የመነሻ ሃሳብ
እኛ የሰው ልጆች ሃይል፣ ብርታት እና ፈጠራ ከመቸውም በላይ በከባድ ጊዜ እና ሁኔታ ከፈጣሪያችን ይቸሩናል:: ለምሳሌ ብዙዎቻችን በከፍተኛ ሃይልና ብርታት የምንሮጠው ጠላት ሊገድለን ሲከተለን ነው ወይስ ለጤናችን ብለን የሩጫ ልምምድ በምናደርግበት ጊዜ ነው? መልሱ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ማለት ምን ማለት ነው? ከፊታችን የተጋረጠብንን ፈተና ልብ እና ሆን ብለን ለበለጠ ሃይል፣ ብርታት፣ ፈጠራ ማግኛ ብንጠቀመውስ?
በቀላሉ እና በሰላሙ ጊዜ እና ሁኔታ የምንኖረው በቀላል እና በሰላም ስለሆነ የተለየ ሃይል፣ ብርታት እና ፈጠራን እንድንጠቀም አያስገድደንም፡፡ ይልቁንም የተለመደ እና ያልሞቀ እና ያልቀዘቀዘ ኑሮን እንኖራለን፡፡ ደግሞም ፈተና የሌለበት ህይወት ቅመም እንደሌለው አልጫ ወጥ ነው ይባል የለም! ይህ እውነት ነው፤ እስኪ በህይወታችንን ዕለት ተዕለት ለማሳካት የምንወጣ የምንወርድላቸውና የምንጓጓላቸው ስራዎች፣ ውጤቶች፣ ክስተቶች ባይኖሩ ህይወታችን ምን ይመስል እንደነበር እናስብ፡፡
ስኬታማ ሰው በፈተና ጊዜ
በሰላም ጊዜ ማንም ሰው በሰላም እና ተረጋግቶ ይኖራል፡፡ ስኬታማ የሆነ እና ስኬታማ ያልሆነ ሰው ልየነቱ የሚገለጠው በፈተናዎች ጊዜ ነው፡፡ ብዙዎቻችን በከባዱ ጊዜ እና ሁኔታ ያለንን ሃይል፣ ብርታት እና ፈጠራ ከመቸውም በላይ በማጣት ተስፋ ስንቆርጥ ጥቂት ስኬታማ ሰዎች ደግሞ በተቃራኒው ከመቸውም በላይ የከፍተኛ ሃይል፣ ብርታት እና ፈጠራ ባለቤት ይሆናሉ፡፡ በዚያን ጊዜም የብዙዎቻችን መፍትሄ ሆነው ይገኛሉ፤ ብዞዎቻችንንም ከአደጋ ይታደጉናል፡፡ ለዚህም ትልቁ ምስጢር ከውስጥ ወደ ውጭ የመኖር ጥበባቸው ነው፡፡ እኛ ልንሆን የፈለግነውን ለመሆን፣ ለማግኘት እና ለመስራት ከራሳችን ውጭ ባለ ነገር ላይ የሚወሰን ሳይሆን እኛ በህይወት እስካለን ድረስ የውጩ ሁኔታ ምንም ይሆን ምን እስከመጨረሻው በዓላማችን ጸንተን በእያንዳንዱ ቀን ወደ ዚያ ወደ ፈለግነው ነገር የምንቀርብበትን መንገድ ማሰብ፣ መቀየስ፣ መከተል እና መሆንን ልምምድ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም የእኛ የህይወት ስኬት መጨረሻው ለብዙ ሰዎች የህይወት ስኬት መንገድ ስለሆነ::
ነገሮች በከብዱ ጊዜም እንኳን እኛ የፈለግነውን ለመሆን፣ ለማግኘት እና ለመስራት ከመቸውም በላይ የበለጠ አስፈላጊ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም ጠንካራ እና አንገብጋቢ የስኬታማነት ፍላጎት ያለው ሰው ሀገር ሲረበሽና ሰላም ሲጠፋ፣ መንግስት ሲፈርስ፣ ሰዎች እንደፈለገው ሳይሆኑለት እና ገንዘብ ሲያጥረው፣ ሰዎች አድሎ ቢያደርጉበት … ወዘተ ብቻ አሉ የተባሉ የምድር ፈተናዎች ቢፈራረቁበትም እነዚህን ፈተናዎች የበለጠ ወደ ስኬት ለመገስገስ እንደ ቀስቃሽ ይጠቀማቸዋል፡፡ ምክንያቱም የእርሱ የህይወት ስኬት የእርሱ ብቻ ሳይሆን ለብዙዎች ህይወት እንደሚያስፈልግ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡
እኛም አሁን በዚህ ዓለም እንዲሁም በምንኖርበት ሃገር እና ሃገረ-መንግስት መናጋት፣ ሰላም መጥፋት ተስፋ መቁርጥ ሳይሆን የበለጠ ሃይል፣ ብርታት እና ፈጠራ የምንላበስበትን መንገድ ማሰብ እና መለማመድ ምርጫችን ማድረግ እንችላለን፡፡ በፈተና ጊዜ የጸና ምስጉን ነው ያለው ልበ-አምላክ ዳዊት ለዚህም ነው፡፡ ዓለም እንዲሁም ሃገራችን ያጣችው በዚህ መንገድ የሚያስብ እና የሚኖር እንጅ የውድቀትን፣ የተስፋ መቁረጥን ... ህይወት የሚመሩ ብዙ ሚሊዮን እና ቢሊዮን ዜጎች አሏት፡፡
ሰዎች ራሳቸውን አስቀድመው በሚንቀሳቀሱበት
እና እኛን በአድሎ በሚያገሉን ጊዜም ሳይቀር እኛ የበለጠ ለብዙዎች ለጠላቶቻችንም ጨምሮ የሚሆን ስራን መስራት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም
ሰው የዘራውን ያጭዳል ነውና ያኔ በዘራነው ዘር መሰረት የምናጭደው የሚያወጣ ዘር ይሆናል፡፡ ይህ አባባል ሃሳባዊ ብቻ አይደለም
ልብ ካልነው በእያንዳንዱ ቀን በህይወት የምንኖረው ተጨባጭ እውነታ ነው፡፡
ስኬት እና የነገሮች መለዋወጥ
መታወቅ ያለበት ነገር ምን ጊዜም ቢሆን በተለይም በዚህ ዘመን ነገሮች ተለዋዋጭ ናቸው፡፡ አንዴ ለበጎ ሌላ ጊዜ ለጥፋት ይለወጣሉ፡፡ ሃገር ታድጋለች፣ ሃገር ጦርነት ውስጥ ትገባለች፣ መንግስት ህዝብን ያሻግራል፣ መንግስት ህዝብን ይጨቁናል፡፡ ታዲያ ለእኛ ህይወት ስኬት ወሳኙ የነገሮች መለዋወጥ ሳይሆን ለለውጦች ያለን አመለካከት እና ምላሽ ነው፡፡ ይህንን ለመረዳት ኮቪድ 19 በሽታ ወረርሽኝን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፡፡
በታህሳስ ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ የተከሰተው የኮሮና ወይም ኮቪድ 19 በሽታ ወረርሽኝን አስቸጋሪ የህይወት ሁኔታ ነው፡፡ በእርግጠኝነት ብዙዎቻችን ራሴን ጨምሮ በዚያ የኮረና ጊዜ አለቀልን ብሎ ተስፋ ያልቆረጠ አልነበረም፡፡ ይህ የኮሮና በሽታ ወረርሽኝ ለብዙው የዓለም ህዝብ ቀውስ፣ ትርምስ እና ሞት በመፍጠር የብዙ ሰዎች ህይወት መጥፋት እና የንግድ መክሰር ሲያስከትል ለጥቂት ሰዎች የህይወት ስኬት እና የንግድ ትርፍ ማግኛ እድሎችን አስገኝቷል።
ይህ ለብዙዎች ሞት እና ክሳራ ለጥቂቶች ደግሞ ትርፍ እንዴት እና ለምን ሆነ?
ጥቂት ስኬታማ ሰዎች ያኔ በወረርሽኙ ተረብሽው እና ተስፋ ቆርጠው እንደ ብዙዎቻችን
ቁጭ ብለው የሞት ቀናቸውን ከመቁጠር ይልቅ ልዩ ሃይላቸውን፣ ብርታታቸውን እና ፈጠራቸውን ተጠቅመው የበለጠ ወደ ውስጣቸው በመመልከት
በዚህ ወረርሽኝ ለተጨነቀው ቢሊዮን ህዝብ ምን ቢያደርጉ እንደሚሻል በየዘርፉ ቁጭ ብለው በማሰብ እና አዳዲስ የአገልግሎት እና ምርት
ማቅረቢያ መንገዶችን፣ መከላከያዎችን፣ ማስታገሻዎችን፣ መድሃኒቶችን … ወዘተ በመፍጠር እንድም ብዙ ቢሊዮን ህዝቦችን ከጭንቀት፣
ከሞት ታድገዋል፤ አንድም የግል ህይወታቸውን ስኬት ግብ መትተዋል፡፡
የኮሮና ወይም ኮቪድ-19 በሽታ ወረርሽኝ ወደ ሁላችንም
እዕምሮ በተመሳሳይ ሁኔታ ቢመጣም
የእያንዳንዳችን አዕምሮ ለኮሮና ወይም ኮቪድ-19 በሽታ ወረርሽኝ ባለው
አመለከከት፣ ግምት፣ ውሳኔ እና በምንወስደው እርምጃ መሰረት ውጤታችንን አግኝተናል፡፡ በእለት ከእለት፣ ከቀላል እስከ ከባድ ሁኔታዎች በተመሳሳይ ሁኔታ በህወታችን
በመከሰት አዕምሯችን ለክስተቱ አስፈላጊውን አመለካከት በመፍጠር እና አመለካከቱ የሚመጥነውን ስሜት በመላበስ፣ ውሳኔ በመወሰን
እርምጃ በመውሰድ ውጤቱን እናጭዳለን፡፡
ዛሬም ቢሆን ብዙዎቻችን በሃገራችን ሁኔታ ተስፋ ቆርጠን ይሆናል፡፡ ነገር ግን ሃገራችን ካለችበት ቀውስ የሚያወጣት እና የሚያድናት ተስፋ ቆርጠን በህብረት ሆነን በመቆዘም እና ሃዘናችንን በመግለጽ ሳይሆን እንደ ግለሰብ ወደ ውስጣችን በመመልከት እና እንደ ቡድን ደግሞ የተሸሉ ሃሳቦች በማሰባሰብ እና ስልት በመንደፍ በመስራት ነው፡፡ ይህ ምርጫ ለብዙዎቻቸን ላይዋጥልን ይችላል፡፡ ነገር ግን እየመረረንም ቢሆን ልንውጠው የሚገባው ሃቅ ነው፡፡ አለበለዚያ ራዕይ የሌለው ህዝብ ይጠፋል የሚለው አምላካዊ ቃል መፈጸሚያ እንዳንሆን እናስብበት፡፡
የሰው ልጅ የህይወቱ ስኬት ከፈተና በስተጀርባ የተደበቀ ነው፡፡ ስለሆነም ፈተናን እንደ ህይወት ማደጊያ መሰላል እንጅ እንደ ገደብ መቁጠራችንን ማቆም አለብን፡፡ ደግሞስ የፈጠራዎች ሁሉ እናት ፈተና ወይም ችግር ነው ይባል የለምን፡፡
እናም ሰው በህይወቱ ስኬታማ የሚሆነው በህይወቱ በጣም ፈታኝ የህይወት ፈተናዎች በበዙበት ጊዜ ነው፡፡ ምክንያቱም ከፈተናዎች በላይ በመሆን ፈተናዎችን ለመቋቋም እና ለፈተናው መፍትሄ በመፈለግ ሂደት አንድ ትልቅ ለፈተናዎች ሁሉ መፍትሄዎችን የሚያመጣ ጠንካራ ማንነት የሚፈጠረው በዚህ አጋጣሚ ነው፡፡
እያንዳንዳችን ስለጤናችን ተግተን በአግባቡ ወደ አምላካችን የምንጸልየው ጤነኛ በሆንን ጊዜ ነው ወይስ በታመምን ጊዜ?
የተሰማራንበትን ስራ በአግባቡ ተግተን የምንሰራው ከቀጣሪ ድርጅቶቻችን ማስጠንቀቂያ በተሰጠን ጊዜ ነው ወይስ በማንኛውም መደበኛ ጊዜ?
ተማሪ ያለ የሌለ ሃይሉን ተጠቅሞ የሚያጠናው ፈተና በደረሰ ጊዜ ወይስ በመደበኛ ጊዜ?
ሌላው ቀርቶ የምር ያለ የሌለ ሃይላችንን ተጠቅመን የምንሮጠው ለጤናችን ብለን ስንሮጥ ወይስ ለህይወታችን ፈታኝ የሆነ አደጋ በተደቀነብን ቅጽበጽ … ወዘተ?
እንደ እኔ ከሆናችሁ ያለ የሌለ ትኩረት እና ሃይሌን ተጠቅሜ የምሰራው በፈታኝ ጊዜ ነው፡፡ ይህም የአብዛኞቻቸን የሰው ልጆች ልምድ እና ልምምድ ይመስለኛል፡፡ የአብዛኞቻቸንን ከላይ የጠቀሱት ጥያቄዎች መልሶቻችን የሚያመለክቱን በህይወታችን ፈተናዎች ወይም ተግዳሮቶች ብለን የምናስባቸው ነገሮች ልብ ማለት ከቻልን ለህይወታችን ስኬት እና ከነበርንበት የተሻለ ሰው እንሆን ዘንድ የተሰጡን መልካም አጋጣሚዎች እንደሆኑ ነው፡፡
አንዴ ቆም ብለህ አስብ፡--
o አሁንኑ ልትተገብረው የምትችለው ከጽሁፍ የተማርከው
አንድ ... ሁለት ... ሶስት ... ወዘተ ሃሳብ ምንድን ነው?
o ስላንድ ነገር ብዙ መረጃ መኖር ዕውቀት ነው፤
መረጃውን በተግባር መጠቀም ደግሞ ጥበብ ነው!
አስተያየት፣ ተጨማሪ ሃሳብ እንዲሁም ጥያቄ ካላችሁ በዚሁ
ድህረ-ገጽ ፃፉልን!
0 አስተያየቶች