መነሻ ሃሳብ
ብዙዎቻችን ስለሆነብን ነገር ሁሉ የእግዚአብሔርን ፍርድ በፍጥነት መምጣት አጥብቀን ስንሻ ፍርዱ ስለመዘግየቱ ግራ እንጋባለን፡፡ ይባስም ብሎ አምላክ ስለመኖሩ እንጠራጠራለን፡፡ ለመሆኑ ለጥያቂያችን መልስ ወይም ፍርድ ከእግዚአብሔር እንዴት እንደሚገኝ ልብ ብለን ይሆን? በእኔ አመለካከት ልብ ያልነው አይመስለኝም፡፡
አንድ ባሪያ ለሁለት ጌቶች ይገዛ ዘንድ አይቻለውም እንዲሉ ሰው ለአምላኩ አሊያም ለዲብሎስ ይገዛል እንጅ ለሁለቱ ይገዛ ዘንድ አይቻለውም፡፡ በዚህም ምላሽ የሚያገኘው በልቡ መዝገብ ካመነው እና ከተገዛለት እንጅ በአፉ ከለፈለፈው እና በአእምሮው ካሰበው አይደለም፡፡ በእውነት አሁን በዚህ ዘመን ብዙዎቻችን እያወቅንም ሆነ ሳናውቀው ለማን ነው እያመንን እና እየተገዛን ያለነው? ምላሽስ እያገኘን ያለነው ከማን ነው?
ማንን እያመንን፣ ለማን እየተገዛን እና ከማን መልስ እያገኘን እንደሆነ ለመረዳት ለጥያቄዎቻችን ምን ዓይነት መልስ እያገኘን እንዳለን አንዴ ቆም ብለን ብናስተውል ግልጽ ሆኖ ይታያል፡፡ ቀድሞ ነገር ተገቢ ጥያቄ ለተገቢው ዳኛ ስለማቅረባችን እኛ ብንሸፋፍነውም እርሱ ግን ያውቀዋል፡፡ እየሆነብን ያለው ነገርም የሚያሳየን እውነቱ ይኸው ነው፡፡ እየሆነብን ያለው ደግሞ ሐዋርያቱ በትምህርታቸው ሰው የዘራውን ያጭዳል እንዳሉ የስራችን ውጤት መሆኑን የማንክደው እና የማናስተባብለው ሃቅ ነው፡፡
ያኔ በአገር
አማን ለእግዚአብሔር የምንገዛ እና የእውነት ፍጹም አማኝ መስለን ማንነታችንን በጉያችን ደብቀን ስንኖር ሳለ ይሄው ዘሬ
የደበቅነው ማንነታችን ለዓለም በይፋ ወጣ፡፡ ዛሬ ላይ ይህ ኢ-አማኒ ማንነታችን የማንደብቀው የአደባባይ ሚስጥር ሆኖብናል፡፡
ስለምን ይመስላችኋል ባደባባይ እየሞትን ያለነው? ስለምንስ ነው የእግዚአብሔር ፍርድ የዘገየው? እግዚአብሔር ስለሌለ ወይስ ስለረሳን? ወይስ ፈተናዎቻችንን መፍታት ስላቃተው? ወይስ ዘመኑ ስለተቀየረ? ሁሉም ግምቶቻችንን ስህተት ናቸው፡፡ ባደባባይ እየሞትን ያለንበት እና የእግዚአብሔር ፍርድም የዘገየበት ዋናው እና ብቸናው ምክንያት እያመንን እና እየተገዛን ያለነው ለዲያብሎስ ስለሆነ ብቻ ነው:: ቀድሞ ነገርስ ለዚህ ሁሉ የአደባባይ ሞት የዳረገን ምን ሆነና፡፡
ይህን ሁሉ ዛሬ መሬት ላይ አለ የተባለ መከራ ደጋጎቹ ቅድመ አያቶቻችን በትንቢት፣ አያቶቻችን በምልክት እኛ አመጸኞች ደግሞ በተግባር እያየነው እና እየተጎነጨነው ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ መከራ እንወጣ ዘንድ ስለ እውነት እና በእውነት ለእግዚአብሔር እንድንታመን እና እንድንገዛ ይርዳን፡፡ ዛሬ ከዚሀ ቅጽበት ጀምሮ በእውነት በእርጋታ ራሳችንን እንጠይቅ፣ እንፈትሽም፡፡ ሰው ከገጠመው ፈተና በዘላቂነት የሚወጣው በጸሎቱ ወይስ በጉልበቱ፣ በእምነቱ ወይስ በድፍረቱ ብየ ብጠይቅ ምናልባትም ሁሉም ሰው መልሱን ከመመለስም ባሻገር ይህንን ጥያቄ በማቅረቤ የክህደ ጥያቄ ነው የሚሉ እና የሚሳድቡ ቀላል አይሆኑም፡፡ ዳሩ ግን ብዙዎቻችን ሳናውቀው በስህተት፤ ጥቂቶቻችን ደግሞ በማወቅ በድፍረት ክደናል፡፡
ብዙ መንፈሳዊ የምላቸው እህት እና ወንድሞቸ ያንን የጸሎት ጊዜ ወደ ኋላ ትተው አመፃን በአመፃ ለመፍታት በየመገናኛ-ብዙሃኑ የአመፃ ሃሳብን ሲጽፉ ሳይ በጣም አዘንኩ፡፡ ተስፋ ቆረጥኩስ አልልም በአምላኬ ሁሌም እስከ ህይወት ህቅታ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ስንቶቻችን በአምላካችን በልባችን አምነን በግብራችን እንገልጸዋለን?
ብዙዎቻችን አማኝነታችን በአፋችን እንጅ በልባችን እና በግብራችን ከሃዲዎች ሆነናል፡፡ ለዚህም የሚከተሉትን እንመልከት፡-
o በአፋችን ጠላቶቻችሁን እንደ ራሳችሁ ውደዱ ሚለውን ቃል በየቤተ እምነቶቻችን እንለፈልፋቸዋለን በልባችን መዝገብ እና በግብራችን ግን ይሄው ከወላጅ እና ቤተሰቦቻችን ጋር እንኳን መግባባት አቅቶን አንዳችን ሌላችን እየገደልን እንገናለን፡፡ ሌላው ቀርቶ ስንቶቻችን ነን ከሁሉም ቤተሰብ አባሎቻችን ጋር ተስማምተን እኖርን ያለነው? ይህ ማለት ደግሞ ሌሎችን ለማስተካከል ከመታተራችን በፊት ራሳችን ላይ ገና ያላስተካከልነው ትልቅ ነገር ያለ አይመስላችሁም?
o በአፋችን እግዚአብሔር ከጠላቶቻችን እጅ ነፃ ያወጣናል እንላለን በልባችን መዝገብ እና በግብራችን ግን ጠላቶቻችንን በራሳችን ኃይል በመሳሪያችን እና በቡድናችን ተጠቅመን ልናጠፋቸው ሌት ተቀን እንታትራለን፡፡
o በአፋችን እግዚአብሔር ከመከራ ስጋ ከመከራ ነፍስ ያድናል እንላለን፡፡ በልባችን መዝገብ እና በግብራችን የእረሱን ማዳን ረስተን በራሳችን ኃይል ልንድን ስንታተር እንውላለን እናድራለን፡፡
o በአፋችን የሰናፍጭ ያህል እምነት ቢኖረን ይህንን ተራራ ከዚህ ሂድ ብንለው ይሄድልናል እንላለን:: በልባችን መዝገብ እና በግብራችን ግን በሰላም ስለማደራችን እምነት ጎድሎን ጠፍተን ልናድር እንደምንችል በማሰብ እንቅልፍ አጥተን እናድራለን፡፡
o በአፋችን እግዚአብሔር ልብን እንጅ መልክን አያይም እንላለን:: በልባችን መዝገብ እና በግብራችን ግን ይሄው ልባችን ከማንፃት ይልቅ አካላችንን ብቻ በማስዋብ ሌሎችን በዝሙት መጣል ላይ ተጠምደናል፡፡
o ክህደቶቻችን ተዘርዝረው አያልቁምና ሌሎችንም እንጨምርበት እና እንገንዘብ …
ፈተናዎቻችንን እንዴት እንፍታ?
በቅድሚያ ልብ ልንለው የሚገባው ነገር እግዚአብሔር ፈተናዎች እና ችግሮች እንዳይገጥሙን ሳይሆን በፈተናዎች መካከል በእምነት ጸንተን፣ በትዕግስት እና በጥበብ የምናልፍበትን መንገድ ያሳየናል፡፡ ከቶ በእግዚአብሔር ጥላ ስር ሆኖ ያለ ሰው ሁሉ ከፈተናዎች በላይ ነው፡፡ ማንም ሰው የእግዚአብሔርን መንገድ ተከትሎ እና የእርሱን ረዳትነት በሙሉ ልብ በማመን ቢተጋ ማንኛውንም ፈተና ማሸነፍ ይችላል፡፡ ከአቅማችን በላይ የመሰለን ፈተና ቢኖር እንኳን ፈቃዱ ከሆነ ለእኛ እንደተራራ ገዝፎ የታየንን ፈተናና እና ችግር ከመቅጽበት ይፈታልናል፡፡
መስሎን እንጅ ቀድሞ ነገር ፈተናዎቻችንን የምንወጣውቸው በእርሱ ፈቃድ እና ከእርሱ በምናበገኘው ጥበብ፣ ትዕግስት እና ኃይል ነው፡፡ ምናልባት በፈተናው አላስፈላጊ መስዋዕትነት መክፈል ከሌለብን እርሱ የፈቀደውን ሁሉ ያደርጋል እንጅ እንዲሁ አይተወንም፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ግን የምናደረገው ሁሉ ጥረት የእግዚአብሄርን መንገድ መሰረት ያደረገ እና በእርሱ ረዳትነት እንጅ በእኛ ኃይል ብቻ እንዳልሆነ መረዳት ይኖርብናል፡፡
በዚህ መንገድ ሆነን የማንወጣው አንዳች ፈተና በዚህ ምድር የለም፡፡ ለዚህም የቅዱሳኑን ታሪክ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ሰው በአንበሳ ተይዞ፣ በውሃ ማዕበል ተወስዶ፣ በዘንዶ ተውጦ እና ከሌሎችም ማመን ከሚያስቸግሩ ፈተናዎች ወጥቷል፡፡ ስለሆነም እኛም ካለንበት ፈተና የማንወጣበት አንዳች ምክንት የለም:: ነገር ግን የቅድሚ ቅድሚ የእግዚአብሔርን መንገድ እና ፈቃድ መልህቅ በማድረግ ፈተናዎቻችንን ለመፍታት መትጋት ይኖርብናል፡፡
ከዚህ ውጭ በሆነ መንገድ የምናደርገው ማንኛውም እንቅስቃሴ ምን ያህል ዋጋ እያስከፈለን እንደሆነ ሁላችን አይተነዋል እያየነውም ነው፡፡ መጽሐፉ እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ ከተማ ጠባቂ በከንቱ ይደክማል አይደል የሚለው፡፡ ደግሞስ እናንት ሸክማችሁ የከበዳችሁ ወደ እኔ ኑ አለን እንጅ በራሳችሁ ወጥታችሁ ወርዳችሁ ፈተናችሁን ተወጡ አለን?
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ እኛ ቂሎች ፈተናዎቻችንን በመሳሪያ፣ በቡድን ወዘተ ለመፍታት እንዲሁ በከንቱ እንደክማለን:: እኔ በጣም ብዙ ጊዜ ግራ ይገባኛል፡፡ ይህ አባባል ለቀልድ ነው የተባለው ብለን ነው የምናምነው? ወይስ አባባሉ የሚሰራው ቀለል ላሉ ፈተናዎች ብቻ ነው ብለን ነው የምናምነው?
በእውነት በፍጹም እምነት ውስጥ ሆነን ለፈራጁ ዳኛ ብንነግረው ፈተናዎቻችንን አይፈታልንም?
ጠላት ዲብሎስ እንደሆነ ደም ማፍሰስ ግብሩ ነው፡፡ ይህንን ሲያደርግ ጠላት ድጋፍ የሚያገኘው ከሳጥናኤል ነው፡፡ እኛ ደግሞ እየገደሉንም ቢሆን ልብ ይሰጣቸው ዘንድ ስለጠላቶቻችን መጸለይ ግብራችን ነው፡፡ ይህንን ስናደርግ ድጋፍ የምናገኘው ከኃያሉ እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለዚህ ከሳጥናኤል እና ከእግዚአብሔር ማን ያሸንፍ ይሆን?
ዳሩ ግን ማን የሚታየውን ጊዚያዊ ፈተና ቻል አድርጎ በፍጹም እምነት ሆኖ በድብቅ ለሚገኘው ዳኛ አቤቱታ ያቅርብ? ይህንን እስካላደረግን ድረስ ምንም እንኳ አሁን ካለው ፈተና የወጣን ቢመስለንም ፈተናዎች ሁሉ መልካቸውን እየቀያየሩ ሲያታግሉን ይኖራሉ፡፡ ወዮልን ለእኛ ሁለት ሞትን ስለምንሞተው …
በእውነት እንዲህ እንደተራራ ለከበደን አሁናዊ ፈተና ዘላቂ መፍትሄ ማግኘት ካለብን አሁንም ራሳችንን በተመስጦ እንመርምርና ሁሉ ወደ ማይሳነው ዳኛ እናመልክት (በጸሎት፣ በጾም፣ በስግደት ...)፡፡ ይህንን ለማድረግ ዛሬም ሊረፍድ ይችላል እንጅ አልመሸም:: ቆም ብለን በማስተዋል አካሄዳችንን ሁሉ በእግዚያብሔር መንገድ እና የእርሱን ረዳትነት በፍጹም እምነት በመጠበቅ ይሆን ዘንድ ያድለን፡፡
የከበደንን ፈተና ለእግዚአብሔር በመስጠት እኛ በእርሱ አማካኝነት ስራ አስፈፃሚዎች መሆናችንን አንዘንጋ፡፡ የእግዚአብሔር ስራ አስፈፃሚ መሆን ማለት ደግሞ ምን እንደሆነ ይገባናል ብየ አምናለሁ፡፡ ይህንን እሳቤ መልህቅ አድርገን ከተንቀሳቀስን የትኛውም ዓይነት ግለሰባዊም ሆነ ሃገራዊ እንዲሁም ዓለማ አቀፋዊ ፈተናዎቻችን መካከል በጥበብ፣ በትዕግስት እና በማስተዋል እናልፋለን፡፡
የፈተናዎቻችን አፈታት ቅደም-ተከተል
በቅድሚያ
የራሳችንን ፈተናዎች ከፈታን የጋራ ፈተናዎቻቸንን መፍታት ቀላል ይሆናል፡፡ አለበለዚ የየራሳችንን ፈተናዎች ያልፈታን ግለሰቦች በቡድን ተሰባስበን የጋራ ፈተናዎችችንን ለመፍታት መሞከር ጋሪው ከፈረሱ የመቅደም ያህል መስሎ ይታየኛል፡፡
እንደእኔ አመለካከት በአሁኑ ሰዓት ትልቁ የሃገራችን እና የዓለም ፈተና የሆነው የራሳቸውን ግላለሰባዊ ፈተና ያልፈቱ ሰዎች በፖለቲካ፣ በመንግስተነት፣ በሃይማኖት ሰበብም ሳይቀር በመሰብሰብ የሌሎችን የጋራ ፈተናዎች እንፈታለን ብለው በሚያድርጉት አስተውሎት እና ልምድ የጎደለው አካሄድ ውጤት ይመስለኛል፡፡
ከምንም ነገር በፊት ዛሬ አሁንኑ ጀምረን ወደ ውስጣችን በመጓዝ የራሳችንን ፈተናዎች በሚገባ በመረዳት እንፍታ፡፡ እያንዳንዳችን በዚህ መንገድ የየግል ፈተናዎቻችንን ከፈታን በስተመጨረሻ የጋራ ፈተናዎችንን በቀላሉ መፍታት እንችላለን፡፡ በዚህም የተሻለ ማህበረሰብ ይፈጠራል፡፡ አሁን ዛሬውኑ አንድ ላይ በቡድን ተሰባስበን መስማማት እና የጋራ ፈተናዎችችንን መፍታት የግድ አይመስለኝም፡፡ በቅድሚያ እያንዳንዳችን የራሳችንን ፈተና መፍታት ከቻልን የጋራ ፈተናወቻችንን መፍታቱ በራሱ ጊዜ ለራሱ ሲል ይመጣል ብየ አምናለሁ፡፡
አስተያየት፣ ተጨማሪ ሃሳብ እንዲሁም ጥያቄ ካላችሁ በዚሁ ድህረ-ገጽ ፃፉልን!
0 አስተያየቶች