መግቢያ

ከታች የምታገኟቸው ፍሬ ሃሳቦች የተወሰዱት ተግባራዊ ክርስትና ከሚለው በዲ/ ሄኖክ ሃይሌ practical spirituality ከተሰኘው አቡነ አትናቲዎስ ዘእስክንድርያ በእንግሊዝኛ ከፃፉት መጽሐፍ ወደ አማርኛ ከተተረጎመው መጽሐፍ ነው፡፡

በዚህ ውብ መጽሐፍ ውስጥ መንፈሳዊነትን ማለትም ክርስትናን እንዴት በእያንዳንዱ የህይወት ዘርፎቻችን እንደምንኖረው ሃሳቦችን ብቻ ሳይሆን ተጨባጭ ዘዴዎችንም ይነግረናል፡፡ መጽሐፉን እኔ ካነበብኳቸው መጽሐፍት ልዩ የሚያደርገው መንፈሳዊነትን ማለትም ክርስትናን በጠጨባጭ የኖሩ በአብዛኛው ባህታዊያን መነኩሳት እንዴት እንደኖሩት እና እንዴትም ይፈተኑ እንደነበር ለእኛ በሚገባ መልኩ ከእነ ተጨባጭ መንገዱ ያብራራል፡፡

ስለዚህ ውድ አንባቢዎች እኒህ ጥቂት መልዕክቶች በመጽሐፉ ውስጥ ካሉት በርካታ ቁምነገሮች መካከል በእኔ ጠባብ እይታ ላካፍላችሁ የወደድኳቸው ጥቂት መልዕክቶች ናቸው፡፡ ሁላችሁም በቻላችሁት ፍጥነት መጽሐፉን እንድታነቡት እመክራችኋለሁ፡፡ ትልቅ ህይወት እንደምትፈጥሩበት ሙሉ እምነቴ ነው፡፡ 

ፈቃድን ከእግዚአብሔር ስለመጠየቅ

ሁልጊዜም በህይወታችን ውሳኔ ለሚያስፈልጋቸው ትንንሽም ይሁኑ ትልቅ የህይወት ጉዳዮቻቸን የእግዚአብሔርን ፈቃድ መጠየቅ መልመድ አለብን፡፡ የእግዚአብሔርን ፈቃድም እንደራሳችን ፈቃድ የመውሰድ ልማድ ሊኖረን ይገባል፡፡ ፈቃዱን ስንጠይቅ ግን የእኛን ውስጣዊ ፍላጎት ወደ ኋላ በመተው መሆን አለበት፡፡ በነገር ሁሉ የእኛን ፍላጎት እንዲያደርግልን ሳይሆን የእርሱን እቅድ እንዲገልጽልን መጠየቅ አለብን፡፡

ስለ ህይወት በመንፈሳዊው ዓለም

ህይወታችሁ ሁለት ሰዎች እንደሚሰሩባት ጀልባ ናት፡፡ የአንደኛው ስራ መቅዘፍ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የጀልባዋን አቅጣጫ መቆጣጠሪያ መልህቅ የሚይዝ ነው፡፡ ጠቢብ ሰው ጌታ ሆይ አንተ አቅጣጫ መቆጣጠሪያውን (መልህቅ) ያዝ እኔ ደግሞ መቅዘፊያውን ልያዝ ይላል፡፡ ይሁን እንጅ ብዙዎቻችን የአሁን ዘመን ሰዎች እኛ ራሳችን የአቅጣጫ ጠቋሚውን ለመያዝ እና እግዚአብሔርን ቀዛፊ ለማድረግ የምንታገል ሆነናል፡፡ በዚህም የተነሳ ወደማንወጣው በስራ መወጠር እና ጭንቀት ዑደት ውስጥ ገብተናልና እናስተውል፡፡

ስለ የእግዚአብሔር ፈቃድ የባህታዊው ቲዎፋን አስተምህሮ በምሳሌ

አንድ ሰው ወይን የያዘ ብርጭቆ ቢኖረው እና በዚያው ብርጭቆ ማር ማስቀመጥ ቢፈልግ ወይኑን ከብርጭቆው በመድፋት፣ የወይኑ መዓዛ እስኪለቅ በፀሐይ ለጥቂት ሰዓታት ማስመታት እና ማሩን ወደ ብርጭቆው መጨመር ይችላል፡፡ የወይን ጭማቂ የተባለው ጊዚያዊ፣ ፍጹም ያልሆነው እና ደስ የማያሰኘው የእኛ ፈቃድ ነው፡፡ ማር የተባለው ደግሞ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ በእኛ ላይ ይገለጥ ዘንድ የእኛን ፍቃድ ከተቻለ ማስወገድ አሊያም ገለልተኛ ማድረግን መለማድ አለብን፡፡ 

ከምናስበው እና ከምናደርገው ነገር ሁሉ በፊት የቅዱስ እግዚአብሔርን መልካም ፈቃድ እንጠይቅ፡፡

ጽሁፉን ለምትወዷቸው ሁሉ ጋሩት!