በድሮ ጊዜ አንድ አቶ ደገመ የሚባል ሰውዬ ነበር፡፡ አቶ ደገመ ከስራ በፊት እና በኋላ ቴሌቪዥን አዝወትሮ ይከታተል ነበር፡፡ አቶ ደገመ ከራሱ ስራ እና ህይወት ይልቅ በቴሌቪዥን ሃሳባቸውን የሚያቀርቡ ጋዜጠኞችን፣ ፖለቲከኞችን ... ንግግር በተመስጦ በመከታተል አንዴ ይደሰታል፣ በሌላ ጊዜ ያዝናል፣ ይበሳጫልም፡፡ በመሆኑም አምሽቶ ስለሚተኛ እና ለስራውም ትኩረት ስለሌለው ምንጊዜም በቢሮ አርፍዶ ነው የሚገባው፡፡ በዚህም በመስሪያ ቤቱ ካሉት ሰራተኞች ሁሉ ብዙ የሰዓት ፊርማ በማሳለፍ እና ባለጉዳይ በማጉላላት ይታወቃል፡፡
አቶ ደገመ ታሪኩ የሚባል የአንደኛ ክፍል ተማሪ ልጅ ነበረው፡፡ አባቱ በቤት ውስጥ የሚሰራውን በተደጋጋሚና በአንክሮ የተመለከተው ተማሪ ታሪኩ ዘወትር በቴሌቪዥን ስክሪን ላይ መደቀን እና መከታተል ከትምህርት ቤት በፊት እና በኋላ የዘወትር ተግባሩን አደረገ፡፡ ታሪክ ራሱን ይደግማል እንዲሉ የአቶ ደገመ ልጅ ተማሪ ታሪኩ በአብዛኛው የቤት ስራውን አይሰራም፣ አምሽቶ ስለሚተኛ ክፍል ውስጥ ያንቀላፋል:: በትምህርቱ ስለደከመ በውጤቱ ከትምህርት ቤቱ ተማሪዎች በሙሉ ዝቅተኛ ሆነ፡፡ ሌላው አስገራሚው ነገር ደግሞ የተማሪ ታሪኩ ሙሉ ስም ታሪኩ ደገመ መሆኑ ነው፡፡ ስምን መላክ ያወጣወል ይሏችኋልም ይህ ነው፡፡
የተማሪ ታሪኩ ደገመ በጣም ዝቅተኛ ውጤት ያሳሰበው የትምህርት ቤቱ ርዕሰ-መምህር አቶ ማስተዋል ተማሪ ታሪኩን ወላጅ እንዲያመጣ ይነግረዋል:: አባትየው አቶ ደገመ እንደ ወላጅነቱ በተጠየቀው መሰረት ወደ ትምህርት ቤት ሄደ፡፡ በመቀጠልም አባትየው አቶ ደገመ እና ርዕሰ-መምህሩ አቶ ማስተዋል የሰላምታ ልውውጥ ካደረጉ በኋላ አቶ ማስተዋል አቶ ደገመን ስለ ልጁ ታሪኩ ደገመ በትምህርት ቤት እና በመማሪያ ክፍል ውስጥ ስላለው የትምህር ክትትል እና አጠቃላይ እንቅስቃሴ ሊያወያየው እንደፈለገው ገለጸለት፡፡ በዚህ አጀንዳ ላይም ውይይት ጀመሩ ...
ይቅርታ ውድ አንባቢዎቸ ... እንግዲህ የአቶ ማስተዋል እና አቶ ደገመ ውይይት ምን እንደሚመስል እና ውጤቱ ምን እንደሆነ አቶ ማስተዋልና አቶ ደገመ ውይይታቸውን ጨርሰው እንዳሳወቁኝ ይዠ በሌላ ጊዜ እመለሳለሁ፡፡ እስከዚው ግን ለምን እናንተ የዚህ ታሪክ ደራሲ ሆናችሁ በአቶ ማስተዋል እና በአቶ ደገመ መካከል የሚደረገውን ውይይት ምን እንደሚመስል እና ውጤቱ ምን እንደሆነ አትጨርሱትም?
በነገራችን ላይ ውድ አንባቢዎች እንደ አጋጣሚ ሆኖ ስማችሁ ወይም የልጃችሁ ስም ከገጸ-ባህሪዎቹ ጋር ከተመሳሰለ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ የገጸ-ባህሪያቱን ስሞች ለታሪኩ መልዕክት ማጠንከሪያ ሲባል የመረጥኳቸው እንጅ የማንንም የሚታወቅ አባት፣ ልጅ እንዲሁም ርዕሰ-መምህር ስም አይወክሉም፡፡
ልብ በሉ ይህ የብዙዎቻችንን ታሪክ የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡
በታሪኩ ውስጥ በቴሌቪዥን የተወከሉ በጣም ብዙ ሌሎች ነገሮች አሉ፡፡
የአባት አቶ ደገመ ታሪክ የእናቶችንም ታሪክ ይጨምራል፡፡
የግንዛቤ ጥያቄዎች፡-
የአቶ ደገመ እና የአቶ ማስተዋል ውይይት አጨራረሱ ምን ይሆን ይመስላችኋል?
አቶ ደገመ ልጁን ታሪኩን ምከረው ቢባከል ምን ብሎ የሚመክረው ይመስላችኋል?
ልጅ ታሪኩ አባቱን
አቶ ደገመን ከምክሩ በስተመጨረሻ ምን የሚለው ይመስላችኋል?
የስንቶቻችን ልጆች ይሆኑ የዚህን ታሪክ ገጸ-ባህሪይ ልጅ የሚወክሉ?
ስንቶቻችን አባቶችና እናቶች ነን የዚህን ታሪክ ገጸ-ባህሪ አባት የምንወክል?
ከታሪኩስ ምን ተማራችሁ?
የት/ቤቱ ርዕሰ-መምህር አቶ ማስተዋል ተማሪ ታሪኩ ደገመን በምን መንገድ ካለበት የትምህርት ድክመት ወደ ጎበዝነት ማምጣት ይችላል ብላችሁ ታስባላችሁ?
አንዴ ቆም ብለህ አስብ፡--
o አሁንኑ ልትተገብረው የምትችለው ከጽሁፍ የተማርከው አንድ ... ሁለት ... ሶስት ... ወዘተ ሃሳብ ምንድን ነው?
o ስላንድ ነገር ብዙ መረጃ መኖር ዕውቀት ነው፤ መረጃውን በተግባር መጠቀም ደግሞ ጥበብ ነው!
አስተያየት፣ ተጨማሪ ሃሳብ እንዲሁም ጥያቄ ካላችሁ በዚሁ ድህረ-ገጽ ፃፉልን!
0 አስተያየቶች