የመነሻ ሃሳብ

በእኔ እምነት በሀገራችን በአብዛኛው ልጆችን የምናሳድግበት መንገድ ከአባቶቻችን የተወረሰ እና ዘመኑን የማይዋጅ ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ ብዙ የሃገራችን ወላጆች፣ አሳዳጊዎች እና ተንከባካቢዎች አስቸጋሪ ባህሪ ወይም ልማድ ላቸውን ልጆች አብዝቶ በመገሰጽ፣ በመሳደብ፣ ሲከፈም በመቅጣት እና አጥብቆ በመቆጣጠር ማስተካከል እንዳለበት ያምናል፡፡ ይህ በጥንቃቄ ሊታይ የሚገባው በእርግጥ ከአሁን ዘመናት በፊት ሊሰራ ይችላል፤ አሁን ግን ሊሰራ የማይችል አስተሳሰብ ነው፡፡

በቅድሚያ በግልጽ መታወቅ ያለበት ዋናው ነገር ልጆቻችን ይህንን ጥሩ ያልሆነ ባህሪ ወይም ልማድ ይዘውት አልተወለዱም፡፡ ይልቁንም በአብዛኛው በቤት ውስጥ እኛው ወላጆች፣ አሳዳጊዎች ወይም ተንከባካቢዎች ራሳችን እና አንዳንዴም ከጎረቤት እና ከቅርብ ጓደኛ የተቀዳ ወይም የተወረሰ የመሆኑ ሀቅ መረዳት እና ማመን ያስፈልጋል፡፡

ለዚህ ማሳያ ቀላል ምሳሌ እንውሰድ፡-

ለምሳሌ ልጆቻችን አብዝተው ቴሌቪዥን መመልከት እና የሞባይል ጫወታ አብዝተው የመጫወት ልማድ፣ ሱስ ወይም ባህሪ አላቸው እንበል፡፡ በእውኑ ልጆቻችን እነዚህን ባህሪያት፣ ልማዶች፣ ሱሶች ይዘዋቸው ተወልደዋልን? ልጆቻችንን ቴሌቪዥን አብዝተው እንዳያዩ እና የሞባይል ጨዋታ እንዳይጫወቱ መገሰጽ እና መቅጣት መፍትሄ ነውን? ወይስ ራሳችን ወላጆች፣ አሳዳጊዎች ወይም ተንከባካቢዎች ቴሌቪዥን የምንከፍትበትን ሰዓት መወሰን እና ሞባይል ለልጆቻችን የምንስጥበትን ሰዓት መወሰን ነው ያለብን? መልሱ ግልጽ ነው፡፡ 

ታዲያ ይህንን ማድረግ አሁንኑ እንጀምር፡፡ ቴሌቪዥን አብዝቶ ማየትን እና የሞባይል ጫወታን እንደ ምሳሌ አቀረብን እንጅ ሁሉም የህጻናት ልማዶች፣ ጥሩ ያልሆኑ ባህሪያት እና ሱሶች በአብዛኛው የሚወረሱት ከወላጆች፣ ከአሳዳጊዎች ወይም ከተንከባካቢዎች እና አንዳንዴ ከጎረቤት እና ከቅርብ ጓደኛ ነው እና ልጆቻችንን ለማስተካከል እና ለመገሰጽ ከመሞከራችን በፊት ምንጩ ላይ እንስራ እላለሁ፡፡

በመቀጠልም ሌላው በግልጽ መታወቅ ያለበት ህፃናትን በምንቀጣበት ጊዜ በአብዛኛው በዚያ ቅጽበት በልጃችን ላይ ያለንን የራሳችን ስሜት ማለትም ቁጣችንን፣ ንዴታችን፣ ብስጭታችንን እና ሃዘናችንን የምንገልጽበት መንገድ እንጅ የልጆችን ባህሪ ለማስተካከል የተደረገ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ ከዚህም በከፋ ልጆቻችን በተደጋጋሚ እንዲህ ናችሁ፣ እንደዚያ ናችሁ (ረባሽ፣ ሰነፍ፣ ውሸታም … ወዘተረፈ) ናችሁ የምንላቸውን ማንነት ነን ብለው ያምኑታል፣ ይቀበሉታል፣ የደረጉትማል (ይህንን ሃሳብ ቢያንስ ሶስት ጊዜ አንብቡት)፡፡ 

ይህ ለብዙ ወላጆች ለእኛ ለታላላቆች ሳይቀር የሚሰራ ግን የማንገነዘበው ሌላው ትልቅ ምስጢር ነው እና ልብ ልንለው ይገባል፡፡ በመሆኑም ይህ አካሄድ የልጆችን ባህሪ ከማስተካከል ይልቅ በልጆች አካላዊ፣ ስነልቦናዊ፣ አእምሯዊ እና ማህበራዊ ህይወታቸው ላይ የበለጠ አፍራሽ እና አሉታ ተጽእኖ ያሰድራል፡፡ በመሆኑም ልጆችን ከአስቸጋሪ ባህሪያቸው ወይም ልማዳቸው ለማስተካከል በመጀመሪያ ከልጁ ጋር ቀላል፣ ግልጽ እና መልካም ግንኙነት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ እርግጥ ነው ይህንን ለማደረግ ከባድ እና ትዕግስት የሚጠይቅ ተግባር ነው፡፡ ግን በእርግጠኝነት መደረግ የሚችል እና ራሴ በተግባር ሰርቸው ጥሩ ውጤት ያገኘሁበት መንገድ ነው፡፡

የልጆቻችንን ስሜት፣ አመለካከት (ስለራሳቸው እና ስለነገሮች)፣ ስነልቦና እና ማህበራዊ ግንኙነቱ እንዲሁም ማንኛውንም የህይወት ገጽታ በጥንቃቄ እና በጥልቀት ማጥናት እና ማጤን ያሰፈልጋል፡፡ እንዲሁም በተቻለ መጠን ለልጆቻችንን የባህሪ መዛነፍ ምክንያት የነበሩትን ነገሮች እንዲሁም እየሆኑ ያሉ ነገሮች ካሉ በልጆቻችን ህይወት ዙሪያ የነበሩ እና አሁኑንም ያሉ ነገሮችን በጥንቃቄ እና በጥልቀት ማጥናት እና ማጤን ወሳኝ ነው፡፡ 

በዚህም ጥናት ጊዜ ለልጆቻችን ባህሪ መዛነፍ ምክንያት እየሆኑ የነበሩ እና አሁንም እየሆኑ ያሉ ነገሮች ካሉ ልጁ ላይ ከመስራታችን በፊት እኒህ ነገሮች ላይ መስራት፡፡ አለበለዚያ ዛፉን ከስሩ ላይ ሆኖ አንዳች ተባይ ስሩን በመቦረቦር እያደረቀው እያለ ቅጠሉን የማከም ያህል ነው እና እናስብበት፡፡

የተግባር ሃሳቦች፡-

ከላይ በምሳሌው እንደቀረበው ልጆቻችን ከእኛ ከወላጆች፣ ከአሳዳጊዎች ወይም ከተንከባካቢዎች ይሁን ከጎረቤት እና ከቅርብ ጓደኛ ያልተፈለገ ባህሪን ወይም ልማድን ተላበሱ እንበልና:- 

ለልጆ ስላ አላስፈላጊ ባህሪያት ወይም ልማዶቻቸው አስተያየቶች ሲሰጡ ስለሚጠቀሟቸው ቃላት እና ስለ ድግግሞሹ ይጠንቀቁ፡፡ ምክንያቱም አላስፈላጊ ባህሪያት ወይም ልማዶቻቸው እንዲተው በሚል በአሉታዊ ስሜት በተሞሉ ቃላት እና በተደጋጋሚ የሚገስጿቸው ከሆነ እነኛ አላስፈላጊ ባህሪያት ወይም ልማዶቻቸው በውስጣቸው በመስረጽ እንደ ማንነታቸው መገለጫ አድርገው የበለጠ ለአላስፈላጊ ባህሪያት ወይም ልማዶቻቸው ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉና፡፡

ልጆቻችንን ከእነዚህ አላስፈላጊ ከሆኑ ባህሪያቸው እና ልማዳቸው እንዲላቀቁ ለማድረግ በዚያ አላስፈላጊ ባህሪ እና ልማድ ዙሪያ በደንብ በማንበብ እና መርሃ-ግብር በመንደፍ ማወያየት፣ ማስተማር፣ መምከር፣ መርዳት፣ መንገዶችን ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ ቀስ በቀስ ያኔ ልጆቻችን ጥሩ ያልሁኑ ባህሪያት ወይም ልማዶች እንዴት እንደሚጎዷቸው ስለሚገነዘቡ የመተው ፍላጎት እና መተው እንደሚችሉ ሃሳብ ይመጣላቸዋል፡፡


ጥያቄ፣ አስተያየት፣ ተጨማሪ ሃሳብ ካለ በዚህ ድህረ-ገጽ ፃፉልን!


ልጆች ድንቅ የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው!


መልካም ጊዜ ከውድ ልጆዎ ጋር!