የመነሻ ሀሳብ
ስሜት ማለት በውስጣችን ወይም በውጭ ለሚከሰቱ ሁኔታዎች ሁሉ ስለሁኔታዎች ባለን አመለካከት መሠረት የሚኖረን አእመሯዊ ሁኔታ ወይም ምላሽ ነው፡፡ ስሜታችን በማንኛውም ጊዜ ከእኛ ጋር ነው፡፡ በህይወት እስካለን ድረስ ከስሜት ውጭ የምንሆንበት አንዳችም ቅጽበት የለም፡፡ ስሜት የእያንዳንዳችን ህይወት የመገንባት ወይም የማፍረስ ሚና የሚጫወት የህይወታችን የመሰረት ድንጋይ ነው::
በማንኛውም የህይወታችን ቅፅበት ውሳኔዎችን እንድንወስን እና በወሰነውም መሠረት እንድንሰራ በማድረግ የስራችንን አጸፋ ውጤት እንድናገኝ የሚያስችለን ስሜት ነው። ስለሆነም ሰው በማንኛውም ቅጽበት ለውስጣዊ እና ውጫዊ ሁኔታዎች ያለውን የራሱን ስሜት የመቆጣጠር ክህሎት በህይወታችን ለቅጽበት ችላ የማይለው ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡
ለዚህም ነው ሰው በህይወቱ ማሰብ እና ማተኮር ያለበት ትልቁ ጉዳዩ ምን እንደደረሰበት ማሰብ ሳይሆን በህይወቱ ለደረሰበት ምን ምላሽ መስጠት እንደለበት ማሰብ ነው የሚባለው፡፡ ምክንያቱም በህይወቱ ስለሚደርስበት ነገር አሰበም አላሰበም ይደርስበታል፡፡ ስለሚሰጠው ምላሽ ግን አእምሮውን ተጠቅሞ በማሰብ ስሜቱን በመቆጣጠር ለክስተቱ የሚሰጠውን ምላሽ በራሱ መወሰን ይችላልና::
ስሜቶቻችን ሙሉ በሙሉ በእራሳችን ቁጥጥር ስር ናቸው፡፡ እንዲያውም ስሜቶቻችን በአግባቡ እና በብልሃት ከተጠቀምንባቸው እንደ ህይወት አማካሪያችን ሆነው ያገለግላሉም፡፡
በዙሪያችን ያለው ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ለምሳሌ እንደ ፍቅር ወይም ጥላቻ፣ ደስታ ወይም ሀዘን፣ ጥሩ ወይም መጥፎ፣ ጤና ወይም ህመም፣ ስኬት ወይም ውድቀት ብቻ የፈለገነውን ስሜት መላበስ እና ማንጸባረቅ እንችላለን። ወሳኙ ጥያቄ ግን የትኛውን ስሜት ብንላበስ እና ብናንጸባርቅ ይሻለናል ነው፡፡ አዎንታዊውን ወይስ አሉታዊውን፣ ገንቢውን ወይስ አፍራሹን?
ሁላችንም አዎንታዊውን እና ገንቢውን እንደምንል አልጠራጠርም፡፡ አው፣ ሁኔታው ምንም ይሁን ምን፣ አዎንታዊውን እና ገንቢውን ስሜት መላበስ እና ማንጸባርቅ ይሻለናል እንችላለንም፡፡
ልብ ካልክ አንተ ማለት ከስሜቶችህ እጅግ በጣም ከፍ ያልክ እና የራስህን ስሜት መቆጣጠር የምትችል እና የማይናወጥ መሰረት ያለህ ሰው መሆንህን በሀይወትህ መመስከር እና መግለጽ ትችላለህ።
ስሜት በህይወታችን ውስጥ እንዴት እንደሚሰራ እና ምን ያህል በራሳችን ቁጥጥር ስር እንደሆነ በተረዳንበት ቅጽበት፣ በእኛ ላይ ለሚከሰቱ ውጫዊ ክስተቶች ያለን አመለካከት እና ምላሽ ሁሌም አዎንታ እና ገንቢ ይሆናል። በእኛ ላይ የሚከሰት እያንዳንዱ ውጫዊ ሁኔታ ወይም ክስተት ሙሉ በሙሉ በራሳችን ቁጥጥር ውስጥ ባሉ ስሜቶች መልክ የሚከሰት የአዕምሮ ጨዋታ መሆኑንም እንገነዘባለን፡፡
ከዚህም ጋር ተያይዞ በህይወታችን በሚከሰቱ ማናቸውም ክስተቶች በእኛ ላይ የሚያስከትለት ውጤት በእኛው ቁጥጥር ስር ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህንን እውነታ በተረዳን ጊዜ እና በራሳችን የዕለት ተዕለት ህይወት ውስጥ ልምምድ በምናደርግበት ጊዜ፣ ምንም ነገር ከመሆን፣ ከማግኘት እና የፈለግነውን ከማድረግ የሚያግን አንዳች ነገር እንደሌለ ሙሉ በሙሉ ግልጽ ይሆንልናል። ብሎም ምንም ዓይነት ተግዳሮት ስኬታማ ከመሆን እንደማያግደን እንገነዘባለን፡፡
በአጠቃላይ በማንኛውንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆነን የፈለግነውን ስሜት መላበስ እና ማንጸባርቅ እንችላለን፡፡ በመሆኑም የምንፈልገውን ስሜት መላበስ እና ማንጸባርቅ ምንም አይነት ሁኔታ አይገድበንም፡፡
ስሜቴቻችንን የመቆጣጠር እና ማስተዳደር ክህሎት ሲኖረን ማንም ሰው እና ምንም ዓይነት ሁኔታ በምንም መንገድ እኛን ዝቅ ማድረግም አይችልም፡፡ ራሳችን እያወቅን በንቁ አዕምሯቸን ወይም ሳናውቅ በድብቁ አዕምሯቸን ካልፈቀድንለት እና የዝቅተኝነት ስሜትን ካልተላበስን እና ካላንጸባረቅን በስተቀር፡፡ ከእግዚአብሔር በነፃ ከተሰጡን የሰው ልጅ ስጦታዎቸ መካከል በማንኛውም ሁኔታ የምንፈልገውን ስሜት የመላበስ እና የማንጸባረቅ ችሎታ አንዱ ነው፡፡
ለዚህም በማንኛውም የሀይወት ሁኔታ ውስጥ ሆነህ የሚጠቅምህን ስሜት የመላበስ እና የማንጸባረቅ ልማድ በተደጋጋሚ ሆነ ብለህ በመለማመድ ገንዘብህ ማድረግ አለብህ፡፡ ይህንን ያደረክ እንደሆን በምንም ዓይነት ፈተና ውስጥ ሆነህ እንኳን ሳይቀር ነገሮችን በስኬት የምትከውንበት መንገድ ይታይሃል፡፡
ከዚህም በኋላ ራስህን በስሜትህ አሳንሰህ መግለጽ የለብህም እኔ ተናዳጅ ነኝ፣ እኔ አይናአፋር ነኝ፣ እኔ ... ወዘተ ብሎ ነገር የለም፣ ማለት የለብህም፡፡ ይልቁንም አንተ ከእነዚህ ሁሉ በላይ ነህና::
ለጥያቄዎች ምላሽ፣ ለቀረቡት ሃሳቦች ማንኛውም ሀሳብ፣ አስተያየት ወይም ጥያቄ ካለ በዘህ ድሀረ-ገጽ ፃፉልን።
0 አስተያየቶች