በእውነት በዚህ ውጫዊ ጫጫታው በበዛበት ጊዜ እና ዘመን ለራስ ጊዜ ሰጥቶ ወደ ራስ ውስጥ እንደመመልከት ስኬት አለን? የራስን ህይወት ምርጫ እና ውሳኔ በራስ እንደመምረጥ እና እንደመወሰን የሚያስፈልግ ትልቅ የህይወት ስኬት መንገድ ምን አለ? 

ምናልባትም ልብ ያላልኩት እና ያልተረዳሁት ከዚህ ቀዳሚ የሆነ የህይወት ስኬት ካለ ሰዎች እስኪ ንገሩኝ?

በዚህ ጊዜ እና ሁኔታ ነው የውጩን ሁሉ ጫጫታ እና እኔን ስሙኝ የሚለውን ሁሉ (ፖለቲከኛውን፣ መገናኛ-ብዙሃኑን፣ የማይጠቅመን ጓደኛችንን፣ የኑሮ ውድነቱን፣ ትክክል ያልሆኑ የሃይማኖት አባቶች ነን ባዮችን ሳይቀር ...) ለጊዜውም ቢሆን ወደ ኋላ ትቶ ለራስ ጊዜ ሰጥቶ ወደ ራስ ውስጥ መመልከት እጅግ ድንቅነት ነው፡፡ 

ህይወታችንንም ልክ እንደ ሳይንቲስት በመመርመር፣ የራስን ህይወት ምርጫ እና ውሳኔ በራስ መምረጥ እና መወሰን የሚያስፈልገው በዚህ ቀውጢ ጊዜ ነው፡፡ 

ብሎም ለራስ ብቻ ሳይሆን ለብዙዎች የሚተርፍ እሴትን መፍጠር ትልቅ የህይወት ስኬት ነው፡፡ ከውስጥ ወደ ውጭ መኖርን መርህ ማድረግ በዚህ ፈታኝ ጊዜ ከመቸውም በላይ ያስፈልጋል፡፡


አለበለዚይ እንዲሁ የውጭውን ጫጫታ እና ሁከት እያየን እየየ ብንል በእውነቱ ፋይዳው ምንድን ነው? 

እየየ ማለታችን የሚያመጣው ለውጥ ቢኖር ይሄው እስከዛሬ ስለምን ለውጥ አላመጣንም? ጭራሽስ አይናችን እያየ እያለቅን አይደለንም? 

ስለምን የኢዮብን ታሪክ አናስታውስም? 

ያንን ሁሉ መከራ እንዴት ቻለው? ስለዚህ ማለቃችን ካልቀረ ጥሩ እየሰራን እንለቅ ወይስ እንዲሁ እያለቀስን? 

ካለቀስንስ በመገናኛ-ብዙሃን ወይስ መልስ ወደሚሰጠን ዳኛ በድብቅ? ምናልባት እኔ ያልታየኝ ነገር ካለ ንገሩኝ፣ ፃፉልኝ ...

መልካም ሰው በተረበሸ ከተማ ውስጥ ሆኖ ሰላምን ያገኛል፣ ክፉ ሰው ደግሞ በሰላም ከተማ ውስጥ ሆኖ በውስጡ አመጽን ያነሳል የሚባለውም ለእንደዚህ ዓይነት ወቅት እጅግ ተስፋን ሰጪ አምላካዊ ቃል ነው፡፡ 

ዳሩ ግን በህይወት ካልኖርነው የቃሉ ተስፋ ሰጪነት ብቻውን በህይወታችን ለውጥ አያመጣም፡፡

ለማንኛውም ምርጫና ውሳኔዎቻችን በሌሎች ሰዎች በመንጋ፣ በመገናኛ ብዙሃኖች፣ በሁኔታዎች ... በሚወስኑልን በዚህ ጊዜ እና ዘመንም ቢሆን ፈቃዳችን እና መሻታችን ከውስጥ ወደ ውጭ መኖር ከሆነ የግል የህይወት ምርጫና ውሳኔዎቻችን ያለማንም እና ያለምንም ጣልቃ-ገብነት ሙሉ በሙሉ በራሳችን መምረጥ እና መወሰን እንችላለን፡፡ ብሎም የምንፈልገውን ህይወት የመኖር አጋጣሚው እና ዕድሉ አለን፡፡ 

ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለብዙዎች የሚሆን እሴት መፍጠርም እንችላለን:: እየተፈጠረ ያለውን አገራዊ እና ዓለም-አቀፋዊ ቀውስ መፍታት እንዲሁ፡፡ 

ለዚህም ነብዩ ሙሴን እናስታውስ፡፡ በማይታመን ሁኔታ ወደ ባህር ተጥሎ ሳለ ለራሱ መትረፍ ብቻ ሳይሆን እስራኤልን ከፈርኦን ባርነት አወጣ፡፡ ይህ በእውነት እንዴት ሊሆን ቻለ?

ምናልባት ውድ አንባቢየ ይህንን ሃሳብ ስታነብ እኔ አንድ ሌሎች በሚመሩት የመንግስት መስሪያ ቤት ወይም የግል ድርጅት ውስጥ ተቀጥሬ የምሰራ ምስጊን ባለሙያ ወይም ምንም ምን የእኔ የምለው ልምድ፣ ሃብት፣ ዘመድ፣ ትምህርት፣ ዕውቀት ... የሌለኝ ምስጊን ግለሰብ እንዴት ነው ከውስጥ ወደ ውጭ መኖር የምችለው? 

እንዴትስ ነው የግል የህይወት ምርጫና ውሳኔዎቼን ያለማንም እና ያለምንም ጣልቃ-ገብነት ሙሉ በሙሉ በራሴ መምረጥ እና መወሰን ብሎም የምፈልገውን ህይወት የመኖር አጋጣሚ እና ዕድል ሊኖረኝ የሚችል? 

ትቀልዳለህ እንዴ ልትል ትችላለህ፡፡ እርግጥ ነው ይህ በደንብ ይገባኛል፣ እረዳለሁም እኔም ቢያንስ አንዱ ሌሎች በሚመሩት የመንግስት መስሪያ ቤት የምሰራ ምስጊን መምህር ስለሆንኩ፡፡ 

ነገር ግን ይህ ምስጊን ባለሙያነታችን ራሳችን ላይ እንናተኩር ሊፈትነን ይችላል እንጅ ሊያግደን ግን አይችልም፡፡ 

ስለሆነም ከዛሬ ጀምሮ በተቻለ መጠን አሰቃቂ ዜናዎችን ባለመስማት ይልቁንም ይህ እንደተራራ ገዝፎ ወገባችንን ያጎበጠንን የዘረኝነት እና የሃይማኖት ጥላቻ እና መገዳደል እንዲሁም የኑሮ ውድነት በቅድሚያ ራሳችንን እንዴት ነፃ እንደምናወጣ መንገዶች መቀየስ፡፡ 

ለእኛ የሰራው መንገድ ለብዙዎች ይሰራል እና በመቀጠልም ሌሎችን ከዚህ ችግር የምንታደግበትን መንገድ ብናስብ እና ብናሰላስልስ? ለዚህም በዚህ ድህረ-ገ የእረፍት ወይም ትርፍ ጊዜን መጠቀም አሁንኑ ተጫንና ከተራ ቁጥር 1-6 የተፃፉትን ሃሳቦች ደግመው ያንብቡ:: 

ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ በመረዳት ዛሬውኑ ወደ ተግባር ይገቡ ዘንድ ያስቡበት፡፡

ነገር ግን የውጭውን ጩኸት በመስማት እያማረርንም፣ እየፈራን፣ እየተሰቃየን ይሄው አምስት ዓመታት ኖረን አየነው፡፡ 

ምናልባት ተራችን ደርሶ እስከምንጠራ ድረስ ስለምን መንገዳችንን ቀይረን ወደ ራሳችን መመልከት አንጀምርም፡፡ 

ደግሞም አላወጣ ካለን ያኔ ወደ ነበርንበት መመለስ ቀላል ነውና እንመለሳለን፡፡ 

አለበለዚያ አሁን ባለው አካሄዳችን እየየ እያልን ለእኛም ለሌሎችም ሳንሆን እንዲሁም ከአምላካችን መንግገድ አፈንግጠን በየተራ ይሄው ሁለት ሞትን እየሞትን አለቅን፡፡ 

ማልቀስ ካለብንም በድብቅ ለእውነተኛው ዳኛ መንገር እንጅ እንዲሁ በመገናኛ-ብዙሃን እየፃፉ ሞት ምን ይሉታል?


አንዴ ቆም ብለህ አስብ፡-

ዛሬ አሁንኑ ልትተገብረው የምትችለው ከዚህ ጽሁፍ የተማርከው አንድ … ሁለት … ሶስት … ወዘተ ሃሳብ ምንድን ነው?  

ስላንድ ነገር ብዙ መረጃ መኖር ዕውቀት ነው፤ መረጃውን በተግባር መጠቀም ደግሞ ጥበብ ነው እና አሁንኑ በተግባር ግባ!

አስተያየት ተጨማሪ ሃሳብ እንዲሁም ጥያቄ ካላችሁ በዚሁ ድህረ-ገጽ ፃፉልን!