መነሻ ሃሳብ

የሰው ልጅ በዚህ ዘመን ከመቸውም በላይ በብዙ ውስብስብ ችግሮች ተተብትቦ ይገኛል፡፡ በጣም ጥት የዓለም ብልህ፣ ታጋሽ፣ እና ጥበበኛ ሰዎች ይህንን ውስብስብ ችግር በሚገባ እና በተረጋጋ መንፈስ በመረዳት ቤታቸውን ዘግተው በቅድሚያ ችግሩን ከራሳቸው ለማስወገድ አሊያም በችግሩ ውስጥ ሆነው የተሻለ ህይወት የሚኖሩበትን መላ እና ዘዴ ይቀምራሉ፡፡ 

በመቀጠልም ይህንን በህይወታቸው የገጠማቸውን ችግር ከእነ ተቀመረው መላ ወይም ዘዴያቸው ልክ እንደነሱ በችግሩ ለሚሰቃየው የዓለም ህዝብ እንካችሁ ይላሉ፡፡ በዚህም የዓለምን ህዝብ ቀልብ በመሳብ የፈለጉትን የህይወት ስኬት ይቀዳጃሉ፡፡ በዚህም ሂደት በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ በአንድ በኩል የራሳቸውን ችግር ይቀርፋሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎችን ከችግራቸው በመታደግ ቢዝነስ ይሰራሉ ማለት ነው፡፡

እኛስ ፈተናዎችችንን እንዴት ነው ምናያቸው?

በአንፃሩ ደግሞ ይህ ተመሳሳይ ውስብስብ ችግር ለብዙዎቻችን ከአቅማችን በላይ ነው በማለት አምነን እንቀበለዋለን፡፡ በዚህም የተነሳ ችግሩን እያማረርን እና አንዳንዴም ችግሩ ለማቃለል አሊያም የባሰ ችግር እንዳይገጥመን ትንሽ ትንሽ ሙከራዎችን በማድረግ እየታገልን እና እየተሳቀቅን እንኖራለን፡፡

በቅድሚያ መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር ሁሉም ቀላልም ሆኑ ከባድ ፈተናዎች መፍትሄ አላቸው፡፡ ልዩነቱ ብዙዎቻችን ችግሮቻችንን ከአቅማችን በላይ ናቸው በማለት አሜን ብለን እንቀበላቸዋለን፡፡ ጥቂቶቻችን ደግሞ ችግሮቻችንን በጥልቀት በመመርመር እና ሰዎችን በመጠየቅ፣ መጽሐፍን በማንበብ እና ሌሎችም ምጮች በማጣቀስ ለችግሮቻችን መፍትሄ የሚሆን ብልሃት፣ ዘዴ እና መላን እናዘጋጃለን፡፡

አንድ ሰው በህይወቱ የሚገጥሙትን ቀላልም ሆኑ ከባድ ፈተናዎች በጥልቀት በመመርመር እና ሰዎችን በመጠየቅ፣ መጽሐፍን በማንበብ እና ሌሎችም ምጮች በማጣቀስ ለችግሮቹ መፍትሄ የሚሆን ብልሃት፣ ዘዴ እና መላን ሲያዘጋጅ ሂደቱ በአንድ ድንጋይ ሁ ወፍ ነው፡፡

ይህንን ጽሁፍ በሚገባ ካነበብከው እና ከተረዳኸው በህወትህ የገጠሙህን እና የሚገጥሙህ ችግሮች ከመቅረፍ በዘለለ ችግሮችህን ወደ ቢዝነስ እንደምትቀይራቸው ፍንጭ ታገኛለህ እና በተመስጦ ማንበብህን ቀጥል ...

እሽ አሁን አእምሮህን ዘና እና ልብህን ክፍት አድርግና ልብ ብለኸው ላታውቅ የምትችው አንድ ከዚህ ቅጽበት ጀምሮ ስለቢዝነስ የነበረህን አስተሳሰብ የሚለውጥ ቁም ነገር ልንገርህ፡፡

አየህ ውድ አንባቢዬ መጽሐፍትን በማንበብ፣ የራስህን እና የሰዎችን የህይወት ተሞክሮ እና የተለያዩ ምንጮችን በመመርምር እና በማጥናት ያንተን የህይወት ችግሮች ከፈታህ ከላይ እንደተመለከትነው የሌሎችን ብዙ ሽ፣ ሚሊዮን እና ቢሊዮኖች ችግር ፈታህ ማለት አይደለምን?

ታዲያ ይህንን ስታደርግ ተጠቃሚነትህ እጥፍ ድርብ (ቢያንስ ሁለት መንገድ) ነው:-

አንደኛ ነገር የራስህን ችግሮች ለመቅረፍ ባደረከው ጥረት አሁን ያሉብህን ችግሮች ብቻ ሳይሆን ሌሎች ወደ ፊት ሊገጥሙህ የሚችሉ ችግሮችህን የመፍታት ክህሎት ባለቤት ሆንክ ማለት ነው:: ይህም ማለት ራስህን ስኬታማ ሰዎች ከሚኖራቸው አንዱ እና ዋናው ክህሎት የሆነው ችግርን በአግባቡ የመረዳት እና የመፍታት ክህሎት ኖረህ ማለት ነው፡፡

ሁለተኛው ነገር ደግሞ አንተን የገሙህ እና ወደ ፊትም የሚገጥሙህ ችግሮች የሌሎች ብዙ ሽ፣ ሚሊዮን እና ቢሊዮኖች ችግሮች ስለሚሆኑ ለሌሎች ተሞክሮህን በማጋራት ከችግራቸው የመታደግ ዕድል ይኖርሃል ማለት ነው፡፡

እንደሚታወቀው ይህንን ችግርን በአግባቡ የመረዳት እና የመፍታት ክህሎትህን ተጠቅመህ ልክ እንዳንተ ሁሉ ሌሎችንም ከችግራቸው ለመታደግ ብዙ መቶዎች እና ምናልባትም መንገዶች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል አሁን በዚህ ቅጽበት እኔ ላንተ ይሄንን ሃሳብ ያካፈልኩ ያለሁበት መንገድ (ድህረ-ገጽ) አንዱ ነው፡፡

የሌሎችን ችግር አቃለልክና ቀረፍክ ማለት ደግሞ በቀረፍከው ችግር እና ችግሩን በቀረፍክላቸው ሰዎች ቁጥር የተባዛ ህይወት ይኖርኻል ማለት አይደለምን? ስለሆነም በህይወትህ የሚገጥሙህን ችግሮች እንደመልካም አጋጣሚ መቁጠር መጀመር አለብህ፡፡ እንዲሁም ችግሮች የምትፈታባቸውን መንገዶች ልብ ብለህ ለሌሎች ችግር መፍቻ መሆን በሚችል መንገድ መቀመርህን አትርሳ፡፡

ስኬታማ ሰዎችስ ችግሮቻቸውን እንዴት ያዩቸዋል?

ለዚህም ነው በጣም ብዙ ጊዜ ልብ ብለህ ከሆነ የብዙ በዓለም አቀፍ ስኬታማ የሆኑ ሰዎችን የህይወት ስኬት ስትመለከት በአብዛኛው ከባድ ከሚባል የህይወት ዘርፎች ፈተና ውስጥ የነበሩ ናቸው፡፡ ከዚህም የተነሳ እኒህ ሰዎች በህይወታችው ፈተና ሲገጥማቸውም በመጀመሪያ በራቸውን ዘግተው የራሳቸውን ችግር ይፈታሉ፡፡ በመቀጠል ያንን ችግር ከነቀመረ መፍተሄው ይዘው ወደ ዓለም ህዝብ እንካችሁ ብለው ብቅ ይላሉ፡፡ የብዙ ስኬታማ ሰዎችን ንግግር እድምጠህ ከሆነ እና መጽሐፋቸውን አንብበህ ከሆነ በህይወታቸው ችግር በገጠማቸው ጊዜ ላድግ እንደሆነ አምናለሁ ይላሉ፡፡

ስለዚህ አንተም ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በህይወትህ አንድም ችግር ሲገጥምህ በመጀመሪያ አታማር:: ምክንያቱም አንደኛ ነገር አብዝተህ በስሜት ያማረርከው ነገር የበለጠ ይበዛል እንጅ አይቀንስም:: ሁለተኛው ነገር ደግሞ  እየሰራህ ያለኸው በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ነውና፡፡ በአጠቃላይ የጽሁፉን መልዕክት በጥሞና ተረድተህ ከሆነ ከዚህ በኋላ በህይወትህ የገጠመህን ችግር ለመቅረፍ የምታደርገው ውጣ-ውረድ ሊያስደስትህ እንጅ ሊያሰለችህ አይገባም፡፡

ይህንን ማድረግ ከቻልክ የራስህን ችግር ከመቅረፍ በዘለለ የሌሎችንም ችግር እየቀረፍክ መሆኑን ስታስብ ችግርህን መፍታት ማለት አንድም ራስህን ከችግር ታላቅቃለህ፣ በሌላም በኩል ቢዝነስ እየሰራህ ነው ማለት ነው፡፡ ለዚህም ነው የዘህን ጽሁፍ ርዕስ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ያልኩት፡፡


አንዴ ቆም ብለህ አስብ፡-

ዛሬ አሁንኑ ልትተገብረው የምትችለው ከዚህ ጽሁፍ የተማርከው አንድ … ሁለት … ሶስት … ወዘተ ሃሳብ ምንድን ነው?  

ስላንድ ነገር ብዙ መረጃ መኖር ዕውቀት ነው፤ መረጃውን በተግባር መጠቀም ደግሞ ጥበብ ነው እና አሁንኑ ወደ ተግባር ግባ!

 

አስተያየት ተጨማሪ ሃሳብ እንዲሁም ጥያቄ ካላችሁ በዚሁ ድህረ-ገጽ ፃፉልን!