መግቢያ
ከታች የምታገኟቸው ፍሬ ሃሳቦች የተወሰዱት የኑሮ መድህን ከሚለው በዲያቆን አሸናፊ መኰንን ከተፃፈ መጽሐፍ ነው፡፡ በዚች አጭር ሃሳብ መጽሐፉን በወፍ በረር አስቃኛችኋለሁ፡፡
በዚህ ጽሁፍ የእኔ ዋና ዓላማ በዚህ ጽሁፍ ከማቀርባቸው ጥቂት ሃሳቦች በላይ በጽሐፉን ራሳችሁ እንድታነቡት፣ ካነበባችሁትም እንድትደግሙት እንደ ማንቂያ ደወል ለመሆን ነው፡፡ ስለሆነም የመጽሐፉን ለሙሉ መልዕክቱ ሁላችሁም መጽሐፉን እንድታነቡት እመክራችኋለሁ፡፡ ህይወታችሁን እንደምታተርፉበት እምናለሁ፡፡
በዚህ ድንቅ መጽሐፍ ውስጥ የኑሮ መድህን ማን እንደሆነ እና እንዴት መድህናችን እንደሆነ በግልጽ በእያንዳንዱ የህይወት ዘርፎቻችን ተንትኖ በተጨባጭ ምሳሌዎች ይነግረናል፡፡ መጽሐፉን እኔ ካነበብኳቸው መጽሐፍት ልዩ የሚያደርገው እግዚአብሔር የኑሮ መድህናችን እንደሆነ በማሰብ እንድናምን ብቻ ሳይሆን በጠጨባጭ እውናዊ በሆኑ ምሳሌዎች በማስደገፍ የኑሯችን መድህንነቱን በተጨባጭ እንድናየው፣ እንድንዳስሰው፣ እንድንረዳው እና እንድናምነው ያስገነዝባል፡፡
ስለዚህ ውድ አንባቢዎች እኒህ ጥቂት መልዕክቶች በመጽሐፉ ውስጥ ካሉት በርካታ ቁምነገሮች መካከል በእኔ ጠባብ እይታ ላካፍላችሁ የወደድኳቸው ጥቂት መልዕክቶች እነሆ፡፡
ምዕራፍ አንድ፡-
ኑሮ እና ህይወት
መጀመሪያ ስለማይቀረው
(ስለሞት) አስብ፡፡ ቀጥሎ ሊሆን ላይሆን ስለሚችለው ነገር ማሰብ ትቀጥላለህ፡፡ ኑሮ የዚህ ዓለም ቆይታችን ነው፤ ህይወት ግን እየሱስ ክርስቶስን ካመንበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዘላለም የሚቀጥል ነው፡፡ ሰዎች በትልቅ ተቋማት ገብተው የሚማሩት የእንጀራ ዕውቀት እንጅ የህይወትን ዕውቀት አይደለም፡፡
ምዕራፍ ሁለት፡-
የፀሐይ ዕድሜ
ህይወትን ከትዕግስተ ይልቅ በቁጣ፣ ከትህትና ይልቅ በትዕቢት ለመምራት መሞከር ለቀጣዩ የህይወታችን መንገድ መሰናክል እንደማዘጋጀት ነው፡፡ መልካም ዕድል የሚሰጥ ሳሆን የሚመረጥ መሆኑን እናስተውል፡፡
ምዕራፍ ሶስት፡-
ቁጥር አንድ
ከሚጠቅሙት ነገሮቻች ሁሉ እግዚአብሔርን ካላስቀደምን ጥቅም የላቸውም፡፡ ምክንያቱም ቀድሞ ነገር የሁሉም ነገሮች ባለቤት ራሱ ነውና፡፡ የሆነው ሆኖ እግዚአብሔር ባስቀመጥነው ሁሉ ቦታ ይቀመጣል፤ ትሁት ነውና፡፡ የምናስቀምጥበትን ቦታ የመወሰን ምርጫው ለራሳችን ነው፡፡ ውጤቱን ማጨድ ግን ግድ ነው፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ስራውን የሚሰራውና ካስቀመጥንበት ቦታ አንፃር ነው፡፡
ምዕራፍ አራት፡-
የሚበልጠውን ይዘናል
ወርቅ የሰጠ ነሃስ እንደማይከለክል ይታወቃልና ነፍስና ስጋችንን የሰጠን አምላክ ስለምን ለነፍስና ለስጋ የሚያስፈልጋቸውን ትንንሽ ነገሮች (ስራ፣ ገንዘብ፣ ስልጣን ወዘተ) አይሰጠንም?
ሁላችንም ሰዎች የመረጃ እጥረት ያለብን እንጅ ብዙ ያጣን ሰዎች አይደለን፡፡
ምዕራፍ አምስት፡-
እርካታ ማጣት
እኛ ሰዎች በህይወታችን ሁሉ ልክ እንደ ጅብ የመጠባበቅ ጉዞ ላይ ነን፡፡ ደግሞም ሁላችን በማንኛውም የህይወታችን ዘርፎች ወረፋ ላይ ነን፡፡
ቁሳቁሶች ራሳቸውን ስለማይለውጡ አያረኩንም፡፡ ራሳቸውን ስለማይጠብቁ እረፍት ይነሱናል፡፡
ምዕራፍ ስድስት፡-
የበረሃ መና
ሙሴን የእስራኤልን ህዝብ ምን እንደሚመገቡ ባሰበ ጊዜ እግዚአብሄር ሙሴንም አለው፡-
እስኪ ይህ ድንጋይ ፈንቅለው ሲል አዘዘው፡፡ ሙሴ ድንጋየን ፈነቀለውም፡፡ ያን ጊዜም ትሎቹ ሲርመሰመሱ ተመለከተ፡፡ እግዚአብሔርም ጠየቀው፡-
እነዚህን ትሎች ማነው ሚመግባቸው አለው፡፡ ሙሴም መለሰ አንተ አለው፡፡ እግዚአብሔርም አለ እነዚህን ትሎች ለመመገብ ቸላ ያላልኩ አምላክ በአምሳሌ የፈተርኩትን ክቡር ፍጡር ሰው ለመመገብ ቸላ የምል ይመስልሃል ሲል ከጭንቀቱ አረጋጋው፡፡
ከእግዚአብሔር ችሎታ በላይ የሆነ ፈተና ገጥሞን አያውቅም፣ አልገጠመንም፣ ወደፊትም አይገጥመንም እና ልባችንና አንደበታችን ሊጸና ይገባዋል፡፡ ድካማችንንም በጸሎት ለእግዚአብሔር መንገር ይኖርብናል፡፡
ጽሁፉን ለምትወዷቸው ሁሉ አጋሩት!
0 አስተያየቶች