የስኬታማ እና ስኬታማ ያልሆነ ሰው ሁሉም ተመሳሳይ ሰው ቢሆኑም እናም ሁሉም ገደብ-አልባ እምቅ አቅም እና ችሎታ ቢኖራቸውም የሚለያዩት እንደሚከተለው ነው፡፡
ስኬታማው ሰው በመጀመሪያ ማን መሆን፣ ምን ማግኘት እና ምን መስራት እንደሚፈልግ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ በመቀጠልም ያንን መሆን የፈለገውን ማንነት፣ ማግኘት የፈለገውን ነገር እና መስራት የፈለገውን ስራ እስከሚሆነው፣ እስከሚያገኘው እና እስከሚሰራው ድረስ ለብዙ ጊዜ ይሞክራል፣ ቢወድቅም አሁንም ደግሞ ይሞክራል፡፡
ስኬታማ ያልሆነው ሰው ግን በቅድሚያ በህይወቱ ማን መሆን እንደሚፈልግ፣ ምን ማግኘት እንደሚፈግ እና ምን መስራት እንደሚፈልግ አያውቅም፡፡ በመሆኑም በህይወቱ በቋሚነት፣ በዘላቂነት እና በተደጋጋሚ ዋጋ እና ካስፈለገም መስዋዕትነት ሊከፍልለት የሚችለው አንዳች ነገር ስለሌለው በተደጋጋሚ መሞከር የሚለው መመሪያ ለእርሱ አይሰራም፡፡ ይልቁን ህይወት ለእርሱ በድንገት ወደ እርሱ የምትመጣበት እና ወደ ፈለገችው አቅጣጫ ትወስደዋለች፡፡ በመሆኑም ህይወቱ (ውሎው፣ ሳምንቱ፣ ወራቱ፣ ዓመቱ … ሁሉ) ዘፈቀደ እና ያልታቀደ ይሆናል፡፡
ስለሆነም ውድ አንባቢ አንዴ ቆም በልና አስተውል፡፡ አንድ የቤት ስራ የሚሆንህ እና ህይወትህን ወደ ተሻለ እይታ እና አቅጣጫ የሚወስድ ጥያቄ ልጠይቅህ ነው፡፡
አንተ በቅድሚያ በእውኑ በህይወትህ በቋሚነት፣ በዘላቂነት እና በተደጋጋሚ ዋጋ ልትከፍልለት ካስፈለገም መስዋዕትነት ልትከፍልለት የምትችለው መሆን የምትፈልገው፣ ማግኘት የምትፈልገው እና መስራት የምትፈልገው በግልጽ ያስቀመጥከው ነገር አለህን?
ካለህስ ምን ያህል ጊዜ ሞክረሃል? ከሌለህስ ማን ለመሆን፣ ምን ለማግኘት እና ምን ለመስራት ነው እዚህ ምድር ላይ ያለኸው?
ደስ የሚለው ነገር ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ሊረፍድ ይችላል እንጅ የትኛውም ዕድሜ እና የህይወት ሁኔታ ላይ ላለ ሰው አይመሽም፡፡ እናም መልስህ ምንም ይህ ነው የምለው ልሆነው ያሰብኩት ማንነት፣ ላገኘው የፈለኩት ግልጽ ነገር እና ልሰራው ያሰብኩት ስራ የለኝም ካልክ መልካም:: ይሄው ዛሬ በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ ማሰብ እንድትጀምር እድል አገኘህ ማለት ነው:: ስለሆነም አሁን ካለህበት ማንኛውም የህይወት ሁኔታ ተነስ እና ከዛሬ አሁን ጀምሮ ለሚቀጥሉት ሶስት ቀናት እኒህን ሶስት ነገሮች አስበህ ወስን፡፡
በቀሪው ህወትህ በዚህ ምድር ላይ ባለህበት ዘመናት ማን መሆን፣ ምን ማግኘት እና ምን መስራት ነው የምትፈልገው?
እያንዳንዳችን ህይወታችንን መቀየር ለፈለግን ሰዎች በሙሉ እኒዚህ ሶስት ነገሮች ግልጽ መሆን የህይወት መመሪያዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም እንደ ቤት ስራ ውሰዳቸው፡፡ እኒህን ሶስት ነገሮች በግልጽ ባስቀመጥክ ቅጽበት በቀጣይ ምን ማድረግ እንዳለብህ በግልጽ ይታይኻል፡፡
በህይወትህ ማን መሆን፣ ምን ማግኘት እና ምን መስራት እንደምትፈልግ ከወሰንክ ቅጽበት ጀምሮ ህወትህ ካለበት ውስብስብ እና ዘፈቀደ ሁኔታ ወደ መደበኛ እና የተደራጀ ማንነት ይኖሆናል:: እንዲሁም በእያንዳንዱ ዕለትና ቅጽበት የሚያስበውንና የሚሰራውን የሚያውቅ ትሆናለህ፡፡ በመሆኑም መሆን፣ ማግኘትና መስራት ከምትፈገው ውጭ የሆነን ማንኛውም ነገር ጊዜ እና ትኩረትህን ለማጥፋት አትሻም፡፡
በህይወቱ ማን መሆን፣ ማን ማግኘት እና ምን መስራት እንደሚፈልግ ያልወሰነ እና ያላወቀ ሰው መዳረሻውን ሳውቅ የሚያበርን አውሮፕላን አብራሪ ይመስላል፡፡ መዳረሻውን የማያውቅ አብራሪ የት ሊደርስ እንደሚችል እና ምን ሊገጥመው እንደሚችል አስቡት፡፡ እኛ በህይወታችን ማን መሆን እና ምን ማግኘት እደምንፈልግ እንዲሁም ምን መስራት እንደምንፈልግ ያልወሰንን እና ያላወቅን ሰዎች ህወት እንዲሁ ወደ ፈለገችው ትወስደናለች፡፡
እኔ በበኩሌ በህይወቴ መሆን፣ ማግኘትና መስራት የምፈልገውን በጥንቃቄ አስቤ ከወሰንኩ ጀምሮ በአብዛኛው ጊዜዬ የማስበውና የምሰራው ሁሉ በጥንቃቄ አስቤ ከወሰንኩት ጋር የሚዛመድ እና ወደፈለኩት የሚወስደኝ ተግባራት ላይ ቀኔን እንድውል ረድቶኛል፡፡ በመሆኑም በማልፈልገው ነገር ላይ ጊዜየንና ትኩረቴን እንዳላባክን ረድቶኛል:: ለእኔ ከሰራ ለእናንተም ይሰራል እና በድጋሚ ለማሳሰብ አሁንኑ ከዛሬ ጀምሮ አስቡበት፡፡
አንዴ ቆም ብለህ አስብ፡--
o ዛሬ አሁንኑ ልትተገብረው የምትችለው ከዚህ ጽሁፍ የተማርከው አንድ ... ሁለት ... ሶስት ... ወዘተ ሃሳብ ምንድን ነው?
o ስላንድ ነገር ብዙ መረጃ መኖር ዕውቀት ነው፤ መረጃውን በተግባር መጠቀም ደግሞ ጥበብ ነው እና አሁንኑ ዕውቀቱን በተግባር!
አስተያየት፣ ተጨማሪ ሃሳብ እንዲሁም ጥያቄ ካላችሁ በዚሁ ድህረ-ገጽ ፃፉልን!
መልካም ዕለተ ሰንበት!
0 አስተያየቶች