መነሻ ሃሳብ
ብዙ ሰው ስኬታማ ለመሆን ብዙ ገንዘብ፣ ስልጣን፣ ሃብታምና ስኬታማ ዘመድ፣ የበለጸገች ሃገር፣ ትልቅ ከተማ ... ወዘተ የሚያስፈልግ ይመስላዋል። ዳሩ ግን እውነታው ተቃራኒው ነው።
ሰው በህይወቱ ስኬታማ ለመሆን ከላይ ከዘተረዘሩት አንድም ነገር ሊኖረው ግድ አይደለም።
በመጀመሪያ የሰው ልጅ ከውስጡ ተነሳስቶ የሚታትረው እና ማድረግ ያለበትን ሁሉ የሚያደርገው ከላይ ተዘረዘሩትን ለማግኘት ነው፡፡
ደስ የሚለው ደግሞ እኒህን ነገሮች ለማግኘት በሚያደርገው የሌት ተቀን መታተር አንድ እጅግ በጣም ታታሪ እና ጠንካራ፣ በብዙ እውቀቶች እና ክህሎቶች እንዲሁም ጥበቦች የተሞላ ማንነት ያለው ሰው ይሆናል፡፡
ምክንያቱም ለመታተር፣ ለመበርታት እና ሌት ከቀን ለመስራት በቂ ምክንያት አለውና፡፡ ይህም ምክንያት የሚፈልገውን ገንዘብ፣ ስልጣን፣ ሃብት ... ወዘተ በአጠቃላይም ስኬትን ማግኘት ነው፡፡
አንድ ሰው እኒህ ነገሮች ካሉት ስለምን እና ምንን ለማግኘት ብሎ ሊታትር ይችላል?
ምናልባት የበለጠ ለማግኘት ሊታትር ይችል ይሆናል፡፡ እውነት ነው የበለጠ ለማግኘት ለመስራት ሊነሳሳ ይችላል፡፡
ነገር ግን ቢያንስ እንዳንተ ምንም ነገር እንደሌለህ ያህል ለመስራት የመነሳሳት ዕድሉ ዝቅተኛ ነው፡፡ ለማለት የፈለኩት ዋናው ነገር ስኬታማ ለመሆን ብዙ ገንዘብ፣ ስልጣን፣ ሃብታምና ስኬታማ ዘመድ፣ የበለጸገች ሃገር፣ ትልቅ ከተማ ... ወዘተ እንደማያስፈልግህ ነው፡፡
ልብ ብለህ ካሰብከው ቢያንስ ቢያንስ ለጊዜው እኒህ ነገሮች በእጅህ አለመኖራቸው አንተን የበለጠ እንድትሰራ እና እንድትተጋ ከእንቅልፍህ የሚቀሰቅሱህ የማንቂያ ደወሎች ናቸው፡፡
በመሰረቱ ስኬት የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ የምተይበት መንገድ ሌላው በሚገባ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው።
ምከንያቱም ለስኬት ከላይ የተዘረዘሩት ያስፈልጋሉ ብሎ የሚያስብ ሰው ስኬትን የሚያይበት ወይም የሚተረጉምበት እና የሚረዳበት መንገድ የዛተባ የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ ነውና፡፡
ለማንኛውም ብታስተውላቸውም ባታስተውላቸውም ለስኬትህ የሚያስፈልጉህ ነገሮች እና ከዚያም በላይ አሁንኑ በውስጥህ እና በዙሪያህ ይገኛሉ፡፡
አኔም ይህንን ጽሁፍ ያዘጋጀውበት ዋና ዓላማ፡-
አንደኛ ለስኬት የሚሆኑህ ነገሮች በሙሉ አምላክህ ሰው ከመሆንህ ማንነት ጋር በስጦታ መልኩ ጠቅልሎ የሰጠህ በራስህ ውስጥ እና በዙሪያህ ያሉ ስጦታዎች መሆናቸውን እንድትረዳ፡፡
ሁለተኛ ለስኬት የሚሆን ነገር የለኝም ብለህ እጅህን ኣጣጥፈህ እንዳትቀመጥ ይልቁንም በውስጥህ እና በዙሪያህ በማስተዋል እንድታገኛቸው ለማድረግ፡፡
ሶስተኛው እና የመጨረሸው ዓላማ ከብዙ ስጦታዎች መካከል ዋና ዋናዎችን በመጥቀስ ልብ እንድትላቸው እና ከዚህ ቅጽበት ጀምሮ በአግባቡ ተጠቅመህ ተፈጥሯዊ የሆነውን ስኬታማ ህይወት እንዲኖርህ ለማድረግ ነው፡፡
ልብ በል:-
እኒህ ለስኬት የሚያገለግሉህ ዋና ዋና ስጦታዎች ሰው መሆን፣ አዕምሮ፣ ጊዜ፣ ደመነፍስ፣ ነፃነት፣ አየር፣ ውሃ፣ የፀሐይ ብርሐን፣ የዘመኑ ቴክኖሎጂ … ወዘተ ናቸው፡፡
በጥቁቱ ለማብራራት ያህል:-
ንቁ አዕምሮህ ... ምትፈልገውን አዲስ ወይም የነበረ ሃሳብ የምታመነጭበት እና የምታስታውስበተ እንዲሁም አሁን በኣካል የሌለን ነገር በምናብ በአካል ምትፈጥርበት
ድብቁ አዕምሮህ ... መልካም ልማዶችን በመገንባት ህይወትህን በቀላሉ የምትመራበት
ጊዜ ... የምትፈልገውን ማንኛውም ትንሽ ወይም ትልቅ ተግባር የምትከውንበት
ደመነፍስ ... ከአእምሮህ በላይ የሆኑ ጥያቄዎችን ወይም ፈተናዎችን መልስ የምታገኝበት
ነፃነት ... የምትፈልገውን የማድረግ እና የማትፈልገውን ያለማድረግ ሙሉ የመምረጥ ዕድል የምትጎናጸፍበት
አየር፣ ውሃ፣ የፀሐይ ብርሐን ... በህይወት በጤና እንድትኖር
በዘመኑ ቴክኖሎጂ (ኢንተርኔት እና ሌሎችም) ... አማካኝነት የምትፈልገውን ማንኛውንም መረጃ፣ እውቀት፣ ጥበብ … ወዘተ በነፃ ያለምን ክፍያ ተሰጥቶሃል፡፡
ወዘተ ...
ለበለጠ ግንዛቤ
የሁሉም ረጅም ርቀት ጉዞዎች በአንድ እርምጃ ይጀመራሉ እንዲሉ በዚህ ምድር ላይ አሉ የተባሉ ስኬታማና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎችን የወደ ኋላ ታሪካቸውን ተመልሰህ ብታጠና የሆነ ቀን እንደ ማንኛውም ሰው ተራ ነበሩ::
እንዲያውም የህይወት ዝቅታ ላይም ነበሩ፡፡ ታውቃለህ ትስማማለህም፣ ማንም ስኬታማ ሆኖ የተወለደ ሰው የለም፤ ስኬታማ ህይወቱን በጥረት የመሰረተ እንጅ፡፡
o አደራ እኒህ ስኬታማና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች በተወለዱበት አገር፣ ቤተሰብ ... ወዘተ እንዳትታበይ፡፡
o እኒህ አይነት ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች አንተ በምትኖርበትም ሃገር እና አንተ ካደክበት ቤተሰብ ጋር ተመሳሳይ እንዲያውም ያነሰ የኢኮኖሚ ደረጃ ቤተሰብ ... ወዘተ ያላቸው አሉና፡፡
እንዲሁም አሉ የምትላቸው የዓለም ትልልቅ ድርጅቶችም እንደነ ዋልማርት፣ አፕል፣ አማዞን፣ ማይክሮሶፍት ... ወዘተ የሆነ ቀን አልነበሩም፡፡
ይልቁንም ከዜሮ ገንዘብ ግን አንተም አሁንኑ ካለህ ከሃሳብ ብቻ ነው የተነሱት ማለትም ምንም ገንዘብ ሳይኖራቸው ሃሳብ ብቻ ባላቸው ሰዎች ነው የተጀመሩት፡፡
በመቀጠልም ሃሳባቸውን ተጠቅመው ገንዘብ አገኙ ወይም ገንዘብ ካለው ሰው ጋር ተደራጁ፡፡
o ሃሳብ ለማፍለቅም ገንዘብ ያስፈልጋል እንዳትለኝ፤ ይህንን ካልክ አእምሮም በገንዘብ ይገዛል እያልክ መሆኑን አስብ::
ስለሆነም ለህይወትህ ስኬት ገንዘብ፣ ስልጣን፣ ሃብታምና ስኬታማ ዘመድ፣ የበለጸገች ሃገር፣ ትልቅ ከተማ ... ወዘተ አስፈላጊ እንዳልሆነ አስብበት፡፡
የተግባር ሃሳቦች
ስለሆነም እንደ ቤት ስራ የምሰጥህ በፍጥነት ቆም ብለህ አሁን ካለህበት የተዘበራረቀ የህይወት እና ከተዛባ የስኬት እይታ እንዴት እንደምትወጣ አስብ፡፡
በህይወትህ ልታሳካው ባሰብከው ነገር ላይ ስኬታማ የሆኑ ከ3-5 ሰዎች እንዴት ስኬታማ እንደሆኑ እና ምን እየሰሩ እንደሆነ በሚገባ ህወታቸውን አጥና፡፡
የእነዚያንም ሰዎች አሰራር፣ አዋዋል፣ ባህሪ፣ አስተሳሰብ ... ወዘተ ላንተ በሚሆንህ መልኩ በመቀመር በተግባር የመኖር ልምምድ አድርግ::
ያኔ ልብ ብለኸው የማታውቀውን እና አይቻልም ብለህ በራስህ አእምሮ የዘጋኸውን የስኬት ህይወት መንገድ ትረዳለህ፡፡
ጥያቄ፣ አስተያየት፣ ተጨማሪ ሃሳብ ካለ በዚህ ድህረ-ገጽ ፃፉልን!
0 አስተያየቶች