መነሻ ሃሳብ
እንደ
ወላጅ ወይም አሳዳጊ ማንም ሰው የልጆችን የአእምሮ አሰራር እና
የማንነት ግንባት ሂደት ማወቅ ይደር የማይባል ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ የልጆች አእምሮ አሰራር ከእኛ ከታላላቆች ለየት
የሚያደርገው ማንኛውንም ያዩትን እና የሰሙትን መረጃ እና የህይወት ተሞክሮ ያለምንም ማጣራት እንዲሁ ይቀበላል፡፡ በዚህም
ምክንያት ልጆች ፈሳሽ ማንነት አላቸው እንላለን፡፡ የልጆችን የአእምሮ
አሰራር እና የማንነት ግንባት ሂደት ማስረጃ ይሆኑ ዘንድ ጥቂት ንጽጽራዊ ሂደቶችን እንመልከት፡-
1. ልጆች ልክ በፈሳሽ ውስጥ የተከተተ ስፖንጅን ይመስላሉ፡፡ በፈሳሽ ውስጥ የተከተተ ስፖንጅ ፈሳሹ መርዛማም ይሁን መርዛማ የልሆነ ፈሳሹን በሚችለው መጠን ወደ ውስጡ ያስገቡታል፡፡ ልጆችም (በተለይ ከ8 ዓመት ዕድሚያቸው ወቅት) በቅርባቸው ካለው ሰው ያዩትን እና የሰሙትን ማንኛውንም መረጃ እና የህይወት ልምምድ (ጠቃሚም ይሁን ጎጂ) ያለምንም ማገናዘብ እና ክለሳ ወደ አእምሯቸው ያስገቡታል፣ ያሰርጹታልም፡፡
2. ልጆች በብርጭቆው ውስጥ የተቀመጠ ውሃን ይመስላሉ፡፡ የውሃው ቅርጽ በብርጭቆው ቅርጽ እንደሚወሰን ሁሉ የልጆችም ማንነት በቅርባቸው ባለው ሰው ማንነት ይወሰናል፡፡
3. ልጆች ልክ በሸክላ ሰሪ እጅ ያለን ሸክላ ይመስላሉ፡፡ በሸክላ ሰሪ እጅ ያለ ሸክላ የተፈለገውን ዓይነት የሸክላ ዕቃ መሆን ይችላል፡፡ የልጆችም ማንነት እንዲሁ በቅርባቸው ሆኖ በሚንከባከባቸው ሰው አያያዝ መሰረት የተፈለገውን ማንኛውም ሰው መሆን ይችላሉ፡፡
4. ልጆች ልክ እንደ መቅረጸ-ድምጽ እና መቅረጸ-ምስል መሳሪያን ይመስላሉ፡፡ መቅረጸ-ድምጽ እና መቅረጸ-ምስል መሳሪያ በአጠገቡ ያለውን ማንኛውም ድምጽ እና ፊትለፊቱ ያገኘውን ማንኛውም አካል ምስል (ጠቃሚም ይሁን ጎጂ) ይቀርፃል፡፡ ልጆም እንዲሁ በቅርባቸው ያለውን ሰው መረጃ እና የህይወት ተሞክሮ ያለምንም ማገናዘብ እንዳለ ወደ አእምሯቸው በማስገባት የህይወታችቸው አንድ አካል እና እምነት ያደርጉታል፡፡
5. ልጆች ልክ እንደ ንጹህ ነጭ ወረቀት ይመስላሉ፡፡ ንጹህ ነጭ ወረቀት በማንኛውም ሰው የተፃፈን ወይም የተሳለን ማንኛውንም ጽሑፋዊ፣ ምልክታዊ ወይም ምስላዊ መረጃ ምንም ይሁን ምን (ጠቃሚ ወይም አደገኛ) የቀበላል። በተመሳሳይ በልጆች አካባቢ ያለ ማንኛውም ሰው የራሱን የህይወት ልምድ (ጠቃሚ ወይም ጎጂ) ወደ ልጆች ማስተጋባት ይችላል።
እነዚህ ንጽጽራዊ ሂደቶች ምን ያስተምሩናል?
እነዚህ የልጆች ምንም ማገናዘብ የሌለው የሌሎችን ማንነት መውሰድ ወይም መቅዳት ለእኛ ለወላጆች ወይም አሳዳጊዎች በልጆች አስተዳደጋችን ሂደት
ውስጥ ትልቅ ተግባራዊ ጠቀሜታ አለው፡፡ በቅድሚያ ማወቅ ያለብን ነገር ይህ ከፍተኛ የሆነ የልጆች የሌሎችን ማንነት የመቅዳት አደጋው ልክ ዕድሚያቸው አድጎ የራሳቸውን ህይወት መኖር ሲጀምሩ ማንኛውንም በህይወታቸው የሚገጥማቸውን ክስተት ሁሉ ለመስራት ላለመስራት፣ ለመወሰን ላለመወሰን እንዲሁም ለመተቸት እንደ ማጣቀሻ የሚጠቀሙት ያኔ በህፃንነታቸው በቅርብ ከነበረው ሰው በቀዱት መረጃ እና የህይወት ተሞክሮ መሰረት ነው፡፡ በዚህም ሂደት ውስጥ በቅርባቸው የነበሩት ሰዎች ህይወታቸው ያልተስተካከሉ እና ያልተገቡ ሃሰቦችን የሚናገሩ እንዲሁም ያልተገቡ ስራዎችን የሚሰራ ቢሆኑ በነዚያ ሰዎች አጠገብ ሆነው ያደጉ ልጆች ህይወት ምን ሊመስል እንደሚችል አስቡት፡፡ ከዚህ ባሻገር ከላይ የተገለጹት ንጽጽራዊ ሂደቶች በጥልቅ እንደሚሳዩን
በልጆች አጠገብ ያለን ማናችንም የማናደርገውንና የማንናገረውን ሁሉ ምን ያህል መጠንቀቅ ያለብን እንድሆነ ነው፡፡ በዚህም የወላጅነት ወይም አሳዳጊነት ኃላፊነት ከምናስበው በላይ እጅግ በጣም ትልቅ መሆኑን እንረዳለን፡፡
![]() |
| የአበባ ስጦታ ለልጀ ሀሰሴት አለባቸው የ5 ሴኮንድን ህግ ጠዋት ከእንቅልፏ ለመነሳት በተከታታይ ለአንድ ወር በትጋት ስለመተግበሯ |
ይህንን የወላጅነት ከባድ ኃላፊነት በመገንዘብ እኛ እንደ ወላጅ፡-
ለልጆቻችን መልካም ስዕብና እና የራሳቸውን ፈጠራ አውጥተው መጠቀም ይችሉ ዘንድ በቤታችን ውስጥ ቴሌቪዥን መክፈት ካቆምን አንድ ዓመት ከግማሽ በላይ ሆኖናል፡፡
ልጆቻችን ከጓደኞቻቸው እና ከሌሎችም ሰዎች የሚሰሟቸውን እና የሚያዩዋቸውን መረጃዎች እንዲሁም የህይወት ልምምዶች በጥንቃቄ በመገንዘብ የሚሆናቸውን እንዲቀስሙ፣ የማይሆናቸውን እንዳይዙ ባገኘነው ሁሉ አጋጣሚ ዘወትር እናስገነዝባቸዋለን፡፡
በቤት ውስጥም እንደ ወላጅነታችን በቻልነው መጠን ተግባብተን እና ተስማምተን ለመኖር ዘወትር እንለማመዳለን፡፡ ከልምምዳችን በላይ የሆኑ የሚያነጋግሩን ጉዳዮች ካሉ ደግሞ በተቻለ መጠን ጉዳያችንን ብቻችን በመነጋገር እንፈታለን፡፡
እንደወላጅ ወይም አሳዳጊ እናንተ ለልጆቻችሁ የወደፊት የተሳካ ህይወት ስትሉ ምን እያደረጋችሁ ነው?
ወደ ፊትስ ምን ልታደርጉ አስባችኋል?
ተሞክሯችሁን አካፍሉን …
አስተያየት ተጨማሪ ሃሳብ እንዲሁም ጥያቄ ካልህ በዚሁ ድህረ-ገጽ ፃፉልን!

0 አስተያየቶች