የመነሻ ሃሳብ

ማንኛውም ሰው ይብዛም ይነስም፣ ይሰፋም ይጥበብም የራሱ እና የቤተሰቡ መተዳደሪያ የሚሆን ስራ አለው፡፡

በዚህም ስራ እንደ ስራው ባህሪ ቢለያይም ጊዜውን፣ ጉልበቱን እና ትኩረቱን ሁሉ ያፈሳል፡፡

ደስ የሚለው ነገር ግን የትኛውም ዓይነት ስራ ይሁን የእረፍት ወይም ትርፍ ጊዜ አለው፡፡

ምክንያቱም ሰው እንደ ማሽን ስላይደለና 24 ሰዓት በሙሉ መስራት ስለሌለበት፤ እረፍትም ስለሚያስፈልገው፡፡

ይህ የእረፍት ወይም ትርፍ ጊዜም እንደየአሰሪ ድርጅቶች የሚለያይ ሆኖ ከሰዓታት እስከ ቀናት እንዲሁም እስከ ሳምንታት የሚደርስ ሊሆን ይችላል፡፡

ያም ሆነ ይህ በዚህ ሁሉ በእጄ ሁሉ በደጄ በሆነበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን በህይወትህ ስኬታማ ለመሆን እንደምታስበው ብዙ ጊዜ ለማግኘት በሚል ስራ መቀየር ወይም ስራ መልቀቅ ግድ አይደለም፡፡

ይልቁንም አሁን የምትሰራውን ስራ ባግባቡ እየሰራህ ይህንን የእረፍት ወይም ትርፍ ጊዜ በአግባቡ በመለየት ለህይወት በሚያተርፍህ ነገር ላይ ማዋል ብትችልስ?

የዚህ ጽሁፍ ዋና ትኩረት

የዚህ ጽሁፍም ዋና ዓላማም ይህንን የእረፍት ወይም ትርፍ ጊዜ የራሳችን የምንለውን ህይወት የምንገነባበትን መንገድ መጠቆም ነው፡፡ 

ስለሆነም ውድ አንባቢዬ ይህንን ጽሁፍ በትክክል ገብቶህ ለህፃን ልጅ ሊገባው በሚችል መልኩ ማቅረብ እስከምትችል ድረስ ደጋግመህ አንብብ እና ተረዳው፡፡ 

በመቀጠልም ሃሳቦችን እና መንገዶችን ምንም ቀጠሮ ሳታበዛ በተረዳኸው ቅጽበት ወደ ተግባር ግባ፡፡ 

ጽሁፉን በሚገባ አንብበህ በህወትህ ምንም ቀጠሮ ሳታበዛ በተረዳኸው ቅጽበት የራስህን ማሻሻያ እያደረክ መተግበር ከጀመርክ በእርግጠንነት በተጨባጭ ህይወትህን አሁን ካለበት በጣም ወደ ተሻለ አቅጣጫ ይወስድሃል፡፡ 

በጽሁፉ ውስጥ በተነሱ ሃሳቦች እና አተገባበራቸው ላይ ለበለጠ ግልጸኝነት ለመወያየት ከፈለክ በኢሜል ብትጽፍልኝ ወይም በስልክ ብትደውልልኝ የምችለውን ለማስረዳት ደስተና እና ዝግጁ ነኝ፡፡

ወደ ዋና ርዕሰ ጉዳይ እንመለስ እና … 

እኛ ሃገር፣ ቢሮ፣ በእኔ አቅም እረፍት ወይም ትርፍ ጊዜ ምንም የሚሰራ ነገር የለም

አየህ ትልቁ ታሪካዊ ስህተት እዚህ ላይ ነው፡፡ 

እንደገና አእምሮህን ክፍት አድርገህ የሚከተለውን ሃሳብ አንብብ እና በተግባር መጠቀም እሰከምትችል ድረስ ተረዳው፡፡ ያኔ ምን እያልክ እንደሆነ ይገባሃል፡፡

እኛ ሃገር፣ እኛ ቢሮ፣ በእኔ አቅም ... ወዘተ የሚሰራ ስራ የለም ካልከ እኛ ሃገር፣ እኛ ቢሮ፣ በእኔ አቅም ... ወዘተ መፍትሄ የሚፈልግ ችግር እና የሚቃለል ህይወት የለም እያልከ እንደሆነ ተረዳ!

አንተ አሁን ተቀጥረህ ወይም በራስህ በምትሰራው ስራ በተጨባጭ የሰዎችን ችግር የሚቀርፍ ወይም የሰዎችን ህይወት የሚያቃልል ሃሳብ፣ ክህሎት እና ዘዴ ካለህ መልካም፡፡ 

ይህንን ሃሳብ፣ ክህሎትና ዘዴ ተጠቅመህ ገንዘብ ማግኘት ወይም ገንዘብ ካላቸው ጋር መደራጀት እና ሃሳቡን ወደ ተግባር መቀየር ትችላለህ፡፡

አሁንኑ ሃሳብ እና ክህሎት ከሌለህም መልካም፡፡ አሁን ካለህበት ማንኛውም የህይወት ሁኔታ ተነስና አሁን የምትሰራውን ስራ ባግባቡ እየሰራህ ባለህ የእረፍት ወይም ትርፍ ጊዜህ ከዚህ ቅጽበት ጀምረህ አሁን ተቀጥረህ ወይም በራስህ የምትሰራውን ስራ በተመለከተ ወይም ሌላ የምትፈልገውን የውስጥና የህወት ዝንባሌ (ራዕይ፣ ዓላማ ወይም ህልም በለው) ከውስጥህ ማግኘት ወይም ራስህ መፍጠር ትችላለህ፡፡ 

ስላለህ የእረፍት ወይም ትርፍ ጊዜ ብዛት እና አስፈላጊነት እንድታስብበት የሚያስችሉህ ጥያቄዎች ልጠይቅህ:-

1. በቀን ውስጥ /በ24 ሰዓት ውስጥ/ ምን ያህል /ደቂቃ፣ ሰዓት/ ትርፍ ወይም የእረፍት ጊዜ አለህ? በሳመንትስ? በወርስ? በዓመትስ?

2. ይህንን የእረፍት ወይም ትርፍ ጊዜ እሰካሁን ድረስ ባለው ህይወትህ እንዴት እያሳለፍከው ነው? ወደፊትስ?

3. ከዛሬ ጀምሮ ይህንን የእረፍት ወይም ትርፍ ጊዜ በሚገባ በመለየት እና በማጤን ብሎም ራሱን የቻለ መርሃ-ግብር በመንደፍ ከዚህ በታች የተቀመጠውን ሂደት በመጠቀም ህይወትህን ስኬት ብትገነባበትስ?

እንዳታደርግ የሚያግድህ ነገር ካለ አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት … ብለህ በኢሜል ፃፍልኝና እንነጋገር

ለመሆኑ በእረፍት ወይም በትርፍ ጊዜህ የምትሰራው ምንድን ነው?

o   ከልክ በላይ መተኛት፣

o   ተገቢ ያልሆነ የስልክ ጥሪን በማሳደድ ጊዜ፣ ገንዘብን እና ትኩረትን ማባከን፣

o   የማይጠቅምህን እንዲያውም የሚጎዳህን የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን መከታተል፣ 

o   ጭብጥ የሌለው ከባልደረባና ጓደኛ ጋር ውይይት ወይም ጉንጭ አልፋ ክርክር ማድረግ፣

o   አልባሌ ቦታ በመሄድ ጊዜን፣ ገንዘብን፣ ትኩረትን ማጥፋት፣ 

o   የሚተቹት ሰዎች ትችቱን ሰምተው ራሳቸውን ማስተካከል በማያስላችላው መልኩ ሰዎችን በመተቸት ጊዜን እና ትኩረትን ማባከን ... ወዘተ አንተን የሚገልጽህን ውሰድ ሌላም ካለ ጨምርበት እና ቆም ብለህ አስብበት፡፡

 

ሌላ ለራስህ የምትመልሰው ጥያቄ ልጠይቅህ፡


o   በምትሰራበት ድርጅት በእውኑ ያንተ የምትለው ሀሳብ፣ አሰራር፣ መመሪያ፣ ደንብ አለን? ከሆነ መልካም!

o   በምትሰራው ስራስ ደስተኛ ነህ? ውጤታማስ ነህ? ከሆነ መልካም!


ካልሆነስ:-


o   እስከመቸ ነው ሌሎችን ሰዎችን ሃሳብ እና ስራ መልሰህ በመደጋገም እየሰራህ የምትኖረው?

o   ድርጅትህ በእውኑ ያንተ የምትለው ሀሳብ፣ አሰራር፣ መመሪያ፣ ደንብ እንዲኖር ትፈልጋለህ?

o   በምትሰራው ስራስ ደስተኛ እና ውጤታማ መሆን ትፈልጋለህ?

እንደኔ ከሆንክ ከላይ ለተነሱት ጥያቄዎች የመለስካቸውን መልሶች መገመት አያዳግተኝም፡፡ 

አውቃለሁ፤ አሁን በእጅህ ከያዝከው የተሻለ ምርጫ የሌለህ ስለመሰለህ ነው፣ ልትሰራው የምትችለው አንዳች ስራ የሌለም ስለመሰልህ ነው፡፡ 

ምርጫ መኖሩን ስታውቅ ደግሞ በአንተ ሃገር፣ ቢሮ፣ አሁን ባለህበት የህወት ሁኔታወዘተ የማይቻል ስለመሰለህ ነው:: 

አሊያም በሌሎች የተገነባው ሰው-ሰራሽ ማንነትህ በተጨባጭ በየዕለቱ ተግባራትን በመውሰድ የተሻለ ማንነት እንዳትገነባ አስሮ ይዞሃል፡፡     

ይህም ያንተ ስህተት አይደለም፤ ከት/ቤት በትኩረት የተማርከው፣ ከማህበረሰቡ እና በዙሪያህ ካሉ ሰዎች በተደጋጋሚ የሰማኸው እና የሰማኸው በመንግስት ተቀጥሮ የደረጃ እድገት፣ ሌላ ስልጣን፣ ሌላ መስሪያ ቤት፣ ሌላ ስራ፣ ሌላ ገር ሌላ ወይም ተጨማሪ ዲግሪ ... ወዘተ መቀየር እና የተሻለ ህይወት መኖር እንዳለብህ ነው፡፡ 

በተቀጠርክበት ስራ ስራውን ከመቸውም በላይ በጥራት እና በፍጥነት እንዲሁም የተቀጠርክበት ስራ ፍላጎትህ ካልሆነ በራስህ ስራ ለመፍጠር አማራጮች እንዳሉህ እና መፍጠር እንደምትችል ከት/ቤት አልተማርክም፣ ከማህበረሰቡ እና በዙሪያህ ካሉ ሰዎች አልሰማህም፣ አላየህምም፡፡

ያም ሆነ ይህ ልብ ልትለው የሚገባው እውነታ በምትሰራበት መስሪያ ቤትም ሆነ በራስህ እልቆ-ቢስ የሆነ ልትሰራው የምትችለው ምርጫ እንዳለህ ነው፡፡ 

ይሁን እንጅ ከእልቆ-ቢሱ ምርጫዎችህ አንዱ ወይም ጥቂቶቹ ላይ ማተኮር ይኖርብሃል፡፡ ሁለት እግር አለኝ ተብሎ ሁለት ዛፍ ላይ እንደማይወጣ ሁሉ፡፡ 

ቀጣይ ህይወት ሁኔታ እና አቅጣጫህ ለመወሰን ከዚህ ቅጽበት ጀምረህ ይህንን ጽሁፍ በሚገባ በማንበብ፣ በመረዳት እና በህይወትህ የተግባር ልምምድ በማድረግ ህይወትህን በምትፈልገው መንገድ መምራት የየዕለት ልምምድህ ማድረግ ነው፡፡ 

3D printer while printing J-Trap of Fruit fly in Unimol, Italy (Just For Memory, 2022) 

ታዲያ እኔ ምን ልሰራ እችላለሁ?

አዎ እርግጥ ነው ያነሳሃቸው ሃሳቦች ጥሩ ስለሆኑ ተስማምቻለሁ:: 

ጥያቄዎችንም ለራሴ በመመለስ ያለኝን የእረፍት ወይም ትርፍ ጊዜ ተረድቻለሁ:: ነገር ግን አስካሁን እዚህ ግባ በማይባል የየዕለት ትርኪ-ምርኪ ነገር ላይ እያሰለፍኩት እንደሆነም ተገንዝቢያለሁ:: 

በምሰራበት /ቤት ወይም ድርጅትም የእኔ ምለው አሰራር እና መመሪያም የለም፡፡ ይልቁንም አለቆቸ እና ባልደረቦቸ የሰጡኝን አሰራር እና መመሪያ እየተገበርኩ ነው፡፡

ነገር ግን አሁን ከዚህ ቅጽበት ጀምሮ ባለኝ የእረፍት ወይም ትርፍ ጊዜ የእኔን ህይወት ስኬታማ የሚያደርግ ምን መስራት እና እንዴት መስራት እችላለሁእኛ ሃገር፣ እኛ /ቤት ወይም ድርጅት፣ በእኔ አቅምእኮ ምንም የሚሰራ ስራ የለም እንደምትለኝ ገመትኩ፡፡ 

መልሱን እንደሚከተለው አብረን እንመልከት …

እኛ ሃገር፣ እኛ መ/ቤት ወይም ድርጅት፣ በእኔ አቅም … እኮ ምንም የሚሰራ ስራ የለም ያልከው ሃሳብ በዚህ መንገድ ካሰብከው እና ካመንከው እውነት ትክክልም ነ፡፡ 

ምክንያቶችንም ከፈለክ (የሃገር በጦርነት መሆን፣ ድህነት፣ በቂ ልምድ አለመኖር፣ መነሻ ገንዘብ ማጣት፣ አስፈላጊ ነገሮች አለመኖር … ወዘተ ሌሎችን ምክንያቶችም መጨመር ትችላለህ) የእትየለሌ ታገኛለህ፡፡

እንዲሁም በእውን ራስህን መቀየር እና ስኬታማ መሆንን ብቸኛው የማትደራደርበት አማራጭ ብታደርግ እና ለዚህ ምርጫህ ማረጋገጫ ምክንቶችን ብትመረምር (የሃገራችን ህዝብ በጦርነት ስለተጎዳ ከመቸውም በላይ ራሱን የለወጠ ሰው ማስፈለጉ፣ ራስን ለመለወጥ ምንም ገንዘብ አለማስፈለጉ፣ በቂ ልምድ በልምምድ እንጅ በልደት የይመጣ መሆኑ፣ በትከክል በምንፈልገው ነገር ላይ ለረጅም ጊዜ ማተኮር ከቻልን ከኢንተርኔት ጋር ተያይዞ የምንፈልገውን ነገር ሁሉ በቀላል ማግኘት መቻላችን … ወዘተ ሌሎችን ምክንያቶችም መጨመር ትችላለህ) የእትየለሌ ምክንያቶችን ታገኛለህ፡፡ 

ስለዚህ ዋናው እና ትልቁ ጥያቄ የቱን ብትመርጥ ይጠቅምሃል ነው፡፡ አለበለዚያ ከላይ እነደየነው ከሁለቱ የፈለከውን አንደኛውን ብትመርጥ ትክክል ወይም ስህተት የመሆን/ያለመሆን አይደለህም፡፡ ምክንያቶች እስካሉህ ድረስ በሁለቱም መንገድ ትክክል ነህ! 

በነገራችን ላይ እንደምታውቀው መስሪያ ቤትህ ወይም አሰሪ ድርጅትህ በስራ ሰዓት ሙሉ ጊዜ፣ ጉልበት እና ትኩረትህን ለድርጅቱ እንድታውል ያስገድድሃል ደመወዝ ስለሚከፍልህ፡፡ 

ነገር ግን በእረፍት ወይም በትርፍ ጊዜህ ማለትም በግል ህይወትህ ከመኖሪያ ቤትህ ወይም የትም ከስራ ውጭ ባለህበት ቦታ መጥቶ ይህን ስራ ያንን አትስራ ሊለህ አይችልም፡፡ 

ይልቁንም በእረፍት ወይም በትርፍ ጊዜህ ምን ልትሰራ  እንደምትችል የምትወስነው አንተ ነህ፡፡  ስለዚህ በዚህ እረፍት ወይም በትርፍ ጊዜህ ምን ልተሰራ እንደምትችል እስኪ እንመልከት፡-

1. ሰው ማለት ምን ማለት እንደሆነ ብትረዳስ?

የዓለም እንቁ ነገር የተቀመጠው መፃህፍት ውስጥ ነው ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ አንድ ሰው ከስኬታማ ሰዎች ጋር በአካል ተገናኝቶ ምክሮች፣ ሃሳቦች ማግኘት ባይችልም ከፃፉት መፃህፍት ግን ማግኘት ይችላል፡፡ 

ያውም በዚህ ሰዓት ከመቸውም በተለየ በማንኛው ርዕሰ-ጉዳይ ላይ መፃህፍት በነፃ ከኢንተርኔት በሚገኙበት ዘመን ይህንን ማድረግ ለማንም አይከብድም፡፡ 

ስለሆነም መንፈሳዊ እና ሳይንሳዊ ጽሁፎችን በማንበብ ሰው ማለት ምን ማለት እንደሆነ መረዳት የማንኛውም ሰው ትልቅ የቤት ስራ ይመስለኛል፡፡ 

በእርግጥ ሰውን ለመረዳት በዓለምም ሆነ በሃገር አቀፍ ደረጃ በጣም ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ሰዎችን ስራ ማስተዋልና መረዳትም ትልቅ ምስክር ነው፡፡ 

ለምሳሌ ሰዎች እስካሁን ባለው እንኳን በሰማይ እንድንበር፣ ያለገመድ እንድንነጋገር እና እንድንግባባ፣ ወደ ሌላ ከመሬት ውጭ ወደ ሆነ ዓለም እንድንሄድ፣ ከዓለም እንድንገናኝ ... ወዘተ አድርገውናል፡፡ 

እኒህ ሰዎች እንዲህ ካደረጉ እኛስ? እናም ብዙዎቻችን ሰው ማለት ምን ማለት እንደሆነ አለማወቃችን አንዱ ገደባችን ስለሆነ ይህንን ብንረዳ ለተግባር ያነሳሳናል ብየ አስባለሁ፡፡

2. አንተ ማን እንደሆንክ ብትረዳስ?

ታውቃለህ እያንዳንዱ ሰው ወደ ዚህ ምድር ሲመጣ ለተለያየ መክሊት ነው፡፡ እያንዳንዱ በዚህ ምድ ላይ ያለ ሰው በተፈጥሮ ማለትም በዘረ-መልህቅ አወቃቀሩ የተለያየ ነው፡፡ 

እንዲሁም ሰው በዚህ ምድር ላይ ሲኖር ያደገበት ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ እና አካበባቢ በመለያየቱ የተለያየ ማንነት ይኖረዋል፡፡ 

በመሆኑም አንተ መክሊትህን እና ማንነትህን ለማወቅ ያደክበት ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ እና አካበባቢ መሰረት በማድረግ የራስህን መክሊት እና ማንነት ልትረዳ ያስፈልጋል፡፡

ዝንባሌህ ምንድን ነው፣ ችሎታህስ፣ ደካማ ጎንስ ... ወዘተ በሚገባ መረዳት እና ዝንባሌ እና ችሎታ ላይ ዘወትር በየቀኑ መስራት እና የበለጠ ማዳበር ያስፈልጋል፡፡ 

ብዙ ሰው ድክመቱን ለማረም ሲታትር ይውላል፡፡ ይህ ስሀተት ነው ይልቁንም ዝንባሌ እና ጥንካሬያችን ላይ ስናተኩር ነው እጅግ ትልቅ ውጤት እና አዳዲስ ነገሮችን ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የምናበረክተው፡፡ 

ድክመትን ለማሻሻል መሞከር ማለት ዓሳን ውሃ ውስጥ እንዲዋኝ በማሰልጠን ፋንታ ዛፍ ላይ እንዲወጣ እንደማሰልጠን ነው፡፡

ራስህን ለማወቅ ባደረከው ጥረት ሄደት ልማድህ፣ ምግባርህ፣ ክህሎትህ፣ ስዕብናህ፣ ዕምነትህ፣ አመለካከትህ እና ሌሎች የማንነት ዘርፎችህ ምን እንደሚመስሉ ትረዳለህ ብየ አስባለሁ፡፡  

3.      የምታሻሽላቸውን የህይወት እና የማንነት ዘርፎችህን ብተለይስ?

ማንኛውም ሰው ሲኖር ሊተዋቸው የማይችላቸው ልዩ ልዩ የህይወት እና የማንነት ዘርፎች አሉት፡፡ 

ዋና ዋና የህይወት ዘርፎች ማንፈሳዊነት፣ ጤና፣ ቤተሰብ፣ ገንዘብ፣ ግንኙነት፣ ትምህርት የመሳሰሉት ናቸው፡፡ 

እንዲሁም ዋና ዋና የማንነት ዘርፎቹ ልማድ፣ ምግባር፣ እምነት፣ ባህሪ፣ ስሜት የመሳሰሉት ናቸው፡፡

ይሁን እንጅ ብዙዎቻችን በህፃንነታችን ሌሎች ሲያደርጉ እንዳየነው እና እንዲሁ እንደመጡልን እንኖራቸዋለን እንጅ ሆነ ብለን አስበን ኣሻለናቸው አናውቅም፡፡ 

እናም አንተም ከላይ የተጠቀሱትን ሁሉንም ወይም ላንተ አንገብጋቢ እና ወሳኝ የሆኑትን መምረጥ ትችላለህ፡፡ 

በመቀጠልም የመረጥካቸውን የህይወት እና የማንነት ዘርፎች ግብ ቀርጾ፣ ዕቅድ አውጥቶ እና የየቀን መርሃ-ግብር ነድፎ ማሻሻል ያስፈልጋል፡፡ 

ልብ በል ሰው ምንም ይሁን ምንም ይስራ የመጨራሻ ግቡ በእነዚህ የህይወት እና የማንነት ዘርፎች ደስተኛ እና ውጤታማ ሆኖ መኖር ነው፡፡ 

በእነዚህ የህይወት እና የማንነት ዘርፎች ደስተኛ እና ውጤታማ ለመሆን ደግሞ እንደመጡለት መኖር ሳይሆን በተጠቀሰው መልኩ በየጊዜው ማሻሻል አለበት፡፡

4. የህይወት ዝንባሌህን (ዓላማህን ራዕይህን ወይም ህልምህን) ብታገኘው ወይም ብትፈጥረውስ?

ራዕይ የሌለው ትውልድ ይጠፋል ...

ሰው እንደተለመደው ከላይ በተጠቀሱት የህይወት እና የማንነት ዘርፎች አማካኝ የሆኑ ውጤቶችን እያገኘ መኖር ይችላል፡፡ 

ከፈለገም ከእነዚህ የህይወት እና የማንነት ዘርፎች ባሻገር በህይወቱ የሚያስደስተውን (ዝንባሌውን) እና በቀላሉ የሚሰራውን (ችሎታውን) ግን ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለብዙ ሽዎች፣ ሚሊየኖች እና ቢሊየኖች የሚሆን ስራን ወይም አሻራን ጥሎ ማለፍም ይችላል፡፡ 

ይህም ዓላማ፣ ራዕይ ወይም ህልም ይባላል (እኔ ዓላማ የሚለውን ቃል እመርጣለሁ)፡፡ ራዕይ፣ ዓላማ ወይም ህልም የምርጫ ጉዳይ እንጅ ማንም ሰው ፍላጎቱ ከሆነ ሊኖረው የሚቻል እና ብዙዎች ሲሰሩት የምናየው ነው፡፡

በመሆኑም አንተስ ትልቁን የህይወት ራዕይ፣ ዓላማ ወይም ህልም ለምን ከውስጥህ ፈልገህ አታገኝም ወይም አትፈጥረውም?

ስለምንስ በዚህ ራዕይህ ላይ በማተኮር ሃሳብ፣ ዕወቀት፣ ጥበብ እና ክህሎትህን ለቀናት፣ ለወራት፣ ለዓመታትም ቢሆን አታዳብርም? ምክንቱም ይህንን ባታደርግም ኖርክ ነው፤ ትኖራለህምና፡፡  

ይህንን ሃሳብ፣ ዕወቀት፣ ጥበብ እና ክህሎትህ ከየት እና እንዴት አገኛለሁ እንዳትለኝ፤ በዚህ የሚፈለገው ዓይነት መረጃ እስከሚፈለገው ጥልቀት ድረስ በነፃ በሚገኝበት ሰዓት ፈጽሞ ይህ በቂ ምክንያት አይሆንም፡፡ 

ልብ ካልክ ከየት አገኛለሁ ላልከው በትንሿ እጅ ሞባይልህ ሳይቀር ይዘኸው እየዞርክ ነው፡፡ እንዴት አገኛለሁ ላልከው ባለህ እረፍት ወይም ትርፍ ጊዜ ሁሉ ማንበብ እና የራስህን የህይወት ተሞክሮ ቆም ብሎ ማየት ነው፡፡

o   ይህንን በእውኑ አሁን ከዚህ ቅጽበት ጀምረህ ማድረግ መጀመር አትችልም?

o   ይህንን አድርገህ በእውኑ ስኬታማ አለመሆንስ ትችላለህ?

o   እሽ ይህን ለማድረግ ገንዘብ፣ ስልጣን፣ የበለገች ሃገር፣ ትልቅ ከተማ ... ወዘተ ያስፈልጋልን?

o   በአንተ ሃገር፣ ቢሮ ... እንደዚህ በትልቅ ራዕይ መልኩ ሊሰራ የሚችል ነገር የለም?

o   የህንን እንዳታደርግ በተጨባጭ እንዳታስብ አእምሮህን የዘጋህ እና ወደ ተግባር እንዳትገባ እጅህን የያዘህ አለ?

o   ምንም ... ስለዚህ የእውነት ችግርህ ገንዘብ፣ የስልጣን፣ የበለገች ሃገር ... ወዘተ ሆን የራስህ መሆኑን የተረዳህ ይመስለኛል፡፡

5. ስለ ራዕይህ፣ ዓላማህ ወይም ህልምህ ያለህን ሃሳብ፣ ዕወቀት፣ ጥበብ እና ክህሎትህን ብትቀምረውስ?

ልብ በል ስላንድ ነገር የፈለገውን ያህል የተሰበሰበ መረጃ ሊኖርህ ይችላል፡፡ ይህም እውቀት ይባላል፡፡ እውቀት ብቻውን ግን ወደፊት ሊጠቅም የሚችል እሴት እንጅ አሁን በተግባር የሚውል ሃብት አይደለም፡፡ 

በመሆኑም ከላይ ዓላማህ፣ ራዕይህ ወይም ህልምህ ላይ በማተኮር ለቀናት፣ ለወራት እንዲሁም ለዓመታት ያከማቸሃቸውን እና የቀመርካቸውን ሃሳቦች፣ ዕወቀቶች፣ ጥበቦች እና ክህሎቶች በመጀመሪያ ራስህ በተግባር በህይወትህ በመኖር ውጤታማነቱን አረጋግጠው፡፡ 

በመቀጠልም የቀመርካቸውን እና በተግባር በህይወትህ ኖረሃቸው የሰሩልህን ሃሳቦች፣ ዕወቀቶች፣ ጥበቦች እና ክህሎቶች ወደ መሬት ወርደው የሌሎች ሰዎችን ችግር የሚቀርበትን ወይም የሰዎችን ህይወት የሚያቃልሉበትን መንገድ መቀመር ያስፈልጋል፡፡

6. እነዚህን ሃሳቦች ለሰዎች የምታካፍልበት መንገድ ብትፈጥርስ?

የሰው ልጅ ስለፈለገው ስለማንኛውም ነገር የሚችለውን ያህል እውቀት፣ ሃሳብ፣ ዕወቀት፣ ጥበብ እና ክህሎት ካዳበረ እና ከቀመረ በኋላ በመጀመሪያ የቀመረውን መንገድ በመከተል ራሱን ውጤታማ ያደርጋል፡፡ 

ደስ የሚለው ነገር አንተን ውጤታማ እና ስኬታማ ያደረገህ መንገድ ሌሎች ብዙ ሰዎችን ውጤታማ እና ስኬታማ ማድረግ መቻሉ ነው፡፡ 

ይህም ብቻ አይደለም አንተን ያስደሰተህን ነገር ሌሎች ብዙ ሰዎች ይደሰቱበታል፣ እንዴት እንደሚያገኙት እና እንደሚያሳኩትም አስተማማኝ መንገድ ይፈልጋሉ፡፡ 

በዚህም መካከል ፈላጊ እና ተፈላጊ (ማለትም ገዥ እና ሻጭ) በሚገርም ድንቅ ዓላማ (ገበያ) ላይ ተገናኙ ማለት አይደለምን?

ስለሆነም ይህንን አንተን ውጤታማ ያደረገህን ራስህ አንተ በፈለከው ነገር ላይ የቀመርከውን ሃሳብ፣ ዕወቀት፣ ጥበብ እና ክህሎት የዘመኑን ቴክኖሎጂ ተጠቅመህ ለሌሎች የምታደርስበትን መንገድ በመፍጠር ሌሎችን እንዳንተ ውጤታማ እና ስኬታማ እንዲሆኑ ብትረዳቸውስ?

ይህ ማለት ምን ማለት ነው?

እንግዲህ ሁላችንም እንደምናውቀው እና እንደምንስማማበት ሰዎችን ለጥሩ ዓላማ የሚረዳ ማንኛውም ሰው የፈለገውን ነገር /ገንዘብ፣ ክብር፣ ስልጣንወዘተ/ አለማግነት አይችልም፡፡ 

እንዲያውም ሰው የፈለገውን ነገር በፈለገው መጠን የማግኘት መሰረቱ እና ገደቡ ሰዎችን የሚያገለግልበት ጥራት እና ብቃት ነው፡፡ 

ትልቅ ሰው መሆን የሚወድ ቢኖር ሰዎችን ያገልግል የሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ እና ሳይንሳዊ ጽንሰ-ሃሳብ መሰረትም ይህ ነው፡፡

ልብ በል ይህ ከላይ የተገለጸውን ሂደት የህይወት ስኬት መንገድ አድርገህ ልትወስደው ትችላለህ፡፡ ነገር ግን ይህን መንገድ በህይወት መተግበር እና መኖር እንደዚህ እንደመፃፉ እና እንደማንበቡ ቀላል አይደለም፡፡ 

በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ በሶስተኛ ... ሙከራህ ባይሳካልህ አትደነቅ፣ ተስፋም አትቁረጥ፡፡ ይልቁንም አሁንም ካለህበት ተነስተህ፣ የውድቀት አቧራህን አራግፈህ ቀጥል፡፡ 

ትልቅ የስኬት ምስጢር ያለው እየወደቁም ቢሆን አሁንም ደግሞ መሞከር ላይ ነው፡፡ ለዚህ አስረጅ የሚሆንልኝ የአንድ የዓለማችን ታላቅ ሰው ሃሳብ እንደሚከተለው ላቅርብልህ፡-

ቶማስ ኤድሰን የኤሌክትሪክን ሃይል ወደ ብርሃን ሃይል የሚቀይር አምፖል ለመስራት ከአንድ ሽ ጊዜ በላይ ሞክሮ ነው ያገኘው:: 

በዚህም የተደነቀ አንድ ጋዜጠኛ ይህንን ሁሉ አንድ ሽ ውድቀት ታግሰህ እንዴት ለዚህ ስኬት በቃህ ሲል ጠየቀው ሲጠይቀው፡፡ 

ቶማስ ኤድሰን ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው? እኔ አንድ ሽ ጊዜ አልወደኩም፣ ይልቁንም አንድ ሽ የኤሌክትሪክ አምፖል መስራት የመይቻልባቸውን መንገዶች ተረዳሁ እንጅ ብሎ መለሰት:: 

ይህ መልስ እየወደቅንም ቢሆን ተነስተን አሁንም መሞከር እንዳለብን የሚያስረዳን ህያው ምስክር ነው፡፡ 

ይህንን ድንቅ የቶማስ ኤድሰን አባባል ልናሳካው የፈለግነውን ነገር እየሞከርን እያለ ውድቀት በጎበኘን ቅጽበት ሁሉ መርህ እና ስንቅ ልናደረገው ይገባል፡፡ 

እንግዲህ ከላይ ከ1-6 የተጠቀሱትን መንገዶች በህይወት ለመተግበርም ዋናው ምስጢር ያላሰለሰ ጥረትን (በትንሽ ጀምሮ እየጨመሩ መሄድ፣ ሲወድቁ አሁንም ደግሞ ካሉበት መነሳት) የውስጥ መነሳሳትን (የሚፈልጉትን ነገር ለራስ በተደጋጋሚ በየቅጽበቱ እና በየዕለቱ ማስታወስ እንዲሁም የፈለግነውን ነገር ለማሳካት ለራስ ቃል መግባት) እና ቁርጠኝነትን (በየቅጽበቱ ከምትፈልገው ነገር ይልቅ የተሻሉ የሚመስሉ እና የሚያማልሉ ማናቸውንም አማራጮች ያለምንም ድርድር ውድቅ ማድረግ) የየዕለት ልምምድ ማድረግ ነው፡፡ 

ያላሰለሰ ጥረትህ ልማድን ያጎናጽፍኃል፡፡ የስውስጥ መነሳሳትኅ ምንም ዓይነት ፈተና ቢገጥምህ ከፈለከው ነገር ለቅጽበትም ወደ ኋላ እንዳትል ጉልበት ይሆንሃል እንዲሁም ቁርጠኝነትኅ ካሰብከው ነገር ውጭ ሌላ ምንም እንዳትሻ እና የከፈለከውን ነገር ማግኘት ሞት ወይም ሽረት የሚል አቋም እንዲኖርህ በማደረግ እኒህ ሶስቱ ነገሮች በህወትህ ስኬትን ያጎናጽፉሃልና ማንኛውንም ነገር ማሳካት በፈለክ ጊዜ ሁሉ ትኩረትህን ከእነሱ አትንቀል፡፡

 

 አንዴ ቆም ብለህ አስብ፡-

ዛሬ አሁንኑ ልትተገብረው የምትችለው ከዚህ ጽሁፍ የተማርከው አንድሁለትሶስትወዘተ ሃሳብ ምንድን ነው?  

ስላንድ ነገር ብዙ መረጃ መኖር ዕውቀት ነው፤ መረጃውን በተግባር መጠቀም ደግሞ ጥበብ ነው እና አሁንኑ በተግባር ግባ!

 

አስተያየት ተጨማሪ ሃሳብ እንዲሁም ጥያቄ ካላችሁ በዚሁ ድህረ-ገጽ ፃፉልን!