ለሰዎች መልካም ነገር ሳደርግ ቅድሚያ የሚጠቅመኝ ራሴን ነው

ያኔ ገና ሳይገባኝ ለሰዎች የማደርገው ደግ ነገር ሁሉ ለሰዎች ብቻ ያደረኩት ይመስለኝ ነበር፡፡ አሁን ግን ሲገባኝ ለካስ ጥቅሙ ቅድሚያ ለራሴ ነው፡፡ 

እስኪ ማነው ለሰዎች መልካም ነገርን አድርጎ የማይደሰት እና የማረካ? 

ሰው በህይወቱ ከመደሰት እና ከመርካት በላይ ምንስ ስኬት አለው? 

ደግሞስ በፈጣሪ አምሳል መፈጠራችን የፈጣሪን ግብር እያደረግን የእርሱን ጸጋና በረከት እንካፈል ዘንድ አይደለምን?

ዳሩ ግን ዓለም ያኔ ገና በጨቅላነት ዕድሚያችን በሰመመን ላይ እያለን በዙሪያችን በነበሩ ሰዎች አማካኝነት ክፋቷን አስተማረችን፡፡ 

ክፉ ማድረግ የየዕለት ልምምዳችን እና ልማዳችን ሆኖብን ይሄው ዛሬ ራሳችንን ስናውቅ መልካም ነገርን የማድረግ መሻትና ፍላጎት ቢኖረን እንኳን በልማዳችን እስር ቤት ቁጥጥር ስር ሆነን ክፉትን ከማድረግ ጋር ተጋብተን እንኖራለን፡፡ 

ሁሌም ቢሆን ልማድ ፍላጎትን ያሸንፋልና፡፡ ስለሆነም መልካም ነገርን ማድረግ ከመሻትና ከመፈለግ ባሻገር በየቅጽበቱ እና በየዕለቱ ልምምዳችን እና ልዳችን ማደረግ ላይ ማተኮር አለብን፡፡

ከላይ እንደተመለከትነው ለሰዎች መልካምን ሁሉ ማድረጋችን የመጀመሪያው ተጠቃሚዎች እኛው ራሳችን መሆናችን አይተናል፡፡ 

ስለዚህ ሁሌም ቢሆን ማልካም ነገርን ማድረግ የህይወታችን መርህ ማድረግ ከሰዎች በበለጠ ለእኛ ያዋጣናል፡፡ 

ምንም ውጣ ውረድ እና ክፍያ ስለሌለው ይልቁን የራሳችንን ደስታ በራሳችን የምንፈጥርበት አንዱ እና ዋናው መንገድ ስለሆነ ለሰዎች መልካም ማድረግን ልምምዳችን እና ልማዳችን እናድርግ፡፡

በሰዎች ላይ የማደርገው ክፉ ነገር ቅድሚያ የሚጎዳ ራሴን ነው

ያኔ ገና ሳይገባኝ በሰዎች ላይ የማደርገው ሁሉ ክፉ ነገር በሰዎች ላይ ብቻ ያደረኩት ይመስለኝ ነበር፡፡ አሁን ግን ሲገባኝ ለካስ ጉዳቱ ቅድሚያ በራሴ ላይ ነው፡፡ 

ያ የማደርገው ሁሉ ክፉ ነገር በእኔው አእምሮ ተጸንሶ በእኔው አንደበት መፈጸሙ ሲገባኝ ክፉ ነገሩ ከሚፈጸምበት ሰው ባላነሰ እንዲያውም በበለጠ በመጀመሪያ ተጎጂው እኔው ራሴ እንደሆንኩ በገባኝ እና ልብ ባልኩ ጊዜ ደነቀኝ፡፡

ደግሞም ሰው የዘራውን ያጭዳል የሚለውን የማይዛነፍ አምላካዊ እና ተፈጥሯዊ ህግ ባሰብኩም ጊዜ የበለጠ ደነቀኝ፡፡ ክፋትን ያደረገ ክፋትን፤ መልካምን ያደረገም መልካን ይጠብቅ ነውና፡፡

ከዚህ ባሻገር እስኪ ማነው በሰዎች ላይ ክፉ ነገርን አድርጎ የማያዝን እና የማይጸጸት? 

ሰው በህይወቱ ከማዘን እና ከመመጸጸት በላይ ውድቀት እና የምድራዊ ሲኦል ኑሮ የታለ? 

በስተመጨረሻም በሰዎች ላይ ክፉ ማድረጌ በራሴ ላይ የበለጠ ክፉ ማድረጌ መሆኑም ግልጽ ሁነልኝ፡፡ 

ንን ሁሉ ተረዳሁ ጊዜ ጀምሮ በምችለው ሁሉ መጠን በሰዎች ላይ የማደርገውን ብቻ ሳይሆን የማስበውን ሁሉ መልካሙን ነገር ለማድረግ ዘወትር ልምምድ እና ልማድ ለማድረግ እጥራለሁ፡፡

እናንተስ?

እዚህ ላይ አንድ መዘንጋት የሌለበት ቁልፍ ነገር በሰዎች ላይ ክፋትን ላለማድረግ ክፋት ላይ ማተኮር፣ ክፋትን ማውገዝ አይጠበቅብንም፣ የለብንምም፡፡ 

ይልቁንም ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ መልካም ነገር ማድረግን አብዝተን ልምድ እና ልማድ ማድረግ ብቻ ነው፡፡ 

ምክንያቱም ተኮርንበት ማንኛውም ነገር (ለህይወታችን ጠቃሚም ይሁን ጎጂ) በህይወታችን የበለጠ ይበዛል፡፡ 

ስለሆነም ክፋትን ማውገዝ ላይ ማተኮር የለብንም መልካም ነገርን ማድረግ ላይ እንጅ፡፡ ደግሞስ ብርሃን ከጨለማ ምን አለው፡፡ 

ብርሃን ጨለማን ይገልጣልና ብርሃን ባለበት ጨለማ የለም እና ብርሃን ስለጨለማ አይጨነቅም፡፡ እኛም መልካም ነገርን ማድረግ ላይ ካተኮርን ክፉ ነገር ከህይወታችን በራሱ ይጠፋልና ስለ ክፉ ነገር ማሰብ አጠበቅብንም፡፡

በነገራችን ላይ ሰዎችን በክፉ ነገራቸው የሚኮንኑ እና የሚፈርዱ ሰዎችም እንዲሁ ናቸው፡፡ሰዎችን በስህተታችው ወይም በኃጢታቸው በምንኮንናቸው ጊዜ፡-

አንደኛ ነገር እኔ ስህተት ወይም ኃጢት አልሰራም፣ ፃድቅ ነኝ እያልን ነው፡፡ ነገር ግን ችንም ኃጢት ነፃ አለመሆናችንን ይህችን ኃጢያተኛ ሴት ከኃጢያት ነፃ የሆነ ይውገራት በተባን ጊዜ ጉዳችንን አይተናል፡፡

ሁለተኛ ነገር ደግሞ የሰዎች ህጸጽ ጎልቶ የሚታየው ሰው ያንን ህጸጽ የሚሰራ ሰው ነው፡፡ አለበለዚያማ ብርሐንን ከጨለማ ምን አገናኘው? መለትም ብርሐን ብርሐንነቱን እንጅ ስለጨለማ የሚያውቀው አንዳች ነገር የለም፡፡

ሶስተኛው ነገር ሰዎችን በክፉ ነገራቸው ስንኮንናቸው እና ስንፈርድባቸው ሳናውቀው እኛው ራሳችን የክፉ ነገሩ ተካፋይ እንሆናለን፡፡ በአእምሯችን እያሰብን እና በአንደበታችን እየተናገርን ያለነው ስለክፉ ነገር ነውና፡፡

ሰዎችን በክፉ ነገራቸው ስንኮንናቸው በአእምሯችን እያሰብን እና በአንደበታችን እየተናገርን ያለነው ስለክፉ ነገር ነውና፡፡ 

አትፍረዱ ይፈረድባችኋል የሚለው አምላካዊ ቃልም መሰረቱ ይህ ነው፡፡ 

እንድም እናንተው ራሳችሁ ብዙ ክፉ ነገርን አድርጋችኋል ሲለን ነው፡፡ 

አንድም በአእምሯችሁ እያሰባችሁት እና ባንደበታችሁ እየኮነናችሁ ወይም እየፈረዳችሁ ባለው በባለ እጀራችሁ ክፉ ነገር ትጠመዳላችሁ ሲለን ነው፡፡ 

በመሆኑም ስለሰዎች ብቻ ሳይሆን ስለራሳችንም ብለን በቻልነው ሁሉ አጋጣሚ ሌሎችን በሰሩት ክፉ ነገር ከመኮነን እና ከመፍረድ እንቆጠብ፡፡


አንዴ ቆም ብለህ አስብ፡-

ዛሬ አሁንኑ ልትተገብረው የምትችለው ከዚህ ጽሁፍ የተማርከው አንድ … ሁለት … ሶስት … ወዘተ ሃሳብ ምንድን ነው?  

ስላንድ ነገር ብዙ መረጃ መኖር ዕውቀት ነው፤ መረጃውን በተግባር መጠቀም ደግሞ ጥበብ ነው እና አሁንኑ በተግባር ግባ!

 

አስተያየት ተጨማሪ ሃሳብ እንዲሁም ጥያቄ ካላችሁ በዚሁ ድህረ-ገጽ ፃፉልን!