ሁላችንም በህይወታችን ቆም ብለን ብናስብ ጠቅሰን የማንጨርሰው የምናመሰግንበት ብዙ የተደረገልን እና ያለን ነገር አለ፡፡

እንኳ ልብ ባንለው እና ባግባቡ ባንጠቀመው እስካሁን መሬት ላይ አለ የተባለ ምንም ዓይነት መሳሪያ የማይወዳደረው አእምሮን ያህል መሳሪያ የተሰጠው ሰው ምን ያህል ጊዜ እና በምን ቋንቋ ነው ይህንን ስጦታ የሚመጥን ምስጋና ሊያመሰግን የሚችለው?

እስኪ ልብ እንበል ያለምንም ክፍያ እንዲሁ በነፃ የሚሰጠንን ጊዜ፣ ጤና፣ ንጹህ አየር፣ የፀሐይ ብርሐን፣ ውሃእናንተም ጨምሩበት እና የተሰጠው ሰው ምን ያህል ጊዜ እና በምን ቋንቋ ነው ይህንን ስጦታ የሚመጥን ምስጋና ሊያመሰግን የሚችለው?

አሁንም እስኪ ልብ እንበል በተመጣጣኝ ክፍያ እና አንዳንዴም በነፃ የምገኛቸውን ለህይወት ወሳኝ የሆኑትን የዘመኑን የቴክኖሎች እና ሳይንሳዊ ውጤቶች ኢንተርኔት፣ መብራት፣ ስልክ፣ ዘመናዊ ትራንስፖርእናንተም ጨምሩበት እና የተሰጠው ሰው ምን ያህል ጊዜ እና በምን ቋንቋ ነው ይህንን ስጦታ የሚመጥን ምስጋና ሊያመሰግን የሚችለው?

ይሁን እንጅ እንዳለመታደልሆኖ ብዙዎቻችን ከሚደረግልን ብዙ ነገር ይልቅ የተደረገብን እንድ ወይም ጥቂት ነገር ላይ እናተኩራለን፡፡ እንዲሁም ካለን የእትየለሌ ነገር ይልቅ በሌለን አንድ ወይም ጥቂት ነገር ላይ እናተኩራለን፡፡ በዚህም ምክንያት በህይወታችን ከማመስገን ይልቅ ማማረር የህይወታችን ቀዳሚ ነገር ሆኖ እንኖራለን፡፡

አሳዛኙ እውነታ ባማረርን መጠን እና በላይ አንድም በህይወታችን የምናማርርባቸው ነገሮች የበለጠ ገዝፈው ይታዩናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሌላ የበለጠ ተጨማሪ የምናማርርበት ነገር ይጨመርልናል፡፡ ይህ ፍልስፍና ሳይሆን በህይወታችን በእያንዳንዱ ቀን የሚከሰት እውነታ ነው፡፡ ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ ሶስት ቀናት ህይወትህ እንዴት እየሰራ እንደሆነ ክትትል ብታደርግ የምትረዳው ግልጽ እውነታ ነው፡፡

አስደሳቹ ነገር ደግሞ ሰው አመስጋኝ ሲሆን አንድም ባመሰገነው ልክ እና ከዚያም በላይ በህይወቱ ልብ ብሏቸው የማያውቃቸው ሊያመሰግን የሚችልባቸው ነገሮች ስለሚታዩት የበለጠ አመስጋኝ ይሆናል፡፡ በሌላም በኩል ሌላ ተጨማሪ የሚያመሰግንባቸው ነገሮች ይጨመሩለታል፡፡ ከላይ እንዳልኩት ሁሉ ይህም ፍልስፍና አይደለም ግልጽ እውነታ ነው፡፡ ይህንንም ለመረዳት ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ ሶስት ቀናት በቀን ቢያንስ አንዴ ከቻልክ ሁለቴ አሊያም ሶስቴ በመደበኛ ሰዓት እና ቦታ በማመስገን በህይወትህ ምን ለውጥ እንደምታይ ሞክረው፡፡

ተጨማሪው አስደሳች ነገር ሰው ከፈለገ ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ ያሉትን ነገሮች እና የተደረጉለትን ነገሮች በማስታወስ ብቻ ሁሌም አመስጋኝ መሆን ይችላል፡፡ ይህ የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ ንያቱም ከላይ እንዳየነው ልብ ልነው ግን በምንም ያህል ጊዜ እና በምንም ቋንቋ ልንገልጸው የማንችለው ብዙ ነገር ተደርጎልናል፣ አለንም፡፡

  

በ2005 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሊሚኖሎጂ ቤተ-ሙከራ ውስጥ የላንጋኖን ሃይቅ ውሃ ጥራት በመመርመር ላይ (ለትውስታ)


እርግጥ ነው በህይወታችን ብዙ ነገር ተደሮጎብናል፣ ብዙ ነገርም የሌለን አለ፡፡ በመሆኑም ብዙ ነገር በተደረገብን እና ብዙ ነገር በሌለን መሰረት ማማረር እንችላለን በዚያም የበለጠ ይደረግብናል፣ ካለንም ይወሰድብናል፡፡ እንዲሁም ልብ ብለህ ከሆነ ብዙ ነገር በተደረገልን እና ብዙ ነገር ባለን መሰረት ማመስገን እንችላለን በዚያም የበለጠ ይደረግልናል፣ ይኖረንማል:: ስለዚህም ነው ሰው በህይወቱ ማማረር ሆነ ማመስገን የምርጫ ጉዳይ ነው ያልኩት፡፡ ስለዚህ ልብ ብለህ በማስተዋል የሚሆንህን ምረጥ፡፡ ማማረር ወይም ማመስገንን ...

እኔ በበኩሌ በተከታታይ ለ30 ቀናት በቀን አንድ ጊዜ በመደበኛ ሰዓት እና ቦታ የምስጋና ልምምድ ካደረኩ ጊዜ ጀምሮ በህይወቴ ከማማርርበት ይልቅ የማመሰግንበት በልጧል፡፡ አሁንም ድረስ የበለጠ የማመስግንባቸው ነገሮች በህይወቴ እየጨመሩ መጥተዋል፡፡ ለእኔ ከሰራ ለአንተም እንደሚሰራ አልጠራጠርም እና ዛሬውኑ ሞክረው፡፡ በማመስገን ብቻ የምታመጣውን አዎንታዊ የህይወት ለውጥ ውጤቱን በዚህ ደህረ-ገጽ ወይም በኢሜል ወይም በስልክ ወይም በአካል እንደምትነግረኝ እተማመናለሁ፡፡

በእውነት በነፃ ስለተሰጡህ ስለምትተነፍሰው ንጹህ አየር፣ የምትሻውን ታደርግ ዘንድ ስለ ተሰጠህ ጊዜ፣ ስላለህ ድንቅ አእምሮ፣ ስለ ፀሐይ ብርሃን፣ ስለ ውሃ ... አንተም ጨምርበት እና ልብ ብለህ እና አመስግነህ ታውቃለህ?

እንደ እኔ እንደ ድሮ ከሆንክ እየቀለድኩ ይመስልህ ይሆናል፡፡ እኔም ያኔ ሳይገባኝ ስለነዚህ ማመስገን እንለብን የሚያወራ ሰው ስሰማ ወይም መጽሐፍ ሳነብ እንደ ማካበድ እና እንደ መቀለድ ነበር የማየው፡፡ ነገር ግን ግልጽ የሚሆንልህ ከላይ ከተጠቀሱት እና ሌሎችም አንዱን፣ ሁለቱን ሶስቱን ... በህይወቴ ባይኖሩኝ ኖሮ ህወቴ ምን ይመስል ነበር ብለህ ራስህን ጠይቅ፡፡ 

ግልጽ ለማድረግ እንዲያው አያድርግብህ እና የሰይጣን ጆሮ ይደፈን እንጅ አስበው ንጹህ አየር ባይኖር (ሳንባህ ቢታመም) አእምሮ ባይኖርህ (አእምሮህን ነካ ቢያደርግህ) የፀሐይ ብርሃን ባይኖር (የአጥንት መልፈስፈስ በሽታ ቢያምህ) ወዘተ ኖሮ ብለህ ብታስብ ማን እና የትኛው ሆስፒታል ነው በነፃ የሚሰጥህ፡፡ 

እሽ ሆነ እንበልና ከእነዚህ ነገሮች በአንዱ፣ በሁለቱ፣ በሶስቱ … እጦት ወይም ህመም ተቸግረህ ሳለህ አንድ ሰው ወደ ሆስቲታሉ ወስዶ ነፃ እርዳታ ቢያደርግልህ ያንን ሰው ምን ያህል ታመሰግነዋለህ? እንደእኔ ከሆንክ መልሱ ግልጽ ነው

ታዲያ ከላይ የተጠቀሱትን እና ሌሎችንም ስጦታዎች በነፃ ያለምንም ጊዜ እና ቦታ ገደብ ለሰጠህ ለባለቤቱ (ለፈጣሪህ) ምን ያህል ጊዜ ልታመሰግነው ይገባል?

በእርግጥ ግልጽ እንዲሆንልህ ብታጣቸው ወይም ብትታመም ብየ ተነሳሁ እንጅ ስለነዚህ እና መሰል ነፃ ስጦታዎችህ ለመረዳት እና በየቅጽበቱ እና በየዕለቱ ለማመስገን የግድ እነሱን ማጣት ወይም መታመም የለብህም፡፡ ይልቁንም እነዚህ ነፃ ስጦታዎች ምን ያህል በህይወትህ ወሳኝ እንደሆኑ ጊዜ እና ትኩረትህን ሰጥተህ በዕለት በዕለ ማስታወስ ብቻ ነው የሚጠበቅብህ፡፡ ያኔ አለማመስገን አትችልም::

እጅግ በጣም የሚገርመው ደግሞ ስለተደረጉልህ እና ስላሉህ ነገሮች ማመስገን ስትጀምር ከዚህ በፊትም የነበሩህ ነገር ግን ልብ ብለኻቸው የማታውቃቸውን ነገሮች መታየታቸው ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ከዚህ በፊት በህይወትህ ያልነበሩህ ሌሎች ነገሮች እና ክስተቶች መጨመራቸው ሌላው አስደናቂው ነገር ነው፡፡ ለዚህም እግዚአብሔር በትንሹ ለታመነ በትልቁ እሾመዋለሁ ብሎ በሐዋርያቱ አማካኝነት ለሰዎች የገባልን ቃል ህያው ምስክር ነው፡፡ ይህ ማለትም በተደረገለት እና ባለው ትንሽ ነገር ያመሰገነ፣ ሌላ ብዙ ነገርን አደርግለታለሁ እሰጠውማለሁ እንደማለት፡፡ በእርግጥ ይህ ተቃራኒውም እንዲሁ ነው፡፡

ስለሆነም አሁንኑ ከዛሬ ጀምሮ ለሚቀጥሉት ሰባት ቀናት በተከታታይ የተደረጉልህን እና ያሉህን ነገሮች በወረቀት (የበለጠ ይመረጣል)፣ በስልክህ፣ አሊያም በላፕቶፕህ በመፃፍ ማመስገን ጀምር እና በህይወትህ ምን ለውጥ እንደምታመጣ አብረን እንመልከት ...


አንዴ ቆም ብለህ አስብ፡-

ዛሬ አሁንኑ ልትተገብረው የምትችለው ከዚህ ጽሁፍ የተማርከው አንድ … ሁለት … ሶስት … ወዘተ ሃሳብ ምንድን ነው?  

ስላንድ ነገር ብዙ መረጃ መኖር ዕውቀት ነው፤ መረጃውን በተግባር መጠቀም ደግሞ ጥበብ ነው እና አሁንኑ ወደ ተግባር ግባ!

 

አስተያየት ተጨማሪ ሃሳብ እንዲሁም ጥያቄ ካላችሁ በዚሁ ድህረ-ገጽ ፃፉልን!