መነሻ ሃሳብ
ሰው የእጅ ስልኩ፣ ላፕቶፑ እና ሌሎችም የኤሌክተሮኒከስ እና የኤሌክተሮኒከስ ያልሆኑ መሰሪያዎቹ እንዴት እንደሚሰሩ እና በአጠቃቀም ግድፈት ብልሽት ቢገጥማቸው ደግሞ እንዴት እንደሚጠገኑ ለመረዳት የተቻለውን ሁሉ ጥረት ያደርጋል፡፡
ይሁን እንጅ የህይወታችንን ዕጣ-ፈንታ የሚወስነውን አእምሯችንን እንዴት እንደምንጠቀምበት እና እንዴት እንደሚሰራ ለማወቅ የኤሌክተሮኒክስ መሳሪያዎቻችን ያህል እንኳን ጥረት አናደርግም፡፡
አእምሯችን እንዴት እንደምንጠቀመው ባለማወቃችንም በእያንዳንዱ የህይወት ቅጽበታችን አእምሯችን እኛን ይጠቀምብናል፡፡
ምናልባት ከዚህ በፊት ባለው ህወታችን ብዙዎቻችን ልብ ላንለው እንችላለን፡፡ ሆኖም ግን ልብ አልነውም ልብ አላልነውም የአእምሯችን አጠቃቀም የህይወት ስኬት እና የህይወት ጥራታችንን በእጅጉ ተጽዕኖ ያደርጋል፡፡
ስለሆነም ከዚህ ቅጽበት ጀምሮ ልብ ብለን እና አስበን ሆነም ብለን አእምሯንን መጠቀምን መለማመድ አለብን፡፡
የሰው ልጅ አእምሮ
እግዚአብሔር ከሁሉም ፍጥረታት በተለየ መልኩ ለሰው ልጆች ከሰጠን ስጦታዎች ከመንፈሳዊ ማንነትችን በመቀጠል አእምሯችን ትልቁ እና ድንቅ የነፃ ስጦታችን ነው፡፡
እግዚአብሔር እኛን የሰው ልጆች በመንፈሳዊ ማንነታችን እልቆ-ቢስ ከሆኑ የማይታዩ መልካም ነገሮች ውቂያኖስ ጋር ያገናኘን ሲሆን እኒህን እልቆ-ቢስ መልካም ነገሮች በፈጠራ ወይም በግኝት መልኩ በህይወታችን /በገሃዱ ዓለም/ ወደ መገለጥ የምናመጣቸው አእምሯችንን ተጠቅመን ነው፡፡
ለዚህም ነው ሰው በአእምሮው ያሰበውን እና በልቡ ያመነውን ማንኛውም ነገር የማግኘት ይችላል የሚባለው፡፡
ሆኖም ግን ይህንን በህይወታችን በተግባር ለመጠቀም ስለ መንፈሰዊ ማንነታችንን ከመረዳት በመቀጠል አእመሯዊ ማንነታችን ማለትም የአእምሯችን ምንነት እና አሰራር በሚገባ ማወቅ እና በተግባር የመጠቀም ልምምድ ማድረግ አለብን፡፡
አለበለዚያ ግን የአእምሯችንን ምንነት እና አሰራር ካላወቅን በተገላቢጦሽ አእምሯችን እኛን ይጠቀምብን እና የምንፈልገውን ማንኛውም ነገር ማግኘት ቀርቶ በምድር አሉ የተባሉ የህይወት አሉታዊና አስከፊ ነገሮችን እያስተናገድን መኖር እንገደዳለን ማለት ነው፡፡
ሶስቱ የሰው ማንነት ገጽታዎች |
የአእምሯችን ምንነት
ብዙ ሳይንሳዊ ጽሁፎች እንደሚስማሙበት የሰው ልጅ አእምሮ ሁለት ክፍሎች አሉት፡፡ ንቁ ወይም አመዛዛኙ አእምሮ እና ድብቁ ወይም የማያመዛዝነው አእምሮ ናቸው፡፡
የንቁ ወይም የአመዛዛኙ አእምሯችን አሰራር
ንቁ አእምሮ አዳዲስ ሃሳቦችን ማመኝጨት፣ ሃሳቦችን ማመዛዘን እና የሚስማሙትን ሃሳቦች መቀበል እና የማይስማሙትን ውድቅ ማድረግ ይችላል፡፡
ንቁ አእምሮ መረጃዎችን በአምስቱ የስሜት ህዋሳቶቻቸን ብቻ ያገኛል፣ ይቀበላል፡፡
እኒህ የንቁ አእምሮ ጠንካራ ጎኖች ሲሆኑ የንቁ አእምሮ ደካማ ጎኖች አንድን ሃሳብ ለረጅም ጊዜ ይዞ የመቆየት ችሎታ እና ትዕግስት የለውም፣ መረጃ ከቁሳዊ ነገር ብቻ ማለትም ከሚታይ እና ከሚዳሰስ ይቀበላል እንዲሁም አቅሙ ውስን ነው፡፡
የድብቁ ወይም የማያመዛዝነው አእምሮ አሰራር
ድብቁ አእምሮ በንቁ አእምሮ የመነጩ ማንኛውንም አዳዲስም ሆኑ የነበሩ ሃሳቦች ሲደጋገሙለት ያለምንም ማጣራት ይቀበላል፣ ለረጅም ጊዜ (ለህይወት ዘመን ሙሉ) ይዞ የመቆየት አቅም እና ትዕግስት አለው እንዲሁም አቅሙ ገደብ አልባ ነው፡፡
ድብቁ አእምሮ መረጃዎችን ከአምስቱ የስሜት ህዋሳቶቻቸን በንቁ አእምሮ ከማግኘት በተጨማሪ በህይወታችን ከገጠሙን የህይወት ተሞክሮዎችና ከራሱ ከውስጠ-ህሊና በደመ-ነፍስ /intuition/ መልኩ ያገኛል፣ ይቀበላል፡፡
የድብቁ አእምሮ ደካማ ጎኖች ሃሳቦችን ማመዛዘን አይችልም ይልቁንም የተደጋገሙለትን ማናቸውንም ሃሳቦች (አሉታዊ እና እኛን የሚጎዱም ሃሳቦች ሳይቀር) በመቀበል የህይወታችን እውነታዎች ያደርጋል፡፡
አእምሯችንን መጠቀም
አእምሮችን የመጠቀም የመጀመሪያው መንገድ የሃሳብ ምንጮቻችንን (በተለይም በአምስቱ የስሜት ህዋሳቶቻችን የምንቀበላቸውን መረጃዎች) በጥንቃቄ በመምረጥ በስሜት ህዋሳቶቻች ወደ አእምሯችን የሚገቡ መረጃዎችን ለራሳችን የሚጠቅሙንን ብቻ ማድረግ ላይ ነው፡፡
ሁለተኛው አእምሮን የመጠቀም መንገድ አንዳንዴ ትልልቅ የህይወት ውሳኔዎችን ለመወሰን አስፈላጊ መረጃዎችን ከተለያዩ ምንጮች ለማግኘት በምንቸገርበት ጊዜ ወደ ውስጣችን በአርምሞ እና በተመስጦ ሆነን በማዳመጥ ከራሳችን ውስጠ-ህሊና መራጃ ማግኘ እንችላለን፡፡
በመሆኑም ከሌሎች የመረጃ ምንጮች አብዝተን ከመፈለግ ይልቅ የራሳችንን ውስጠ-ህሊና እንደ ታማኝ የመረጃ ምንጭ መጠቀምም እንችላለን፡፡
ሶስተኛው አእምሮን የመጠቀም መንገድ የንቁውን እና የድብቁን አእምሮ አሰራር እና ደካመ ጎኖች በመረዳት እጅግ በጣም ከምናስበው በላይ የህይወት ስኬት ማለትም በህይወታችን የምንፈልገውን ማንኛውም ነገር ለማግኘት መጠቀም ነው፡፡
ይህንንም በተለይ ልንተኛ በተቃረብንበት እና ከእንቅልፋችን እንደተነሳን ማለትም ንቁ ወይም አመዛዛኙ አእምሮ በሰመመን /በድንግዝግ/ በሚሆንበት ጊዜ መጠቀም በጣም ውጤታማ ነው፡፡
አእምሯችን እኛን ሲጠቀምብን
ከላይ በተገለጸው የድብቁ አእምሯችን አሰራር መሰረት በአግባቡ ካልተጠቀምነው መሉ ለሙሉ ተኝተን በእንቅልፍ ውስጥ ሆነንም ሆነ በንቃት እያለን ልክ እንደ ድብቅ መቅረጸ-ምስል /ካሜራ/ እና ድብቅ መቅረጸ-ድምጽ /ቴፕ ሪከርደር/ የሚጠቅመንንም ሆነ የማይጠቅመንን ብሎም የሚጎዳንን ማነንኛውም በአይናችን በተደጋጋሚ ያየነውን መረጃ በምስል መልኩ በመቅረጽ እና በጆሯችን በተደጋጋሚ የሰማነውን መረጃ በድምጽ መልኩ በመመዝገብ የህይወታችን እውነታ ያደርገዋል፡፡
በጣም የሚከፋው ነገር ከዚህ ቅጽበት በኋላም ማንኛውንም በህይወታችን ለማድረግ ወይም ላለማድረግ ዋናው የድርጊቱ ትክክለኛነት ማጣቀሻ የሚሆነው በዚህ በምስል ወይም በድምጽ መልኩ በተቀረጸ መረጃ መሰረት ይሆናል፡፡
በስተመጨረሻም ብንሰራው እንደሚጠቅመን እያወቅን አንሰራውም፣ ባንሰራው እንደሚጎዳን እያውቅን እንሰራዋለን፡፡ ለዚህም በጎጅ በሱስ የተጠመዱ ሰዎች ህያው ምስክሮች ናቸው፡፡
ስለሆነም ሰው ከመቸውም በላይ ሊተኛ ሲል፣ ከእንቅልፉ እንደተነሳ እንዲሁም በተደጋጋሚ እና ለረጅም ጊዜ የሚያስበውን ሃሳብ፣ የሚያየውን እና የሚሰማውን መረጃ እጅግ በጣም መምረጥ አለበት፡፡
የተግባር ልምምድ ሃሳብ
ውድ አንባቢየ ከዛሬ እና ከዚህ ቅጽበት ጀምሮ አእምሮህን በአግባቡ ለመጠቀም በአምስቱ ህዋሳቶችህ በተለይም በአይንህ የምታያቸውን መረጃዎች እና በጆሮህ የምትሰማቸውን እንዲሁም በተደጋጋሚ እና ለረጅም ጊዜ የምታስባቸውን ሃሳቦች በአንክሮ እና በጥንቃቄ ምረጥ፡፡
የእረፍት ጊዜየ ነው ብለህ የማይሆንህን መረጃ ከመቀበል ተጠንቀቅ፤ በአያንዳንዷ ቅጽበት ህይወትህን ወደ ሆነ አቅጣጫ እየወሰድክ መሆኑን ተረዳ፡፡
ልትተኛ ስትል፣ ከእንቅልፍህ እንደተነሳህ፣ በተደጋጋሚ እና ለረጅም ጊዜ የምታስባቸውን ሃሳቦች፣ የምታያቸውን እና የምትሰማውን መረጃዎች እጅግ በጣም በጥንቃቄ ምረጥ፡፡
አንዴ ቆም ብለህ አስብ፡-
o አሁንኑ ልትተገብረው የምትችለው ከጽሁፍ የተማርከው አንድ ... ሁለት ... ሶስት ሃሳብ ምንድን ነው?
o ስላንድ ነገር ብዙ መረጃ መኖር ዕውቀት ነው፤ መረጃውን በተግባር መጠቀም ደግሞ ጥበብ ነው!
አስተያየት ተጨማሪ ሃሳብ እንዲሁም ጥያቄ ካለህ በዚሁ ድህረ-ገጽ ፃፉልን!
2 አስተያየቶች
በጣም ጠቃሚ ፅሑፍ ነው፡፡ እናመስግናልን ወንድሜ !!
ምላሽ ይስጡሰርዝለገንቢ አስተያየትዎ እጅግ በጣም እናመሰግናለን!
ምላሽ ይስጡሰርዝ