የመነሻ ሃሳብ

የሰው ልጅ በቀን 60-70 የተለያዩ ሃሳቦችን በአእምሮው ያመላልሳል፡፡ ነገር ግን ለብዙዎቻችን እነዚህ ሃሳቦች ብዙዎቹ (›80%) በላይ የሚሆኑት ተደጋጋሚ እና አሉታዊ ናቸው፡፡ እንደዚሁም ከእነዚህ ሳቦች በጣም ብዙዎቹን (›95%) በላይ የሚሆኑትን ሳቦች ምን እንደሆኑ እና ከየት እንደመጡ እውቅና የለንም፡፡ እነዚህ ሁሉ ሃሳቦች በአንድ ወይም በጥቂት አዎንታዊ ነገሮች ላይ ብቻ ቢያርፉ ተዓምር እንደሚሰሩ ግልጽ ነው፡፡ ይሁን እንጅ በዚህ ዘመን ከመቸውም በላይ የመረጃ፣ የአዳዲስ አሳዛኝ እና አስደንጋጭ ወቅታዊ ነገሮች፣ ጥሩ እና ጥሩ ያልሆኑ የአማራጮች መብዛት ትኩረታችንን በአንድ ወይም በጥቂት ነገሮች ላይ እንዳናደርግ ትልቅ የህይወት ፈተና ሆነውናል፡፡ በመሆኑም በዚህ ዘመን በአንድ ወይም በጥቂት ነገሮች ላይ የማተኮር ክህሎት እንደመኖር ወሳኝ ነገር የለም፡፡

ትኩረት ምንድን ነው?

ትኩረት ማለት ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚመጡ ብዙ ጥሩ አማራጮችን ቢሆን ሆነ ብሎ በመተው ይልቁንም አሁን በዚህ ቅጽበት እና ወደ ፊትም እኛ በምንፈልጋቸው ለህይወታችን በሚያስፈልጉ ነገሮች ላይ ብቻ ሃሳባችንን እና ስሜታችንን አሁን ከዚህ ቅጽበት ጀምሮ አነዚሁ ላይ ማሳረፍ፣ ማድረግ ማለት ነው፡፡

ትኩረት ሃይል ነው፡፡ ይህም ሃይል በአንድ ወይም በጥቂት እና አዎንታዊ ነገሮች ላይ ሲያርፍ ያንን አንድ ወይም ጥቂት ነገር እስከ ቂያኖስ ጥልቀት ድረስ የመረዳት ዕድል ይሰጠናል፡፡ ትኩረት ልናደርግበት የፈለግነው ነገር የሚሰራ ተግባር ከሆነም ተግባሩን ማንም አማካኝ ሰው ሊሰራው ከሚችለው ደረጃ በላይ የመስራት ዕድልን ያጎናጽፈና፡፡

ብዙ ዕድሎችን እና አጋጣሚዎችን የማሳደድ አደጋ

በዚህ ዘመን ብዙዎቻቻን ብዙ ነገሮችን መሞከር እንዳለብን እና ዕድሎቻችንን እና አጋጣሚዎቻችንን ማስፋት እንዳለብን እናስባለን፣ እናምናለን እንተገብራለንም፡፡ በዚህም የተነሳ ትኩረቶቻችን በብዙ ወቅት በወለዳቸው ነገሮች ላይ ይበታተናል፡፡ ትኩረትን በብዙ ነገሮች ላይ ሚያደርግ ሰው አስር ኳሶችን በአንድ ጊዜ ወደ ሰማይ ወርውሮ በተመሳሳይ ጊዜ አስሩንም ኳሶች በእጁ ለመቅለብ የሚሞከርን ሰው ይመስላል፡፡ ይህንን ሊያደርግ የሞከረ ሰው አንድም ኳስ ሳይዝ ሁሉም ኳሶች በየአቅጣጫቸው ይወድቃሉ፡፡ ትኩረቱን በብዙ ነገሮች ላይ የደረገ ሰውም ባተኩረባቸው ብዙ ነገሮች ላይ ጥቂት ጥቂት ነገሮችን ሊያገኝ ይችላል፡፡ መቸም ቢሆን የሚገባውን ያህል ግን አያገኝም፡፡ 

እናም በዚህ ዘመን ከመቸውም በላይ አንድ ወይም ጥቂት ነገሮች ላይ ብቻ በማተኮር ጥልቀት ያለው ሃሳብ፣ አሰራር፣ ዘዴ መፍጠር የማንኛችንም የህይወት ስኬት የግዴታ ውዴታ ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙ ተራ እና የተለመዱ አሰራሮች እና ክንውኖች በተቀላጠፈ እና በአጭር ጊዜ ውስጥ በሮቦቶች እየተሰሩ ስለሆነ የተለመደ እና ተራ አሰራርን በሰዎች ማሰራት ቀርቷል፡፡ይልቁንም የሰው ልጅ የዚህ ዘመን ትልቁ ትኩረት መሆን ያለበት የዘመኑ ሮቦቶች የማይሰሩትን አንድ ወይም ጥቂት ነገር ላይ በማተኮር ተደርጎ የማያውቅ ጥልቀት ያለው አሰራር፣ መንገድ፣ ልማድ፣ ክህሎት፣ ጥበብ፣ ምግባር፣ አስተሳሰብ ወዘተ መፍጠር ነው፡፡በአንድ ወይም በጥቂት ነገሮች ላይ የማተኮር ክህሎት ሲጀመር ለጊዜው ሂደቱ ከበድ ያለ ቢመስልም ውጤቱ እጅግ አመርቂ እና ዘላቂ ነው:: በመሆኑም ትኩረት የማድረግ ክህሎታችን አሁንኑ ከዛሬ ጀምረን በአንድ ወይም በጥቂት ነገሮች ላይ የማድረግ ልምምድ እንጀምር፡፡

ትኩረትን እንዴት እናዳብር?

በአሁኑ ሰዓት በተጨባጭ ዓለምን በሳይንስም፣ በቴክኖሎጂም ሆነ በአኗኗር ዘይቤ እየመሩ ያሉ እንደነ ቢልጌት፣ ጄፍ ቤዞስ፣ ጥቂት ሰዎች የመጀመሪያ ከብዙ የዓለም ህዝብ ልዩ የሚያደርጋቸው ክህሎት ይህ በአንድ ወይም በጥቂት ነገር ላይ የማተኮር ክህሎታቸው ነው፡፡ እጅግ በጣም ደስ የሚለው ዜና ግን ማንም በአንድ ወይም በጥቂት ነገር ላይ የምር ማተኮር የፈለገ ሰው ይህንን አንድ ወይም ጥቂት ነገሮች ላይ ማተኮር ክህሎት በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ማዳበር ይችላል፡፡ አንድ ወይም ጥቂት ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደማንኛውም ክህሎት በተደጋጋሚ ልምምድ መዳበር ይችላልና፡፡

ትኩረትን በምዕናብ እይታ ማጠንከር

የትኩረት ክህሎት ልምምድ በምዕናባዊ እይታ ሲታጀብ የትኩረት ክህሎትን የበለጠ በፍጥነት በህይወታችን እውን ይሆናል፡፡ ይህ ማለትም በቅድሚያ ትኩረት ልናደርግበት የፈለግነውን ነገር በምንፈልገው መልኩ ተጠናቆ ምን እንደሚመስል በምዕናብ ማየት እና ስሜቱ ምን እንደሚመስል በግልጽ በአእምሯችን ምስል መፍጠር እስከመቻል ድረስ መረዳት ማለት ነው፡፡ ይህ ምዕናባዊ ልምምድ ብቻውን የፈለግነው ነገር ላይ የበለጠ እንድናተኩር በእጅጉ ይረዳናል፡፡ ይህንን ለመረዳት ለምሳሌ ነገ አርብ ከቀኑ 9 ሰዓት በስራ ቦታው ስራውን በሚገባ እያከናወነ ለተገኘ ማንኛውም ሰው ሃምሳ ብር ይለገሳል የሚል መረጃ ዛሬ ሐሙስ ዕለት ላይ ሆነህ ሰማህ እንበል፡፡ ስለዚህ ዛሬ ሐሙስ ከዚህ ቅጽበት ጀምሮ ምን ታደርጋለህ? ትኩረትህስ ምን ላይ ይሆናል? መልሱን ለራስህ ልተወው እና ትኩረት ልናደርግበት የፈለግነውን ነገር ወይም ተግባር በዚህ ደረጃ ግልጽ እና ምስል ፈጣሪ ስናደረገው አለማተኮር አንችልም፡፡

ከዚህ ውጭ በሆነ መንገድ የምናደርገው ሁሉ ትኩረት ጊዚያዊ እና ሁሌ በጥረት እና በተጋድሎ የተመሰረተ ይሆናል፡፡ ንያቱም ለአእምሯችን ቀድሞ በማያውቀው እና በማያስደስተው እንግዳ ነገር ላይ እንደማተኮር ትልቅ ፈተና የለም፡፡ ለዚህም ነው አንድ ህይወታችንን ሆኖ በማያውቅ መንገድ እንደሚቀይረው ጠንቅቀን የምናውቀውን ወሳኝ ስራ በስተጀርባ አስቀምጠን እዚህ ግባ የማይባል የመገናኛ-ብዚሃኖች ላይ አፍጥጠን የምውለው፡፡

የትኩረት ግንባታ ሂደት ተጨባጭ ምሳሌ

ለምሳሌ አንድ የመመረቂያ ምርምሩን እየሰራ እና እየፃፈ ያለ ሰው ቢኖር የመመረቂያ ምርምሩን እንዴት በስኬት እያስኬደው እንዳለ፣ የሚያገኛቸው ውጤቶች ምን ያህል የሰዎችን ቀልብ እንደሚስቡ እና የመመረቂያ ምርምር ውጤቶቹንም ለሚመለከታቸው (ለአማካሪ፣ ለውስጥ እና ውጭ ገምጋሚ፣ ለገንዘብ ደጋፊ፣ ለሌሎች) ሲያቀርብ ምን ያህል በምርምሩ ውጤቶች እንደተደመሙ ሳይቀር ቁልጭ ያለ ምሰል ፈጣሪ ሃሳብ በአእምሮው መሳል መለማመድ አለበት፡፡ ይህንንም የፈለግነው ተግባር በስኬት ተጠናቆ ማየት ስሜቱ ምን እንደሚመስል የበለጠ እና በፍጥነት በአእምሯችን ምስል የመፍጠር ሂደቱን ለማፋጠን በወረቀት ላይ እየፃፍን ልንለማመድ እንችላለን፡፡

ይህንን ምዕናባዊ እይታ ልምምድ ማድረግ በጀመረ በሳምንት ጊዜ ውስጥ ሃሳቦቹ እና ስሜቶቹ ሁሉ በዚያ ምርምር ላይ ሆነው ያገኛቸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ይህንን የምርምር ስራ እና ጽሁፍ በመታገል እና በማማረር ሳይሆን እነዚያን ምዕናባዊ ውጤቶች በአእምሮው እያመላለሰ በደስታ እና በጉጉት መስራት ይጀምራል፡፡ ቀድሞ ነገርስ የሚፈለገው ይህ እማይደል? ለዚህም ነው ሰው በህይወቱ ስኬታማ የሚሆነው በመታገል፣ በመውጣት በመውረድ ደም፣ ላብ፣ ወዝ በማፍሰስ ሳይሆን ሳይሆን በብልሃት እና በጥበብ ነው የሚባለው፡፡ ደግሞም ህይወት ደስ የሚል ጨዋታ መሆን አለባት የሚባለው ለዚሁ ነው፡፡

አንዴ ቆም ብለህ አስብ፡-

ዛሬ አሁንኑ ልትተገብረው የምትችለው ከዚህ ጽሁፍ የተማርከው አንድ … ሁለት … ሶስት … ወዘተ ሃሳብ ምንድን ነው?  

ስላንድ ነገር ብዙ መረጃ መኖር ዕውቀት ነው፤ መረጃውን በተግባር መጠቀም ደግሞ ጥበብ ነው እና አሁንኑ ወደ ተግባር ግባ!

በጽሁፉ ላይ ተጨማሪ ሃሳብ፣ አስተያየት፣ ጥያቄ ካለ መነጋገር መርሃችን ነው፡፡

ጽሁፉ ይጠቅማል ብለው ካሰቡ ለሌሎች ያጋሩ፡፡