መነሻ ሃሳብ
እንደኔ ከሆንክ በመደበኛ ሁኔታ ለማንበብ ብዙ ጊዜ ለራስህ ቃል እንደገባህ እና ለማንበብ እንደሞከርክ፣ ነገር ግን ብዙ ጊዜ መዝለቅ አቅቶህ ያውቃል። ይሁን እንጅ ያን ጊዜ አላደረከውም ማለት ከዛሬ ጀምሮ አታደርገውም ማለት አይደለም እና ተስፋ አትቁረጥ፡፡ በነገራችን ላይ መደበኛ የማንበብ ልማድ ስል ለማለት የፈለኩት መሻሻል በምትፈልገው የማንነት እና የህይወት ዘርፎችህ እንዲሁም በህይወትህ ወሳኝ የምትላቸውን ጥያቄዎችህ ላይ የተፃፉ ጽሁፎችን እና መጽሐፍትን ዘወትር በተመሳሳይ ጊዜ እና ሰዓት ማንበብን ማለቴ ነው፡፡
አለበለዚያ ለየዕለት ተዕለት ተግባሮችህ ወይም ለስራህ ስትል የምታነበው ንባብ እንዲሁ ማንኛውም ሰው የተለመደ ስራውን ከመስራት የተለየ አይደልም:: ይህ ዓይነት ንባብ በአብዛኛው የተለመደ ስራህን በየዕለቱ ከመስራት የዘለለ የትም አያደርስም፡፡ ቢሆን ኖሮማ የታላላቅ ድርጅቶች እና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ዜና አንባቢ ሁሉም ጋዜጠኞች በዓለም አንደኛ አንባቢ እና ስኬታማ ተብለው በጂነስ ቡክ በተመዘገቡ ነበር፡፡
እኔም በበኩሌ ዛሬ ላይ ያለኝን መደበኛ የየቀን የማንበብ ልማድ ለመገንባት በጣም ብዙ ሞክሬ ብዙ ወድቄ ነው ያገኘሁት፡፡ እናም አሁን በዚህ አጋጣሚ እኔ መደበኛ የማንበብ ልማዴን ለመገንባት የተጠቀምኩባቸውን መንገዶች እንደሚከተለው ላካፍልህ። በመሆኑም አንተም እንደሚከተለው የተገለጹትን መንገዶች በመከተል በሚቀጥሉት 30 ቀናት ውስጥ ተመሳሳይ እና የበለጠ መደበኛ የማንበብ ልማድ እንደምታዳብር እተማመናለሁ፡፡
1. ምን ማንበብ እንዳለብዎ በጥንቃቄ ይምረጡ
መደበኛ የንባብ ልማድ ለማዳበር እኔ ያደረኩት እንዲዚህ ነው፡፡ በመጀመሪያ ላሻሽለው የምፈልጋቸውን የህይወት እና የማንነት ዘርፎች መረጥኩ፡፡ እንዲሁም ለእኔ በወቅቱ አንድ ህይወቴን ዛሬ ላይ ወደለሁበት ያመጣኝ ጥያቄ ነበረኝ፡፡ በመቀጠልም ወደ መጽሐፍት መደብሮች በመሄድ እንዲሁም ከጉግል በመግባት በመረጥኳቸው የህይወት እና የማንነት ዘርፎች እና በነበረኝ ጥያቄ ላይ የሚያትቱ መጽሐፍትን እና ጽሁፎችን በመጠቀም መደበኛ የማንበብ ልምምዴን ጀመርኩ፡፡ አንተም ይህንን መንገድ ተከትለህ የምትፈልጋቸውን ጽሁፎች ወይም መጽሐፍትን መምረጥ ትችላለህ። ይህ የሚሆንህን ጽሁፍ ወይም መጽሐፍ መርጦ ማግኘት የመጀመሪው ወሳኝ ሂደት ነው፡፡
2. ለአጭር ጊዜ ብቻ በማንበብ ይጀምሩ
እኔ በመጀመሪያ ለ10 ደቂቃ ብቻ በማንበብ ነበር የጀመርኩት፡፡ በየሳምንቱ ቀስ በቀስ ጥቂት ጥቂት ደቂቃዎች በመጨመር ዛሬ ላይ በቀን ቢያንስ ለ45 ደቂቃዎች የማንበብ ልማድ አዳብሪያለሁ። ነገር ግን ብዙዎቻችን የምንሳሳተው አንድ ቀን የማንበብ ፍላጎት በመጣልን ጊዜ ለሰዓታት እናነብ እና ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በማናውቀው መንገድ ማንበብ የሚባል ነገር እንጠላለን፡፡ ይህ በራሳችን አእምሮ ሴራ ስለሚሰራብን ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ትልቁ የስኬት ቁልፍ ያችን አጭር የማንበብ ጊዜ ማስቀጠል ነው፡፡
3. በመደበኛ ጊዜ እና ቦታ ያንብቡ
እንግዲህ እዚህ ጋ መታወቅ ያለበት አንድ ሃቅ እያንዳንዳችን የማንበብ ፍላጎት የሚኖረን በተለያየ ጊዜ እና ቦታ ሊሆን ይችላል፡፡ የምናነብበት ጊዜ እና ቦታ ይለያይ እንጅ በአጠቃላይ ግን ይህንን መደበኛ የማንበብ ልምምድ ተመሳሳይ ጊዜ እና ቦታ መተግበር ልማዱን ለመገንባት የበለጠ ውጤታማ ያደርገዋል፡፡ እኔ በበኩሌ ከሌሊቱ 10፡00 ሰዓት ሁሌም በተመሳሳይ የማንበቢያ እና መፃፊያ ጠረጴዛየ ላይ በማንበብ ነበር የጀመርኩት፣ አሁንም እንዲሁ፡፡
4. የንባብ ልምምድዎን ሂደት ቀላል ያድርጉ
መደበኛ የማንበብ ልማድ ለሌለው ሰው ሊያነብ በተነሳበት ወይም በወሰነበት ቅጽበጽ ለማንበብ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ማለትም መፅሐፍ፣ እስክሪብቶ፣ ማስታወሻ ደብተር፣ ቀለም፣ እርሳስ በማንበቢያ ጠረጴዛው ላይ በቀላሉ ካላገኛቸው እነዚያን ነገሮች ከያሉበት ፈልጎ አምጥቶ ማንበብ መጀመር ለእርሱ ትልቅ ስራ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ወዳላቀደው ሌላ በቀላሉ ወደ ሚያገኘው ክንውን ለምሳሌ ተንቀሳቃሽ ስልኩ ላይ ወደ መገናኛ ብዙሃን በመግባትና በመጎርጎር ጊዜውን ሊያባክን ይችላል፡፡ በዚህም ጊዜ ጭራሽ ሌላ ያልተፈለገ ልማድን ያዳብራል፡፡ ራሱን ባላቀደው ክንውን ባገኘ ጊዜም ምነው በሰላም ተኝቸ ባደርኩ ሲል ይጸጸታል፡፡ ስለዚህ እጅግ ጥብቅ የሆነ ራስን መቆጣጠር ይፈልገል፡፡
እኔም በበኩሌ ይህንን በጣም ብዙ አድርጌው አውቃለሁ፡፡ ትልቁም ፈተናየ ነበር፡፡ ለዚህም እንደመፍተሄ ያደረኩት ከመተኛቴ በፊት የማነበውን መጽሐፍ እና ለማንበብ የምጠቀማቸውን ነገሮች በማንበቢያ ጠረጴዛየ ላይ አደርጋለሁ፡፡ ሌላው የራሴ መመሪያ ደግሞ በዚህ በማነብበት ሰዓት ስልኬን በምንም አይነት መንገድ ከማነብበት ጠረጴዛ ላይ አላስቀምጥም፡፡ እናንተም ተመሳሳይ ወይም ሌላ ለእናንተ የሚሰራ መንገድ እንደትከተሉ እመክራችኋለሁ፡፡
6. ምናባዊ ልምምድ ማድረግ
በመሰረቱ አዲስ ልማድ በምንመሰርትበት ጊዜ በምዕናብ ያ ልንገነባው የፈለግው ልማድ (ማንበብ) የራሳችን ቢሆን ህይወታችን ምን ሊመስል እንደሚችል በአይነ-ህሊና ማየት እና ስሜቱን መረዳት መለማመድ ያንን ልማድ በፍጥነት እንድንለምደው ያደርጋል። ምክንያቱም ይህን የምዕናብ እይታ ልምምድ ስናደርግ፣ ያንን ልንለምደው የፈለግነውን ነገር (ንባብ) ወደ ድብቁ አእምሮአችን እንመዘግበዋለን። በዚህም ያንን ልማድ ልምምድ ለማድረግ እና ለመገንባት ውስጣዊ መነሳሳት ይኖረናል።
7. ለፈተና ይዘጋጁ
እንግዲህ እንደሚታወቀው እንድን አላስፈላጊ የለመድነው ልማድ (ማጨስ፣ መጠጣት፣ መሴሰን …) ከህይወታችን ለማስወገድ እንዲሁም አዲስ የምንፈልገውን ልማድ (ማንበብ፣ አካል ብቃ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ በጠዋት ከእንቅልፍ መነሳት …) እንደመፃፉ ቀላል አይደለም፡፡ ምክንቱም ምንጊዜም ቢሆን ወደን ሳይሆን ሳናውቀው በድብቁ አእምሯችን ተገደን በለመድነው ልማድ የመቀጠል ከፍተኛ የሆነ ውስጣዊ ዝንባሌ አለን፡፡
አንድ ለዓመታት አንብቦ፣ የአካል ብቃ እንቅስቃሴ ሰርቶ፣ በጠዋት ከእንቅልፉ ተነስቶ … የማያውቅን ሰው ዛሬ ብድግ ብለን የተጠቀሱትን በመደበኛነት እናድርግ እናድርግ ማለት አንድን ወትድርና ያልሰለጠነን ሰው ጦር ሜዳ ላይ አሁንኑ እንዲዋጋ እንደመሞከር ቁጠሩት፡፡ ስለዚህ መደበኛ የማንበብ ልምድን ለመገንባት ሀ ብለህ ስትጀምር ጦር ሜዳ ላይ ለመዋጋት እንደሰለፍክ ቁጠረው። ይሀ አባባል ሊያስፈራራህ አይገባም፣ ይልቁንም የሚመጣውን ፈተና አስቀድመህ በማወቅ ፈተናውን የሚቋቋም ብረት-ለበስ ማንነትን ለመገንባት ተጠቀምበት፡፡
በመሆኑም በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ ጠዋት ተነስቶ ለማንበብ አስቸጋሪ እንደሚሆንብህ የተጠበቀ ነው። ለዚህም ነው ብዙ ስኬታማ ሰዎች ማንም ሰው በህይወቱ ስኬታማ መሆን ቢፈልግ የሚወደውን ሳይሆን የሚሆነውን ማድረግ መለማመድ አለበት የሚሉት፡፡ ምትወደው ነገር ማለት የለመድከው ነው፡፡ በዚህ አውዳዊ ሁኔታ ስንመለከተው ደግሞ አንተ የለመድከው አለማንበብን ነው፡፡ በመሆኑም በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ ማንበብ ሲኖርብህ ሳታነብ ስትቀር ራስህን ከመኮነን ይልቅ አሁንም በመወሰን ካሉበት አቧራን አራግፎ መቀጠል ያስፈልጋል፡፡ በመሰረቱ ለዚህ ጽሁፍ ማንበብን እንደምሳሌ አነሳን እንጅ ሁሉም ልማዶች የሚገነቡት በዚሁ መሰረታዊ ሂደት ነው፡፡ ስለሆነም ይህንን ሂደት ማንኛውንም የምትፈልገውን ልማድ ለመገንባት መጠቀም ትችላለህ፡፡
እንግዲህ ውድ አንባቢዎቻችን በዚህ መደበኛ የማንበብ ልማድ ግንባታ እና ህይወትን የመቀየር ሂደት ልንረዳችሁ የምንችለው ነገር ካለ በዚህ ድህረ ገጽ ላይ በጥያቄ፣ አስተያየት ወይም በጥቆማ መልኩ ብትጽፉልን ያለችንን ለማድረግ ደስተኛ ነን፡፡
መደበኛ የማንበብ ልማድዎን እውን ለማድረግ የሚከተለውን ቅጽ በመጠቀም ግልጽ ውሳኔ ያሳርፉ፡፡ ይህንንም ቅጽ ማንበብ ከመጀመርዎ በፊት ሁልጊዜ ይመልከቱት፡፡
ቀን፡-
------------------------------------
የማነበው መጽሐፍ ርዕስ፡- ------------------------------------------------------------------------
መጽሐፍ የማነብበት ሰዓት፡- ------------------------------------
ዛሬ ምን ያህል ጊዜ አነባለሁ (ማንቂያ ደወል ይጠቀሙ)፡- ------------------------------------
መጽሐፍ የማነብበት ቦታ፡- ------------------------------------
መጽሐፍ ለማንበብ አስፈላጊ ነገሮች በቦታው አሉን፡- ------------------------------------------------------------------------
ሳነብ የሚገትሙኝ ፈተናዎች ምንድን ናቸው፡- ------------------------------------------------------------------------
ሳነብ ለሚገጥሙኝ ፈተናዎች መፍትሄዎችስ፡- ------------------------------------------------------------------------
አንዴ ቆም ብለህ አስብ፡-
o ዛሬ አሁንኑ ልትተገብረው የምትችለው ከዚህ ጽሁፍ የተማርከው አንድ … ሁለት … ሶስት … ወዘተ ሃሳብ ምንድን ነው?
o ስላንድ ነገር ብዙ መረጃ መኖር ዕውቀት ነው፤ መረጃውን በተግባር መጠቀም ደግሞ ጥበብ ነው እና አሁንኑ ወደ ተግባር ግባ!
አስተያየት፣ ተጨማሪ ሃሳብ እንዲሁም ጥያቄ ካላችሁ በዚሁ ድህረ-ገጽ ፃፉልን!
መልካም የመደበኛ ንባብ ልማድ ግንባታ ጊዜ እመሰግናለሁ!
0 አስተያየቶች