነገረኝ ዕለት ሙሉ ቀን እጅግ ከባድ የመሸማቀቅ፣ የበታችነት፣ የሀዘን፣ የጸጸት ስሜት እና ለቅሶ አደረኩ፡፡ ይህንንም ሁኔታ ለቤተሰቡ ለመተረክ እና ለማሳቅ እንዲመቸው ወንድሜ ተዋበ ስሜቴን እየኮረኮረ የበለጠ ያሸማቅቀኝ፣ ያሳዝነኝ እና ያስለቅሰኝ ቀጠለ፡፡ ከዚህም ሁነት በኋላ ወደ ቤተሰቡ ስንቀላቀል ወንድሜ ተዋበ ጉዳዩን አነሳው እና የበለጠ ማልቀስ ጀመርኩ፡፡ ቤተሰቡም ከፊሎቹ በተዋበ የሃሰት ታሪክ አመሰራረት ችሎታ በመደነቅ እና እኔ በማሰማው የመንሰቅሰቅ ለቅሶ በመገረም ሲስቁ ከፊሎቹ ደግሞ ነገሩ ሃሰት እንደሆነ ሊነግሩኝ ሲሞክሩ እኔም የሆንኩትን ሆኘ የራሴን ግንዛቤ በውስጤ ይዤ ህይወት ቀጠለች፡፡

ገጠመኙን አሁን ላይ ሆኘ ሳስበው ለካ ተጥሎ የተገኘ፣ የማይታወቅ ቤተሰብ ልጅ የሚለው አስቂኝ መሳይ የሃሰት ትርክት ነገር ግን ለእኔ ለወቅቱ ታዳጊ እውነት የመሰለኝ ታሪክ በውስጤ የበታችነትና የአልረባምነነት እውነታ ሆኖ በውስጤ ተወቅሮ ኖሯል፡፡ ከዚህም የተነሳ እኔ ምንም በማላውቀው እና በማልጠብቀው ሁኔታ በራስ መተማመኔ (ስለራሴ ያለኝ ግምት ዝቅተኛ መሆን) ከሰዎች ጋር ያለኝ ግንኙነት ውስንነት፣ እንዲሁም መሆን፣ ማግኘት እና መስራት የምፈልገውን ሁሉ መሆን፣ ማግኘት እና መስራት እንደማልችል በውስጤ የተወቀረ እውነታ ሆኖ ኖሮ በነበረኝ የተመስጦ ጌዜ ወደ ውሰጤ በጥልቀት ገብቸ በማግኘት ተረዳሁት፡፡

እናም ያን በውስጤ የተወቀረውን የውሸት ትርክት መሆኑን መረዳት ቻልኩ፡፡ በመሆኑመም አሁን ያለኝ ሙሉ እምነት እና እውነታው እንደማንኛውም ሰው አምላኬ በአምሳሉ ከገደብ አልባ አቅም እና ችሎታ ጋር ስለፈጠረኝ እና አስፈላጊውን መስዋዕተነት እሰከከፈልኩ ድረስ መሆን፣ ማግኘት እና መስራት የምፈልገውን ነገር ሁሉ ያለምንም ጥርጥር እንደምሆን፣ እንደማገኘውና እንደምሰራው ሙሉ እምነት አለኝ፡፡

ይሀንንም እምነት ሆነ ብየ ለራሴ ደጋግሜ በመንገር እና በመፃፍም ጭምር ገነባሁት፡፡ እናንተም ተመሳሳይ እና ሌሎች የልጅነት አሉታዊ ገጠመኞች ካሏችሁ ሳታውቁት በድብቅ ወደ ኋላ ስለሚስቧችሁ ልክ እንደ እኔ በተመስጦ በመሆን የመለየት ስራ ሰርታችሁ አዎንታዊ የሆነውን እምነት መገንባ ትችላላችሁ፡፡

ዛሬ ላይ እኔ ራሴ እገዚአብሔር ፈቅዶ ለሁለት ልጆች ወላጅነት ስለበቃሁ አምላኬን እያመሰገንሁ ነገር ሁሉ ለበጎ ነው እንዲሉ ወላጆቸ ባለማወቅ ይሰሯቸው የነበሩ የልጅ አስተዳደግ ስህተቶችን መረዳቴን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም በልጆቸ እና በማውቃቸው እና በማገኛቸው ማንኛውም የጎረቢት እና የጓደኞቸ ህፃናት ላይ ገዳቢ የአስተዳደግ ዘዴዎችን ለመሞገት የተቻለኝን አደርጋለሁ፡፡ ስለልጆች አስተዳደግ እና ስለልጆች ሁለንተናዊ ዕድገት አሉ የተባሉትን ሁሉ ማጣሻ መጽሐፍ መጽሐፍን ቅዱስን ጨምሮ በተቻለኝ እያነበብኩ በልጆቸ ህይወት ላይ በተግባር እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡ ለዚህም እግዚአብሔር ይመስገን፡፡

ከታሪኩ እንደምንረዳው ብዙዎቻችን በእንደዚህ እና ማናልባትም በባሰ ቤተሰብ ውስጥ ልናድግ እንችላለን፡፡ አሁንም ቢሆን በከተማም ሆነ በገጠር አካባቢ አብዛኛዎች ህፃናት እያደጉ ያሉት እንዲሁ ነው፡፡ የታሪኩ መልክ ሊቀየር ቢችልም በከተማም አለ፡፡ ብዙዎቻችን ቢያንስ ታናናሽ ወንድም እና እህቶች አለበለዚ ልጆች በቤት ውስጥ ይኖሩናል እና ከዚህ ቅጽበት ጀምሮ ለልጆች የምንነግራቸውን ታሪክ፣ ሃሳብ እንዲሁም የምሳያቸውን ተግባር ልብ እንበል፡፡

ለግንዛቤም ያህል ልጠይቃችሁ:-

1. ምን ያህሎቻችንስ እንዲህ እና ሎሎች መሰል ገጠመኞች በህይወታችን ገጥመውናል?

2. ወይም የማንን ተመሳሳይ ታሪክ ታውቃላችሁ?

3. ምንስ ዋጋ አስከፍለውናል? ምንስ ዋጋ እያስከፈሉን ነው?

4. ከእኒህ ገጠመኞች ለመዳንስ ምን መንገድ ተጠቀማችሁ?

5. ምን ያህሎቻችን ህፃናት ወንድም እህቶቻችንን፣ ልጆቻችንን ለእነሱ ከማይመጥኑ ለእኛ ቀልድ ከሚመስሉ፣ ለእነሱ ግን የወደፊት ህይወታቸውን የሚወስኑ የስህተት ታሪኮች፣ ከማይመጥኗቸው ንግግሮች፣ ክርክሮች፣ ድርጊቶች፣ የቴሌሌቪዥን መርሃ-ግብሮች እና ከመሳሰሉት ነገሮች እንጠብቃለን?

ለጥያቄዎቹ መልስ እንዲሁም ተመሳሳይ ታሪክ እና አስተያየታችሁን በዚህ ድህረ-ገጽ ፃፉልን፡፡  

 

መልካም የንባብ ጊዜ፡፡