መነሻ ሃሳብ

ብዙዎቻችን ለህይወታችን በእውኑ ለሚያስፈልጉን ነገሮች እና የህይወት ዘርፎቻችን በቂ ትኩረት እና ጊዜ አንሰጥም፡፡ ከሰጠንም ትንሽ የቀን ውሎ ትኩረት እና ጊዜን ብቻ ነው የምንሰጠው፡፡ እርግጥ ነው ሰው በሀይወቱ እና በቀን ውሎው ትኩረቱን እና ጊዜውን የሚሹ በጣም ብዙ ነገሮች እና የህይወት ዘርፎች አሉት፡፡ የሰው ልጅ የህይወት ስኬቱ እነዚህን ለሕይወቱ ወሳኝ የሆኑ የተለያዩ ነገሮች እና የህወት ዘርፎች እንደየሚገባቸው የትኩረት እና ጊዜ መጠን መድቦ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ማስኬድ እና የሚገባውን ውጤት ማስመዝገብ መቻሉ ነው፡፡

የሰው ልጅ በህይወቱ ስኬታማ ለመሆን ከተለመደው ደመ-ነፍሳዊ አኗኗር በመውጣትና ከውጫዊ ጫጫታ ራሱን በማግለል የትኞቹ የህይወት ዘርፎቹ የመጀመሪያና ትልቅ ትኩረት እና ጊዜ እንደሚፈልጉ መወሰን ያስፈልጋል፡፡ ይህን ማድረግ ለማንኛውም እና የትም ደረጃ ላይ ያለ ሰው ዛሬ ከአሁንኑ ጀምሮ የሚቻል ግን ልብ የማንለው ነፃ ስጦታ ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ መንፈሳዊነት፣ ጤና፣ ቤተሰብ፣ ትምህርት፣ ስራና ዓላማ አብዛኛውን ትኩረቴን እና ጊዜየን የመደብኩላቸው ስድስቱ የተመረጡ የህይወት ዘርፎቸ ናቸው፡፡ የእናንተስ? የእናንተን እናንተ በራሳችሁ የህይወት ተጨባጭ ሁኔታ መሰረት መለየት እና አስፈላጊውን ትኩረት እና ጊዜ መመደብ ጊዜ የማትሰጡት የአሁን የቤት ስራችሁ ይሁን፡፡

እንዳለመታደግ ሆኖ ብዙዎቻችን ለህወታችን በእውኑ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን እና የህይወት ዘርፎቻችን እነማን እንደሆኑ አስበናቸው አናውቅም፣ አናውቃቸውም፡፡ በመሆኑም እያንዳንዱ ቅጽበት እና ቀን ያመጣልንን ይህ ነው ለማይባል ነገር፣ የህይወት ዘርፍ፣ ክስተት፣ ድርጊት ሙሉ ትኩረት እና ጊዚያችን በመመደብ ስናሳድድ እና ስንከተል የእኔ የምንለው ህይወት ሳይኖረን ቀናት፣ ሳምንታት፣ ወራት እና ዓመታ ይነጉዳሉ፡፡ የሚገርመው ነገር ህወታችንን በአግባቡ መራንም አልመራንም ህይወት እንዲሁ ታልፋለች፣ ታረጅማለች እንጅ ገና አልተዘጋጃችሁም ብላ እስክንዘጋጅ ለቅጽበት እንኳን ቆም ብላ አትጠብቀንም፡፡ ለዚህም ጊዜ እየበረረ ሳይታጠፍ ክንፉ፣ እኛ በቁማችን ምንድን ነው እንቅልፉ የምትል አንድ የመጀመሪያ ደረጃ (ባልሳሳት 3ኛ ክፍል አማርኛ መጽሐፍ ያነበብኳት ግጥም) ትዝ አለችኝ፡፡

ጅምሮን የሚባል ጸሃፊ፣ አነቃቂ ንግግር አቅራቢ እና አሰልጣኝ እንደሚለው ህይወትህን ራስህ በጥንቃቄ አቅደህ ካላስኬድከው ሌሎች (ኃላፊህ፣ ጓደኛህ፣ ክስተቶችሌሎች ጨምሩበት) ያቅዱልሃል፡፡ ልብ ካልን ሌሎች የእኛን ህይወት አቅደው ወዴት እንደሚወስዱት፣ የት እንደሚያደርሱት እና ምን ያህል ስኬታማ እንደሚያደርጉን እስካሁን ባለው ህይወታችን ያነው ህያው ምስክር ነው፡፡ ለማንኛውም እኔ ያለችኝ ይህችን ያህል ሃሳብ ካቀረብኩ ሳነብ ካገኘሁት የዶ/ር አዱኛ ጓዴ የስኬት ቁልፎችን ከመልካም ስዕብና ጋር እዝናኑ የሚያስተምሩ አጫጭር ዘመን ተሸጋሪ ተረቶች ከተሰኘ የልጆች እና ወጣቶች የትርጉም መጽሐፍ ውስጥ ለወላጆች ብለው የፃፏትን በሚከተለው ስዕል የተገለጸች አንድ ንጽጽራዊ ጽሁፍ ላቅርብላችሁ በሚገባ አንብቡት፡፡


 

አንድ ፕሮፌሰር ተማሪዎችን ሊያስተምር የፕላስቲክ ገንቦ፣ የከረንቡላ ኳስ፣ ጠጠሮች፣ አሸዋ እና የተፈጨ ቡና በስኒ ይዞ ወደ ክፍል ይገባል፡፡ በመቀጠልም ፕሮፌሰሩ የከረንቡላ ኳሶች ወደ ፕላስቲክ ገንቦው በማስገባት ተማሪዎችን ይህ ገንቦ ሙሉ ነው ይላቸዋል፡፡ ተማሪዎችም እርግጠኛ በመሆን አዎ በሚገባ ሞልቷል ይላሉ፡፡ በመቀጠልም ፕሮፌሰሩ ጠጠሮችን ወደ ገንቦው በመቸመር ተማሪዎችን በድጋሚ ይህ ፕላስቲክ ገንቦ ሙሉ ነው ይላቸዋል፡፡ በዚህ ሰዓት ተማሪዎች ግራ ይጋቡ እና ጸጥ ይላሉ፡፡ ፕሮፌሰሩ አሸዋውን እና የተፈጨውን ቡና በየተራ ወደ ገንቦው እየጨመረና ተማሪዎችን እየጠየቀ እና ተማሪዎችም የሚመልሱት ግራ እየገባቸው ዝም እያሉ ሁሉን ወደ ገንቦው ጨምሮ ጨረሰ፡፡ 

በመቀጠልም ሲያደርጉ የቆዩትን ምን ለማስተማር እንደፈለጉ ማብራራት ጀመረ፡፡ አያችሁ ተማሪዎች እኛ ሰዎች ትኩረታችንን እና ጊዚያችንን የሚሹ በጣም ብዙ የህይወት ዘርፎች አሉን፡፡ ይሁን እንጅ ሰው እንደመሆናችን ለያትኛው የህይወት ዘርፍ ምን ያህል ትኩረት እና ጊዜ መስጠት እንዳለብን መወሰን አስፈላጊ ነው፡፡ በእርግጥም ከመቸውም በበለጠ በዚህ ዘመን ትልቁ የሰው ልጅ ችሎታ ደግሞም ፈተና ይህንን ማደረግ ነው፡፡ ምክንያቱም በእያንዳንዱ የህይወት ቅጽበታችን እና ቀናችን ሃሳብ እና ስሜቶቻችንን የሚቆጣጠሩ ብሎም ሙሉ ትኩረት እና ጊዚያችንን የሚበዘብዙ በጣም ብዙ ብልጭልጭና ከላይ ከላይ ሲታዩ አስፈላጊ የሚመስሉ ጠቅሶ ለመጨረስ የሚያዳግቱ ቁሳዊ እና ረቂቅ ነገሮች ተከበናል፡፡  

የታሪኩ ዋና ዋና መልዕክቶች

አንደኛከላይ የተጠቀሱት ቁሶች ውክልና      

እንግዲህ ከላይ እንዳየነው በመጀመሪያ የፕላስቲክ ገንቦው የእኛን ይወት ይወክላል፡፡ የከረንቡላ ኳሱ ደግሞ ወሳኝ የሆኑትን የህይወት ዘርፎቻችንን (እንደየግለሰባዊ የህይወት ሁኔታችን ቢወሰንም መንፈሳዊነት፣ ጤና፣ ትምህር፣ ገንዘብ፣ ስራወዘተ)፡፡ እነዲሁም ጠጠሮች ሌሎች ጠቃሚ ነገር ግን ብዙ ወሳኝ ያልሆኑ ነገሮችን ማለትም ያሉን ቁሳዊ ነገሮች (መኪና፣ ቤት፣ አንዳንድ የቤት ዕቃዎችወዘተ) ይወክላል፡፡ አሸዋው ለህይወታችን አስገዳጅ ያልሆኑ ነገሮችን ማለትም አልኮል መጠጥ፣ ኬክ መመገብወዘተ ሲወክል የተፈጨ ቡና ደግሞ ትኩረት የማንሰጣቸው ትናንሽ የሚመስሉ ነገር ግን ለህይወታችን በጣም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን እንደ ግንኙነት፣ እርዳታ መጠየቅ፣ የመዝናኛ ጊዜወዘተ ይወክላሉ፡፡ 

ሁለተኛየፕላስቲክ ገንቦው በቁሶች አሞላል ቅደም ተከተል መልዕክት

እንግዲህ ከላይ ንጽጽሩን እነዳያችሁት ፕሮፌሰሩ የፕላስቲክ ገንቦውን የሞሉበት ሆን ብለው ከከረንቡላ ኳሱ በመጀመር ቀጥሎ በጠጠሮች፣ በአሸዋው እና በተፈጨ ቡና ነው፡፡ ይህ የፕሮፌሰሩ አሞላል ቅደም ተከተል ራሱን የቻለ መልዕክት አለው፡፡ ፕሮፌሰሩ በመጀመሪያ የፕላስቲክ ገንቦውን በከረንቡላ ኳሱ የሞሉበት ምክንያት ምንጊዜም ቢሆን ወሳኝ ለሆኑ ነገሮች ወይም የህይወት ዘርፎቻችን የቅድሚያ ቅድሚያ መስጠት እንዳለብን ሲነግሩን ነው፡፡ ነገር ግን ዋናው መመለስ ያለበት ጥያቄ ለእኛ የከረንቡላውን ኳሶች የሚወክሉት ወሳኝ ነገሮች ወይም የህወት ዘርፎቻችን ምን ምን ናቸው? በመቀጠልም ፕሮፌሰሩ የፕላስቲክ ገንቦውን በጠጠሮች ሞሏቸው፡፡ ይህም ማለት ምንም እንኳ ቁሳቁስ ነገሮች እንደ መኪና፣ ቤትጠቃሚ ቢሆኑም የወሳኝ ነገሮችን እና የህይወት ዘርፎቻቸንን ያህል ለህይወታችን አስፈላጊ እንዳልሆኑ እና በሁለተኛ ደረጃ ትኩረት እና ጊዜ መስጠት እንዳለብ ሲነግሩን ነው፡፡ እንዲሁም በሶስተኛ ደረጃ አሸዋውን የጨመሩበት መልዕክት ለህይወት አስገዳጅ ያልሆኑ ነገሮችን የመጨመር እና ያለመጨመር የእኛ የመጨረሻ ምርጫችን መሆን እነዳለበት ለማጤቅ ነው፡፡  

በዚህ የፕላስቲክ ገንቦ አሞላል ቅደም ተከተል ላይ ልብ ልንለው የሚገባ አንድ ነገር የተፈጨው ቡና ለአሞላ ምቾት ሲባል በስተመጨረሻ የረተጨመረ ቢሆን ከአስፈላጊነት ቅደም ተከተል አነፃር ግን ምናልበናትም በሁለተኛ ወይም ሶስተኛ ደረጃ የሚመጥን መሆኑን ነው፡፡ ማትም ከሰዎች ጋር ግንኙነት ማድረግ፣ እርዳታ መጠየቅ፣ የመዝናኛ ጊዜ መመደብለህይወት ስኬታችን አስፈላጊ ነገሮች እና የህይወት ዘርፎች ናቸው፡፡

ሶስተኛየፕላስቲክ ገንቦው በቁሶች አሞላል ቅደም ተከተል ሲገለበጥ ያለው መልዕክት

በስተመጨረሻ ፕሮፌሰሩ ያስተላለፉት መልዕክት ይህንን የቁሶች አሞላል ቅደም ተከተል ብንገለብጠው ምን የሚሆን ይመስላችኋል ብለው ቢጠይቁን መልሳችን ምን ይሆን?

ማለትም ለህይወታችን ወሳኝ ከሆኑ ነገሮች እና የህይወት ዘርፎቻችን ይልቅ ወሳኝ ላልሆኑት የቅድሚያ ቅድሚያ እና ብዙ ትኩረት እና ጊዜ እየሰጠን ብኖር ውጤቱ ምን ይሆን ይመስላችኋል? መልሱ ለሁላችንም ግልጽ ነውና አላስፈላጊ ማብራሪያ በመስጠት ውድ ጊዚያችሁን ማባከን አልፈልግም፡፡ እናንተ ግን ለራሳችሁ መልሱን ፃፉት

 

አንዴ ቆም ብለህ አስብ፡--

o አሁንኑ ልትተገብረው የምትችለው ከጽሁፍ የተማርከው አንድ ... ሁለት ... ሶስት ... ወዘተ ሃሳብ ምንድን ነው?  

o ስላንድ ነገር ብዙ መረጃ መኖር ዕውቀት ነው፤ መረጃውን በተግባር መጠቀም ደግሞ ጥበብ ነው!

 

አስተያየት ተጨማሪ ሃሳብ እንዲሁም ጥያቄ ካላችሁ በዚሁ ድህረ-ገጽ ፃፉልን!