የመነሻ ሃሳብ
እኔ እንደሚመስለኝ ብዙዎቻችን ህይወትን የምናይበት መንገድ ቁንጽል አሊያም የተንሻፈፈ ነው፡፡ በእኔ ግንዛቤ ከራሴ ተሞክሮ፣ ከሰዎች እና ካነበብኩት ተነስቸ የሰዎችን የስራ እና የህይወት እይታ በሶስት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡
የመጀመሪያው እና የድሮ እይታ ምንም ገንዘብ ቢያስገኘንም ባያስገኘንም በሆነ አጋጣሚ ወይም ለእኛ ትክክል ነው ብለን ለተሰማራንበት ስራ ሙሉ ህይወታችንን ስንገብርበት እንኖራለን፡፡ ነገር ግን በዚህ ዓለም ውስጥ እየኖርን ተወደደም ተጠላም አሁን ባለው ሁኔታ (ገንዘብ ሁሉንም የህይወት ዘርፋችንን በሚነካበት ጊዜ) ህይወታችንን በመደብንለት ስራ በሰራነው ልክ እና በላይ ገንዘብ ካላገኘንበት ስራው ብቻውን የእውነተኛ እና ዘላቂ ደስታ ሊያመጣልን አይችልም፡፡
በመጀመሪያ ሁላችንም ማወቅ ያለበትን ነገር ቢኖር ለህይወታችን የምንሰራው ማንኛውም ስራ የመጨረሻው ግቡ መሆን ያለበት በስራው እኛ ብቻ ሳይሆን ሌሎችን ብዙ ሰዎች እንዲማሩበት፣ ችግሮቻቸውን እንዲቀርፉበት እና ህይወታቸውን እንዲያቀሉበት በስተመጨረሻም እንዲደሰቱበት ነው:: ይህም ከሆነ ደግሞ የምንሰራው ስራ ወደ ብዙ ሰዎች የሚደርስበትን መንገድ በመፍጠር በስራው ልክ እና በላይ ገንዘብ ማግኘት አስፈላጊ ነው፡፡ አለበለዚ ግን ምንም እንኳን ስራችን ለጊዜውም ቢሆን የወደድነው ቢመስለን የሚገባንን ሳናገኝ በስራችን የመዝለቅ እና በዘላቂነት የመደሰት ዕድላችን ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡
ሁለተኛው እና የብዙዎቻችን የህይወት እይታ ደግሞ ህይወት ማለት ምንም ይሁን ምን ቢያስደስተንም ባያስደስተንም፣ በቀላሉ እና ባጋጣሚ ያገኘነውን ማንኛውም ስራ እየሰራን ብቻ ብዙ ገንዘብ ማግኘት ከቻልን እንደ ስኬታማ ህይወት ብለን እንተረጉመዋለን፡፡ በመሆኑም ሙሉ ህይወታችንን ምን መስራት ያስደስተናል ሳይሆን ምን ስራ ብዙ ገንዘብ የስገኛል የሚለውን ማዕከል በማድረግ ገንዘብ የሚያስገኝ ማንኛውም ስራና አጋጣሚ ስናሳድድ እንኖራለን፡፡ ዳሩ ግን በምንሰራው ስራ ብዙ ገንዘብ ማግኘት ብንችልም ውስጣችን ደስተኛ አለመሆኑን የሆነ ጊዜ እንገነዘባለን፡፡ ምክንያቱም ብዙ ገንዘብ የሰውን ልጅ የእውነተኛ (የውስጥ ደስታ) አያመጣምና፡፡ ይባስም ብሎ ገንዘቡ የተገኘበት መንገድ በትክክል ካልሆነ እና ገንዘቡን ባግባቡ መጠቀም ካልተቻለ የውድቀት እና የቀውስ መንስኤ ሊሆንም ይችላል፡፡
ሶስተኛው እና ወቅቱን የዋጀው የህይወት እይታ ነገር ግን ጥቂቶች ብቻ የሚያንጸባርቁት የሆነው ህይወት ማለት ለእኛ የሚያስደስተንን እና በቀላሉ የምንሰራውን ስራ በመስራት፣ ለሌሎች ብዙ ሰዎች የተሻለ አስተዋጽኦ በማድረግ ለስራችን ተመጣጣኝ ክፍያ በማግኘት ሌሎችን የህይወት ዘርፎችንም ተመጣጣኝ ጊዜ በመስጠት ሚዛኑን የጠበቀ ህይወት መኖር ነው፡፡ በዚህ የህይወት እይታ ውስጥ ደስ የሚለው ነገር እኛ የሚያስደስተንን እና በቀላሉ የምንሰራውን ስራ ስለምንሰራ ምንም ፈተና ቢመጣ ስራውን ልክ ጨዋታ በሚመስል መልኩ በዘላቂነት በጥራት እና በፍጥነት እንሰራዋለን፡፡ በዚህም ብዙዎችን ተጠቃሚ ማድረጋችን አይቀሬ ነው፡፡ ብዙዎችን ተጠቃሚ ካደረግን እና ካገለገልን ደግሞ ባገለገልናቸው ሰዎች ህይወት ልክ የእኛ ይህይወት ዘርፎች ይባዛሉ፡፡
ከምናስበው በላይ ህይወትችንን በቁጥጥራችን ስር ማድረግ እንችላለን፡፡
ነገር ግን ብዙዎቻችን በቀላሉ በጥራት እና በፍጥነት የምንሰራውን እንዲሆም የሚያስደስተንን ነገር ቆም ብለን አጢነነው ስለማናውቅ በእያንዳንዱ ቀን ህይወት እኛን ወደ ፈለገችው አቅጣጭ ትወስደናለች እንጅ እኛ ህይወትን በምንፈልገው ቅጣጫ አንወስዳትም፡፡ ለብዙዎቻችን ህይወት ማለት አንዴ ተዘጋጅታና ያለቀላት ሆና በእጣፈንታ መልኩ የተሰጠችን ስለሚመስለን፡፡ በሆነ አጋጣሚ ሳናገናዝበው በጀመርነው ህይወት ለዓመታት እንዲሁም ለዕድሜ ልካችን በዚያው ህይወት በመሆን ወደ ወዲያኛው እንሄዳለን፡፡ ነገር ግን ከላይ የተባለውን ማድረግ ከቻልን በተጨባጭ ህይወት እኛ ሆነ ብለን በሚመቸን መልኩ የምንፈጥረው እና ወደ ፈለግነው አቅጣጫ የምናስይዘው መሆኑን መረዳት እንችላለንና አሁንኑ ቆም ብለን እናስብበት፡፡
ለማሳያም ህይወታችን ማለት በእያንዳንዷ ቅጽበት እና በየዕለቱ ቀላል በሚመስሉን ግን የህይወት መሰረት በሆኑት በራሳችን ሙሉ ፈቃድ በምንመርጠቸው ምርጫዎች እና በምንወስናቸው ውሳኔዎች የተገነባች ናት፡፡ መቸም ምርጫዎች እና ውሳኔዎች አንዴ ተወስነው ነው የሚመጡት አትለኝም፡፡
እናም ልብ ብለን ከተመለከትን እነዚህን የየዕለት ምርጫዎች እና ውሳኔዎች አስበን መምረጥ እና መወሰን ከቻልን ህይወታችንን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራችን ስር ማድረግ እንችላለን ማለት ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆን ከዶ/ር
አዱኛ ጓዴ የስኬት ቁልፎችን ከመልካም ስዕብና ጋር እያዝናኑ የሚያስተምሩ ዘመን ተሻጋሪ ተረቶች ከሚለው የልጆች መጽሐፍ ሳነብ አንዲት ለወላጆች የተፃፈች ታሪክ ላንሳ፡፡
ደሞም ሰው በዕየለት ተዕለት ህይወቱ ምንም ይስራ ምን የመጨረሻው ግቡ ወሳኝ በሚላቸውየህይወት ዘርፎቹ የተሻለ ስራ በመስራት፣ የተሻለ ውጤት አግኝቶ በእነዚያ የህይወት ዘርፎቹ የሰራቸውን ስራዎች እና ያገኛቸውን ውጤቶች እያጣጣመ መኖር ነው፡፡ ስለሆነም እኒህን የህይወት ዘርፎቹ አሰራር እና ውጤት በየጊዜው ማሻሻልም አንዱ እና ዋናው የህይወቱ ሚዛን ማስጠበቂያ መንገድ ነው፡፡
በመሰረቱ ሰው በተደጋጋሚ ያሰበውን እና ያተኮረበትን ማንኛውንም ነገር ይሆናል፣ ያገኛል፣ ይሰራል፡፡
ልብ ባንለውም የዕለት ተዕለት ህይወታቸን የሚመራው በዚህ ህግ ነው፡፡ ማለትም ደጋግመን ያሰብነውን እና ያተኮርንበትን ነገር ነው እያገኘን እየኖርን ያለነው፡፡ ሰው የዘራውን ያጭዳል ማለትም ይህ ነው፡፡ ለዚህም ልብ ብለን ካየነው እያንዳንዳችን በህይወታችን የሆነው፣ እያገኘን እና እየሰራን ያለነው ሁሉ ህያው ምስክር ነው፡፡ ስለዚህ ትልቁ የሰው ልጅ ጥንቃቄ እና ጥያቄ መሆን ያለበት የቱን በተደጋጋሚ ባስብ እና ባተኩር ይጠቅመኛል ነው፡፡
ሰው በማንኛውም የህይወቱ ቅጽበት ሁለት መንታ መንገዶች (ምርጫዎች) ይጠብቁታል፡፡ እኒህ ምርጫወችም የሰውን ልጅ ህይወት ይገነባሉ ወይም ያፈርሳሉ፡፡ የሰው የህይወት ስኬቱ እና እርካታው የሚወሰነውም እነዚህን ምርጫዎች በሚገባ አስቦ በመወሰን ብቃቱ ነው፡፡ ማንም ሰው በእነዚህ የየቅጽበት የህይወቱን ውሳኔዎች ጥቅም እና ጉዳቱን እንዲሁም ወዴት ሊወስዱት እንደሚችሉ በማሰብ በመወሰን ህይወቱን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ማድረግ የመጀመሪያው እና የተሻለው ምርጫ ነው፡፡
ነገር ግን ከዚህ ተጻራሪ በሆነ መንገድ ከምርጫዎቹ አንዱን እንደመጣለት ወይም በቀላሉ ያገኘውን (ሰፊውን መንገድ) ተከትሎ በመወሰን ህይወቱ እሱን እንድተቆጣጠረው እና ወደ ፈለገችው አቅጣጫ እንድትወስደው መፍቀድ ነው፡፡ በመሆኑም ለብዙዎቻችን ህይወት እኛን ትሰራናለች እንጅ እኛ ህይወትን ስንሰራት አንታይም፡፡ በብዙዎቻችን እየሆነ ያለውም ይህ ነው እና ከዛሬ ጀምሮ ልብ እንበል፡፡
የማጠቃለያ ሃሳቦች
ሰው በህይወቱ ስለህይወት ባለው እይታ መሰረት የየቀን ውሎውን ይወስናል፡፡
በዚህም ስኬታማነቱ እና ስኬታማ አለመሆኑ ከዚህ የህይወት እይታው ይመነጫል
ስለሆነም እናንተ ህይወትን ከተጠቀሱት በየትኛው መንገድ እያያችኋቸው እንደሆን ቆም ብላችሁ ራሳችሁን ገምግሙ፡፡
በምታገኙትም ውጤት መሰረት አስፈላጊ ማስተካከያ ወዲያውኑ አድርጉ እና ውጤቱን እዩት፡፡
ማንኛውም ሰው የሚሆነው፣ የሚያገኘው እና የሚሰራው በተደጋጋሚ የሰበውን እና የተኮረበትን ነው፡፡
ስለዚህ የምናስበውንና የምናተኩርበትን ልብ ብለን እንወስን፡፡
ከሰው ልጅ ትልልቅ ክህሎቶች አንዱ የሚሆነውን መምረጥ እና መወሰን ሲሆን በዚህም ክህሎት ማንኛውም ሰው ህይወቱን በሚፈልገው መንገድ መስርራት ይችላል፡፡
በመጨረሻ ስለሁሉም ነገር ጥበብ፣ ማስተዋል እና ትዕግስት እንዲሰጠን መጠየቅና እንደተሰጠንም ማመን በራሱ ጥበብ ነው፡፡
አንዴ ቆም ብለህ አስብ፡--
o ዛሬ አሁንኑ ልትተገብረው የምትችለው ከዚህ ጽሁፍ የተማርከው አንድ ... ሁለት ... ሶስት ... ወዘተ ሃሳብ ምንድን ነው?
o ስላንድ ነገር ብዙ መረጃ መኖር ዕውቀት ነው፤ መረጃውን በተግባር መጠቀም ደግሞ ጥበብ ነው እና አሁንኑ ዕውቀቱን በተግባር!
አስተያየት፣ ተጨማሪ ሃሳብ እንዲሁም ጥያቄ ካላችሁ በዚሁ ድህረ-ገጽ ፃፉልን!

0 አስተያየቶች