መነሻ ሃሳብ

ሃሣብ የነገሮች ሁሉ መነሻ ታላቅ ሃይል ነው:: እጅግ በጣም ደስ የሚለው ነገር ደግሞ ሃሣብ ለሁላችንም የሰው ልጆች በነፃ ያለ ምንም ክፍያ ከተቸሩን ትላልቅ ስጦታዎች አንዱ መሆኑ ነው። 

ዛሬ ላይ በአካል የምናያቸውም ይሁኑ ረቂቅ፣ ትልቅም ይሁኑ ትንሽ፣ ጠቃሚም ይሁኑ ጎጂ ነገሮች፣ ድርጅቶች፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምር ውጤቶች የመሳሰሉት ... ባጠቃላይ ማንኛውም በዚህ ዓለም ላይ ያሉ ነገሮች በሙሉ የሆነ ጊዜ በሰዎች አእምሮ ውስጥ ሃሳብ ነበሩ። ስለሆነም ሃሳብ የዚህን ያህል የነገሮች ሁሉ መነሻ ምንጭ የሆነ አስፈላጊ ሃይል ነው።

ለእያንዳንዳችን ሃሳብ የእግዚአብሔር የነፃ ስጦታ በምንም ቁሳዊ ነገር በገንዘብም ቢሆን የማይተመን ትልቁ ሃብታችን ነው፡፡ 

ነገር ግን ብዙዎቻቸን ለሃሳቦቻችን ብዙ ትኩረት አንሰጥም፡፡ ይሁን እንጅ ትኩረተ ሰጠነውም አልሰጠነውም የሁላችንም ዛሬ ላይ የምንኖረው እያንዳንዱ የህይወት ዘርፋችን (መንፈሳዊነታችን፣ ጤናችን፣ ግንኙነታችን፣ ቤተሰባችን፣ የምናገኘው የገንዘብን መጠን፣ የትምህርት ደረጃችን ... ወዘተ) ያለምንም ጥርጥር የሃሳባችን ውጤት ነው፡፡

ስለ ሃሳብ አስገራሚ የጥናት ውጤት መረጃዎች

ጥናቶች እንደሚያሳዩት አንድ መደበኛ ወይም አማካኝ ሰው በቀን በአማካኝ ከ60-70 ሺ ሃሳቦችን ያስባል፡፡ 

ይህም ሰው ከነዚህ በቀን ከሚያስባቸው 60-70 ሺ ሃሳቦች በአማካኝ 5% ሃሰቦቸን ብቻ ሆነ ብ የሚያስባቸው እና ስለሚያስባቸው ነገሮችም የሚያውቅ ሲሆን ቀሪውን 95% የሚሆነውን ከ60-70 ሺ ሃሳቦች ግን ሳያውቅ ስለሚያስባቸው ሃሳቦቹ ምን እንደሆኑ አያውቃቸውም፡፡ 

ከዚህም ጋር ተያይዞ አንድ መደበኛ ሰው በቀን ውስጥ ስለሚያደርጋቸው ነገሮች 5% ብቻ በንቁ አዕምሮው ስለሚያደርጋቸው እውቅና ሲኖረው ቀሪውን 95% ግን በድብቁ አዕምሮው በልማድ መልኩ ስለሚካሄዱ ሳያውቀው እና ሳያስበው የሚያደርገው ነው፡፡ 

አጠቃላይ ከምናስባቸው ሃሳቦች 98% የሚሆነው ተደጋጋሚ እና ልማድ የሆነውን ነገር ነው፡፡ በጣም አስደንጋጩ ነገር ደግሞ በአጠቃላይ ከምናስባቸው ሃሳቦች 80% የሚሆኑት አሉታዊ ናቸው ይላሉ ጥናቶች፡፡ 

ሃሣብን የሚያመነጨው የአእምሮ ክፍል ንቁ አእምሮ ሲሆን ይህ ሃሣብ በተደጋጋሚ በዚሁ የአእምሮ ክፍል ሲታሰብ ወደ ስሜትነት በመለውጥና ወደ ድብቁ አእምሮ በመግባት ለተፈጠረው ሰሜት ተመጣጣኝ የሆነ ድርጊት በስጋዊ አካላችን ድርጊት እንዲንወስድ ትዕዛዝ ይተላለፋል::

አስፈላውን ድርጊትም በስጋዊ አካላችን እንወስዳለን። በመሠረቱ ይህ በየቀኑ በእያንዳንዷ ቅፅበት ህይወት የሚከናወንበት ሂደት በአጭሩ ሲገለጽ ነው።

በአንድ ሰው አእምሮ ውስጥ ያለ ሃሳብ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በአንድ ሰው አእምሮ ውስጥ በአንድ ቅጽበት ወይም በተመሳሳይ አዎንታዊ እና አሉታዊ ሊኖሩ አይችሉም:: ከሁለት አንዱ ብቻ እንጂ:: ማለትም አዎንታዊ ወይም አሉታዊ።

ማንኛውም ሰው በህይወቱ ዘላቂ ስኬት ከፈለገ ከምንም በፊት የራሱን ሃሣብ ይዘትና ዓይነት በጥልቀት መገምገምና መረዳት እንዲሁም አስፈላጊውን የሃሣብ ማስተካከያ ማድረግ አለበት። 

ስለሆነም አንድ ሰው ሃሣቡን መገምገምና ማወቅ ማለት በአብዛኛው በቀን ተቀን ውሎው ውስጥ የሚያስበው ሃሣብ አዎንታዊ ነው ወይስ አሉታዊ፤ ስለምንስ ነው የሚያስበው የሚሉትን ጥያቄዎች መመለሰ ነው። 

ይህንንም የሚያደርገው ራሱን በተቻለ መጠን ጸጥ ባለ ቦታ በተመስጦ ወይም በአርምሞ በመሆን ማለትም ስጋዊ አካልን ዘና በማደረግና ጥልቅ ትንፈሳ ለጥቂት ሴኮንዶች በማድረግ ንቁ አእምሮውን በለሆሳስ እንዲሆን በማድረግ ወደ ውስጡ [ወደ ድብቁ አእምሮው] በጥልቀት በመግባት በውስጡ ያለው የሃሣቡ ይዘት ምን እንደሚመስል እና በአብዛኛው ስለምን እንደሚያስብ መረዳት ይችላል፡፡ 

በእርግጥ በዚህ ሂደት ሃሣብን ለማወቅ ለጀማሪ ሰው ከሳምንት ያላነሰ ተደጋጋሚ ልምምድ ይጠይቃል።

በዚህም መንገድ የሃሣቡን ይዘትና ዓይነት ከተረዳ በኋላ አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ እና የሚፈልገውን ማንኛውም መልካም ሃሣብ በንቁ አእምሮው በመምረጥ፣ በተደጋጋሚ በማሰብና ወደ ስሜት በመለወጥ ይህንን መልካም ሃሳብ ወደ ድብቁ አእምሮው በማስረጽ በስጋዊ አካሉ መልካሙን ሃሳብ የሚመጥን ድርጊት እንዲካሄድ በማድረግ መልካምን ውጤት ማግኘት ይችላል። ለዚህም ነው ሰው የዘራውን ያጭዳል፣ ያሰበውን ይፈጸማል የሚበለው።

ማንኛውም የህይወት ሁኔታ ላይ ያለ ሰው፣ ጎዳና ተዳደሪም ቢሆን ይህን የሃሣብ ሃያልነት ተረድቶ እና ከላይ በተጠቀሰው መንገድ ሃሣቡን በመገምገምና በማወቅ መቆጣጠርና የራሱንና የሚወደውን ሃሣብ ወደ አእምሮ ማስረጽ ከቻለ መቸም ወደ ኋላ ላይመለስ ለዘለቄታው ወደ ስኬት ጣሪያ ይገሰግሳል::


ማጠቃላያ፦

ውድ አንባቢየ ከዝርዝሩ እንደተረዳኸው የሃሣብ ሃይል በህይወትህ ትልቅ ቦታ አለውና በተቻለ መጠን ትኩረትህን ለቅጽበትም ቢሆን ከሃሳብህ አትንቀል::


ጥያቄ፣ አስተያየት፣ ተጨማሪ ሃሳብ ካለ በዚህ ድህረ-ገጽ ፃፉልን!


መልካም ንባብ