የሰው ልጅ ተስፋው ቁሳቁስ ነውን?

ብዙዎቻችን ተስፋችንን ገንዘባችን ላይ፣ ስልጣናችን ላይ፣ ዲግሪዎቻችን ላይ፣ ቤተሰቦቻችን ላይ፣ መንግስት ላይ፣ ባሉን ንብረቶቻችን ላይ … እናንተም ጨምሩበትና በመሳሰሉት ቁሳቁሶች ላይ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ የየዕለትና የየቅጽበት ስሜቶቻችን ማለትም ደስታችን፣ ፍቅራችን፣ እርካታችን … ሁሉ በእነዚህ ቁሳቁሶች የተወሰነ ነው፡፡ ይባስ ብሎም እነዚህ ቁሳቁሶች የማንነታችን መገለጫ እስኪመስሉን ድረስ ተስፋ እናደርግባቸዋልን፡፡ 

እንደሚታወቀው ቁሳቁስ ለሚና ጠፊ ነውና አንዴ ይለማሉ ሌላ ጊዜ ይጠፋሉ፡፡ ተስፋችንን ቁሳቁሶች ላይ የማድረጋችን ትልቁ አደጋም አዚህ ላይ ነው፡፡ ቁሳቁሶቻችን ሲለሙ ተስፋችን አብሮ ይለመልማል፣ ሲጠፉ ደግሞ ተስፋችንም አብሮ ይጠፋል፡፡ ስለሆነም በህይወታችን አንድ ጊዜ ባለተስፋ፣ ሌላ ጊዜ ተስፋ-ቢስ እየሆንን ኑሯችንን እንገፋለን ማለት ነው፡፡ እንደየወቅቱ አየር ጠባይ የሚቀያየር ኑሮ እንገፋለን፡፡ 

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በጣም ብዙው የዓለም ህዝብ በዓለም ላይ ያለውን ጭንቀት፣ ሽብር፣ ውጥረት፣ ህመም፣ መገዳደል፣ እብደት፣ ክህደት … ወዘተ እናንተም ጨምሩበትና የተንሰራፋበት ህይወት መሰረቱ ተስፋን በአይን ከሚታይ እና አላፊ፣ ጠፊ ከሆነው ከቁስ ላይ በማድረጋችን ነው፡፡ እርግጥ ነው ከላይ የተጠቀሱት ቁሳቁሶች ለህይወታችን አስፈላጊ ናቸው፡፡ ተስፋችን ግን ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም እኛ ከቁሳቁሶቹ በፊት የተፈጠርን እና ከቁሳቁሶቹ በላይ የሆንን ድንቅ በፈጣሪችን አምሳል የተፈጠርን ነንና፡፡ 

ታዲያ ለዚህ ሁሉ ዘላቂው እና አዋጪው መፍትሄ የእውነተኛው የሰው ልጅ ተስፋ ምን እንደሆነ ጠንቅቆ በማወቅ ተስፋችንን ለእውነታኛው እና ለዘላቂው የተስፋ ባለቤት ላይ ማድረግ ነው፡፡ እግዚአብሔር እኛን ሰዎችን ፈጠረ፣ እኛ ሰዎች ደግሞ እግዚአብሔር በገለጠልን ጥበብ መጠን ቁሳቁሶቹን ፈጠርን፡፡ ስለዚህ ጉዳያችን ተስፋ ስለመሆን ከሆነ እኛ ለቁሳቁሶቹ መኖር ተስፋዎች እንጅ ቁሳቁሶች ለእኛ ተስፋ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ አለበለዚያማ ቁሳቁሶች የሌሉት እንድ ምስጊን ሰው የመኖር ተስፋው ምን ይሁን? 

ስለዚህም የተስፋችንን ትኩረት አቅጣጫ አሁንኑ ማስተካከል ይኖርብናል፡፡ ይሀን ስናደርግ ትኩረታችን ውጤቱ ላይ ሳይሆን መንስኤው ላይ ሆነ ማለት ነው፡፡ ባይሆን ስላሉን ቁሳዊ ነገሮቻችንን ስናስብ ጥበቡን ገልጾልን እንድንፈጥራቸው ስላስቻለን እግዚአብሔር እንደ ማመስገኛ መሳሪያ ልንጠቀማቸው እንችላለን፡፡ 

እንዲሁም ያሉንን ቁሳቁሶቻችንን በባለቤቱ በእግዚአብሐር ስም ማድረግ አለብን፡፡ ይህንን ያደረግን እንደሆን ቁሳቁሶቻችን ሲለሙልን አምላካችንን እንመሰግናለን፣ ሲጠፉብን ደግሞ ባለቤቱ በፈቀደው ጊዜ ሁሉ የወደደውን ለበጎ ያደርግ ዘንድ ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድረርጎ ሰራው እንላለን እንጅ ተስፋ-ቢስ መሆናችን መሰረት የለውም፡፡  

ይሁን እንጅ ብዙዎቻችን ተስፋችን ባሉን በሚታዩ፣ በሚያልቁ፣ በሚሰረቁ፣ በሚጠፉ … ቁሳቁሶቻችን ላይ ነው:: ይባስ ብሎም ቁሳቁሶች እንደ ማንነታችን መገለጫ ተስፋዎቻችን እንቆጥራቸዋለን:: ስለሆነ እኒህ ቁሶቻችን ሲያልቁ፣ ሲሰረቁ እና ሲጠፉ ከቁሶቹ የበለጠ ዋጋን በራሳችን ፈቃድ እንከፍላን፡፡ ማለትም ፊታችንን እንፈጃለን፣ ጸጉራችን እንነጫለን (ጸጉር የሌላቸው መላጣዎችን አይጨምርም)፡፡ ባጠቃላይም የህይወት ደስታችን እና ተስፋችንን እናጣለን፡፡ በዚህም የተነሳ ይሄው ዓለም የሃዘን፣ የሽብር፣ የውጥረት፣ ህመም፣ መገዳደል፣ እብደት፣ ክህደት … ወዘተ ቀጠና ከሆነች ከራርማለች፡፡ በእርግጥም ደስታችንና ተስፋችንን በቁሶቻችን ላይ ማድረጋችንን እስከ ቀጠልን ድረስ የዓለም ህይወት ተስፋ-ቢስነቱ የሚቀጥል ይሆናል … 

ሰው በፈጣሪው አምሳል የተፈጠረ ድንቅ ፍጡር ከመሆኑ በላይ ምን ተስፋ አለው?

የሰው ልጅ ትክክለኛና የማይናወጥ ተስፋው ሰውን ብቻ ሳይሆን ዓለምንም ጨምሮ ካለመኖር ወደ መኖር ቀጥሎም ዓለም እና በውስጧ ያሉ ሁሉም ነገሮች ስርዓታቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ፣ የሚያልፉትም በጊዚያቸው እንዲያልፉ … በሚያደርገው በሃያሉ አምላክ እግዚአብሐር ነው፡፡ ይህንን በበኩሌ ከአባቶቼ በጣም ብዙ ጊዜ የምሰማው እና ምን አዲስ ነገር አለ፣ ይህማ እውነት ነው በሚል በውስጤም ጥርጥር አለው እንዴ ነበር የምለው፡፡ ይሁን እንጂ የሰው ልጅ ተስፋው እግዚአብሔር ነው ስለሚለው ሃሳብ ስላለኝ እምነት ራሴን በእውነት ስገመግም ይህ ሃሳብ ምዕናባዊ አባባል እንጅ በተግባር በህይወታችን የሚሰራ የህይወታችን መሰረት መሆኑን ልብ የማልለው እና እምነቴም የጎደለ ሆኖ አገኘሁት፡፡ እናንተ ሃሳቡን ስትሰሙት ምን እንደሚሰማችሁ እና ምን ያህል እንደምታምኑት ለእናነተው ልተወው፡፡

በእውነት ለሰው በፈጣሪው አምሳል የተፈጠረ ድንቅ ፍጡር ከመሆኑ በላይ ምን ተስፋ አለው? በእግዚአብሔር አምላክ አምሳል እኮ ነው የተፈጠርነው፡፡ ሃሳቡ በታላቁ መጽሐፍ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ ተጽፎ ይገኛል፡፡ የቃሉ ባለቤት እግዚአብሔር አምላክም ለደቀ-መዛሙርቶቹ በመገለጥ ሃሳቡን ለዓለም ህዝብ በተግባር እንዲገልጡ እና እንዲያስተምሩም ነግሯቸዋል፡፡ ደቀ-መዛሙርቱም ለኣለም ህዝብ ገልጠዋል (በስሙ አምነው ተዓምራትን በማድረግ)፣ አስተምረውማል፡፡ እንዲሁም አባቶቻችን ከልጅነት እስከ ዕውቀት አስተምረውናል፡፡ ዳሩ ግን እንሰማለን እንጅ አናዳምጥም፣ አንረዳም፡፡ አዳምጠን፣ ተረድተን እና ልብ ብለን ቢሆንማ የሰማይ አእዋፋት፣ የምድር አበቦች፣ የዱር አራዊት ሳይቀሩ ህይወታቸውን በአግባቡ መምራት ሲችሉ እኛን ምን ነካን? ይህንን አባባል በተደጋጋሚ ለራሴ ባወጣሁ ባወረድሁ ጊዜ ሁሉ እጅግ በጣም ይደንቀኛል፡፡ እናም ልብ እንበል ራሳችንንም በሚገባ እንረዳ፡፡ ማን እንደሆንን እንመርምር፡፡ 

ለሰው ልጅ በእምነቱ ብቻ ተራራን ያፈልስ ዘንድ የተሰጠው ሃይል ምንኛ ትልቅ ተስፋ ነው?

ሰው በአእምሮው ያሰበውን፣ በልቡ ያመነውን ሁሉ ያገኛል፡፡ ሰው እንዳሰበው እና በልቡ እንዳመነው እንደዛው ነው የሚለው የእግዚአብሐሔር ቃልም ይሄው ነው፡፡ ብዙዎቻችን እንደነዚህ እና የመሳሰሉ ከአምስቱ የስሜት ህዋሶቻችን መረዳት በላይ የሆኑ ሃሳቦችን ስናነብና ስንሰማሰማ እንዴት ሊሆን ይችላል በማለት ጥያቄዎች እናነሳለለን፣ እንሞግታለንም፡፡ ይሁን እንጅ ይህ ጥያቂያችን እና ሙግታችን በእግዚአብሔር አሰራር ስላለን የእምነት ጉድለት ቁልጭ አድርጎ ከማሳየት የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ ልብ አለማለታችን እንጅ በጣም ብዙ ነገሮች የሚሆኑት ከእኛ መረዳት በላይ ው፡፡ ደግሞስ የእግዚአብሔርን አሰራር ምርምሮ የሚደርስ ማነው? ለዚህም የራሳችንን ሰውነት እና በውስጡ የሚካሄዱ ስራዓቶች በራሳቸው ከእኛ መረዳት በላይ ናቸው፡፡ እንድ ገበሬ ወቅቱን ጠብቆ ዘሩን ይዘል እንጅ ዘሩ እንዴት እንደሚበቅል፣ ደቃቋ ዘር እንዴት ወደ ዛፍ እንደምትቀየር፣ እንዴትስ አንዷ የዘር ፍሬ ብዙ መቶዎች እና ሽዎች ዘሮች እንደምትሆን ለማወቅ አይዳዳም፣ ቢዳዳም ሊረዳው አይችልም …  

 



ስለዚህ ሰው ካመነ የፈለገውን ነገር ይሆንለታል፣ ይደረግለታል የሚለው አምላካዊ ቃል ለሰው ልጆች ሁሉ ትልቁ ተስፋችን ነው፡፡ እኛ እያንዳንዳችን ዛሬ አሁን በህይወት ዘርፎቻችን ያሉን ማንኛውም ውጤቶቻቸን (የትዳር ጓደኞቻቸን፣ ገቢዎቻችን፣ ስራዎቻችን፣ ትምህርታችን …) በእምነታችን ልክ የተሰጡን ናቸው፡፡ በህይወት ዘርፎቻችን ስለምንፈልጋቸው ማንኛውም ነገሮች የምናገኝበት መጠን የሚወሰነው ነገሮቹን ልናገኛቸው እንደሚገባን እና እንደሚሰጡንም ባለን እምነት ልክ ነው፡፡ 

እጅግ በጣም የሚገርመው ነገር ደግሞ ስላንድ ነገር ማመናችንን ብንረዳም ባንረዳም እንዲሁም ለጥሩም ሆነ ለመጥፎም መስራቱ ነው፡፡ የእምነትን ሃይል እና በህይወታችን ያለውን ፋይዳ ለመረዳት አንድ ምሳሌ እንውሰድ እና እንመልከት፡፡ አንድ ሰው ገና በህፃንነቱ ድህነት ጥሩ እንደሆነ እና ለጽድቅ እንደሚያበቃ በተደጋጋሚ ቢነገረውና ይህንን ሃሳብ ሳያውቀው በድብቁ አእምሮው ይዞት ቢሆን በህይወቱ ድህነት ይገለጣል፡፡ ድህነትም ለእርሱ የጽድቅ በር ነው፡፡ ይህንን የውስጥ እምነቱን እርሱ ላይረዳው ይችላል፡፡ ነገር ግን ሰውየው በውስጡ (በድብቁ አእምሮው) ሰለድህነት ያለው የተሳሳተ እምነት ሰውየውን ሌት ተቀን ለድህነት እንዲሰራ ያደርገዋል፡፡

ይህም ብቻ አይደለም ሰውየው ግብሩ፣ ልማዱ፣ ባህሪው፣ ስዕብናው … ሁሉ ድህነትን የሚገልጽ ይሆናል፡፡ ሰውየው ንቁ አእምሮውን ተጠቅሞ ሃብትን እና ብልጽግናን ቢያስብ እና እንደምንም ሃብታም ለመሆን ቢሞክርም እንኳ በመጀመሪያ ሃብት እና ብልጽግናን የማግኘት ዕድሉ ዝቅተኛ ነው፡፡ እንደምንም ተሟሙቶ ካገኘም ደግሞ ውስጣዊ ማንነቱ ግብሩ፣ ልማዱ፣ ባህሪው፣ ስዕብናው … ሁሉ ሳይወድ በድግ እና ሰይረዳው በውስጡ (በድብቁ አእምሮው) ድህነትን የሚገልጽ ይሆናል፡፡ ለዚህም ነው ብዙዎቻችን በቀን ውሷችን እና በህወታችን በንቁ አእምሯችን ልንሰራው የምንወደው አንድ ነገር፣ በተጨባጭ ስንሰራ የምንውለው እና የምንኖረው ደግሞ ሌላ ነገር ሆኖ ከማያስደስተን ህይወት ጋር ስንታገል የምንኖረው፡፡ 

አብዛኞቻችን ይህንን ምስጢር ስለማንረዳ ብዙ ጊዜ በህይወታችን ስለሆነብን ነገር ሁሉ እግዚአብሔር እንደማይወደን እና እንደረሳን እንዲሁም ራሳችንን እንደ ዝቅተኛ፣ ደካማ እና እንደማይችል ሰው አድርገን በማሰብ እና በማመን አምላካችንን እና ራሳችንን በመውቀስ ጭራሽ በወቀስነው ልክ እና በላይ ሆኑ የህይወት ቀውሶች እየተዳረግን ህይወት ትግል ሆናብን እንኖራለን፡፡ለዚህም ነው ሰው በህይወቱ ስለሆነው ነገር ሁሉ ማመስገን እንጅ ማማረር የሌለበት፡፡ ይህም ምስጋናው ስለሁለት ነገር ነው፡፡ አንድም እኛ ሰዎች ይወታችን ስለሆነው ነገር እንዴት እና ለምን እንደሆነ ስለማናውቅ፡፡ አንድም ሰው የዘራውን ያጭዳልና ባመሰገነ ቁጥር የበለጠ የሚያመሰግንበትን ሁሉ ይጨመረዋልና ነው፡፡

ለዚህ ሁሉ የእምነት ዝንፈት እና የህይወት ቀውስ መላው ምንድን ነው?

ደስ የሚለው ዜና ለዚህ ሁሉ ለነገሮች ያለን የተዛነፈ ወይም የተንሻፈፈ የእምነት ማስተካካያ አስተማማኝ እና እርግጠኛ መንገድ አለው፡፡ መንገዶቹም እንደሚከተለው ተገልጸዋል እና ተግባራዊ ልምምድ ዛሬውኑ አሁን እንጀምር፡- 

በመጀመሪያ በህይወት ዘርፎቻችን የተዛነፈውን ወይም የተንሻፈፈውን እምነት (ከላይ ባየነው ምሳሌ መሰረት ድህነት የጽድቅ በር ነው) በሚገባ ለይቶ ማወቅ ነው፡፡ 

በመቀጠልም በተዛነፈው ወይም በተንሻፈፈው እምነት ልንተካው የምንፈልገውን አዎንታዊ እና ትክክለኛ እነምነት (ከላይ ባየነው ምሳሌ መሰረትም ብልጽግና ራሴን ነፃ የማደርግበት፣ ቤተ-እምነት የምገነባበት፣ የተቸገሩትን የምረዳበት … ለህይወቴ አስፈላጊ ነገር ነው) መወሰን፡፡ 

በስተመጨረሻ ልክ ያ የተዛነፈው ወይም የተንሻፈፈው እምነት በልጅነታችን ሳናውቅ በተደጋገመልን መሰረት እንደተጋባብን ሁሉ ይህንን የምንፈልገውን አዎንታዊ እና ትክክለኛ እምነት ለራሳችን በመደጋገም (በተለይ ልንተኛ ስንል እና ከምኝታችን እንደተነሳን) ቢቻል በጽሁፍ አለበለዚያም በንግግር ለራሳችን በመንገር ከሃሳብነት ወደ እምነት በመቀየር የድብቁ አእምሯችን አንድ ፕሮግራም ማድረግ እንችላለን፡፡ 

ይህ የምፈልገው አዎንታዊ ሃሳብ ወደ እምነት በተቀየረ ቅጽበት ጀምሮ እንዴት እንደሆነ ሳናውቀው እና ሳንረዳው ሌት ተቀን ለሃብት እና ለብልጽግና ስንሰራ እና ስንታተር ራሳችንን እናገኛለን፡፡ ባህሪያችን፣ ስዕብናችን፣ ልማዳችን፣ ምግባራችንም ሁሉ የሃብታም እና የባለጸጋ ይሆናል፡፡ ይህም ከሁለት እስከ አራት ሳምንታትን ይወስዳል፡፡ ይንን ራሴ አድርጌው ለውጥ አምጥቶልኛል እና ዘሬውኑ በራሳችሁ ላይ ልምምዱን ጀምሩት፡፡ ይህንን ለማድረግ ምንም ክፍያ እና የማንንም ፍቃድ አይጠይቅም፡፡ የሚያስፈልገው ነገር ቢኖር ራሳችን በራሳችን ላይ ሙከራ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆን ብቻቻቻ …

እንግዲህ ውድ አንባቢዎች ድህነትን እንደምሳሌ አነሳን እንጅ በሁሉም የእያንዳንዱ የህይወት ዘርፎቻችን የሚሆነው ይሄው ነው፡፡ እናም በህይወታችን ስኬታማ ልንሆን የፈለግን ሰዎች ሁሉ ስኬታማ ለመሆን ጉዟችንን ከመጀመራችን በፊት በህይወት ዘርፎቻችን ልናሳካው የፈለግነውን ነገር አስበን ከመወሰን በመቀጠል ልናሳካ ስለፈለግነው ነገር ያለን ውስጣዊ እምነት ምን እንደሚመስል ራሳችንን መገምገም ወሳኝ ነውና እንዲሁ እናድርግ፡፡ 


አንዴ ቆም ብለህ አስብ፡--

አሁንኑ ልትተገብረው የምትችለው ከጽሁፍ የተማርከው አንድ ... ሁለት ... ሶስት ... ወዘተ ሃሳብ ምንድን ነው?  

ስላንድ ነገር ብዙ መረጃ መኖር ዕውቀት ነው፤ መረጃውን በተግባር መጠቀም ደግሞ ጥበብ ነው!

 

አስተያየት፣ ተጨማሪ ሃሳብ እንዲሁም ጥያቄ ካላችሁ በዚሁ ድህረ-ገጽ ፃፉልን!