መልካም ነገሮች

ለእያንዳንዱ ሞሊሴ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ለሚያስፈልጉ ሂደቶች /ቢሮ ለማመቻቸት፣ የዩኒቨርሲቲውን E-mail እና Wifi ID ለማግኘት የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች ቅን ትብብር መኖር::

በእያንዳንዱ ከዩኒቨርሲቲው ውጭ ላሉ ሂደቶች /ኢሚግሬሽን ቢሮ ላለው ሂደት፣ ከባንክ ደመወዝ ለመቀበል፣ የከተማው መታወቂያ ለማውጣት ...ወዘተ/ አብሮን ጉዳይ የሚያስፈጽም የተመደበልን መሆኑ::

ከታች በምስሉ እንደምታዩት የዩኒቨርሲቲው ግቢ አንድ ህንፃ ብቻ ስላለው ግቢውን ለማወቅ እና ለመልመድ ብዙ ጊዜ የማይወስድ መሆኑ::     

ሞሊሴ ዩኒቨርሲቲ፣ አንድ ህንፃ ግን አንድ ካምፓስ (ታህሳስ፣ 2014 ዓ.ም በአለባቸው ታዴ)

                                    

ከጉዞ በፊት የሰራናቸው ስህተቶች

የአየር በረራ ትኬት ክፍያ

የትራነስፖርት ብር በዚያን ዓመት ባልሳሳት ወደ 32000 ብር ያህል ከዛው ከሞሊሴ የአየር በረራ ትኬት ቆርጠን እንላክላችሁ ወይም ቆርጣችሁ ስትመጡ እናወራርድላችሁ የሚል የአማራጭ ጥያቄ ቀርቦልን ነበር፡፡ ሆኖም በይሉኝታ ራሳችን ቆርጠን ስንመጣ ታወራርዱልናላችሁ ብለን መለስን:: ሆኖም እኔ በበኩሌ ከወንድሜ ተበድሬ ለመቁረጥ ተገድጃለሁ::  ከዚህም እንደዚህ እና መሰል ምርጫዎች ሲቀርቡልን በይሉኝታ ሳይሆን መሆን ያለበትን መወሰን እንዳለብኝ ተምሪያለሁ፡፡

በኢትዮጵያ የጣሊያን ኢመባሲ በኢሜል በመጠበቅ ያጠፋነው ጊዜ

በመጀመሪያ ሰዎች ስንጠይቅ እና ኦንላይን ስናይ ለቪዛ ሂደት ኦንላይን ማመልከት እንደምንችል እና የኦንላይን መሙያ ፕላትፎረሙን አግኝተን ከሁለት ሳምንት ያላነሰ ጊዜ አጥፍተናል፡፡ በኋላ ባጣራነው መሰረት ግን የኢመባሲው ኦንላይን ሲስተም አፕዴት ስላልተደረገ እንደማይሰራ እና በአካል አዲስ አበባ በሚገኘው የጣሊያን ኢምባሲ ማመልከት እንዳለብን ስላወቅን ሄደን ሂደቱን ለመጨረስ ችለናል:: ስለሆነም አሁንም የኦንላይን ማመልከቻው ፕላትፎርም መስራቱን እና አለመስራቱን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

የገጠሙን ፈተናዎች

እንግሊዝኛ  ቋንቋ

በኢጣሊያን አገር ብዙ ሰው በሮም ፊዩሚሲኖ አየር ማረፊያ ያሉ ሰራተኞች ይቀር እንግሊዝኛ  ቋንቋ ስለማይጠቀሙ በፊዩሚሲኖ አየር ማረፊያ እንደደረስን የሚቀበለንን ሰው መድረሳችንን ደውለን ለማሳወቅ እጅግ በጣም ተቸግረን ነበር፡፡ በመጨረሻ ባጋጣሚ ኢትዮጵያዊ አግኝተን በመደወል ፈተናውን ተወጣነው፡፡ ነገር ግን ይህ እንግሊዝኛ  ቋንቋ ችግር በሄድንበት ሞሊሴ ከተማ የባሰ ችግር ሀኖ አገኘነው:: በተለይ ሱቅ ስንሄድ ስለተቸገርን በ google translator ተጠቅመን አማርኛውን ወይም እንግሊዝኛ ወደ ጣሊያንኛ በመተርጎም መግባባት ጀመርን፡፡ እናም አሁን ሲገባኝ አየር ማረፊያም የገጠመንን አለመግባባት በgoogle translator አማርኛን ወይም እንግሊዝኛን ወደ ጣሊያንኛ በመተርጎም እንዲደውሉልን እርዳታቸውን መጠይቅ እንችል እንነበር በተረድቻለሁ እና ይህንን ዘዴ መጠቀም ይቻላል፡፡

እጅግ ከፍተኛ ቅዝቃዜ

እጅግ በጣም ከፍተኛ ቀዝቃዛ (እስከ 1◦) የሆነው የክረምት የአየር ጠባይ (ጥር፣ የካቲትና መጋቢት) ለተለያዩ ህመሞች ተጋልጠን ነበር፡፡ ወዲያውኑ አካባቢውን የሚመጥን ልብስ (ጃኬት፣ ሹራብ እና ጫማ) በመግዛት ከህመማችን አገገምን፡፡

የአድሪያቲክ ባህር በሞሊሴ፣ ጣሊያን (መጋቢት፣ 2014 ዓ.ም በአለባቸው ታዴ)


አሌክትሮኒክስና ልብስ የሚሸጥበት ቦታ

አሌክትሮኒክስና ልብስ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚሸጥበትን ቦታ ባለማወቃችን ውድ በሆነ ዋጋ ስንገዛ ቆይተናል፡፡ ከዕለታት ባንድ ቀን በተመጣጣኝ ዋጋ የሚሸጥበትን ቦታ አግኝቸ የተወሰኑ ልብሶችን በጣም በተመጣጣኝ ዋጋ መግዛት ችያለሁ፡፡ ስለሆነም ማንም ሰው ወደ ሞሊሴ እና ሌሎች የአውሮፓ አገሮች ሲሄድ ይህንን አሌክትሮኒክስና ልብስ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚሸጥበትን ቦታ ማወቅ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡  

የምግብ ችግር

ሱቅ ሄደን የምንፈልገውን ዓይነት ምግብ ለማግኘት ተቸግረን ነበር፡፡ እኛ በነበርንበት ሞሊሴ ከተማ በተለይ የኢትዮጵያ እንጀራ የማይታሰብ ነው፡፡ በእርግጥ ሮም ከተማ በቀላሉ እንደሚገኝ ሰምቻለሁ፡፡ ሞሊሴ ከተማ ግን ለማግኘትም ብዙ አልሞከርንም የሚገኝም አይመስለኝም፡፡ ከዛ ውጭ ባብዛኛው ስንጠቀማቸው የነበሩ ምግቦች ፓስታ፣ መኮረኒ፣ ሩዝ፣ ዳቦ፣ ከፍራፍሬዎች ደግሞ አፕል፣ ሙዝ፣ ብርቱካን ... ናቸው፡፡ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ ስንሆን ደግሞ በአየር የታሸገ ውሃ፣ ፔፕሲ እና ከታች የምታዩት ፕሉም ኬክ በአብዛኛው እንጠቀም ነበር::


 ሞሊሴ ዩኒቨርሲቲ የምግብ እና መጠጥ ማሽኑ ውስጥ ከሚገኙ ኬኮች አንዱ (መጋቢት፣ 2014 ዓ.ም በአለባቸው ታዴ)


የቤት ኪራይ

የምንፈልገው ቤት በተመጣጣኝ ዋጋ አለማግኘት ሌላው ፈተና ነበር፡፡ ምንም እንኳ ከሞሊሴ ዩኒቨርሲቲ በተፃፈልን ደብዳቤ መሠረት የመኖሪያ ቤት ወጪ ዩኒቨርሲቲው እንደሚሸፍን የሚገልጽ ቢሆንም ከሄድን በኋላ የተነገረን ግን በራሳችን መሸፈን እንዳለብን ነበር፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ያኔ እኛ የሄድንበት ወቅት በኮኮሮና ምክንያት ለ10 ቀናት ለይቶ ቆየት ግድ ስለነበር ባለ 4 ኮከብ ሴንትረም ፓላስ በሚባል ውድ ሆቴል ለ10 ቀናት ተብሎ ገባን፡፡ ቀጥሎም ባላወቅነው ምክንያት ወሩን እንንቆይ ተደረግን፡፡ ከዛም ከአንድ ወር በኋላ ሌላ ቤት ለመከራየት ባደረግነው ሙከራ በሞሊሴ ከተማ አከራዮች መሰረት አንድ ሰው ቢያንስ የ6 ወራት መክፈል ግድ ሆነ:: በመሆኑም ከላይ በተጠቀሰው ባለ አራት ኮከብ የሆቴል አልጋ ውድ ክፍያ እየከፈልን ቆይተናል፡፡


የዩሮ ንቲሞች (ከ1 ሳቲም - 2 ዩሮ)



 

ጥያቄዎች ካ ጻፉልን!