እያንዳንዷ ቀን የልደት ቀንህ ናት ብልህስ፡፡ የልደት ቀንህ ማለት አንተ አዲስ ማነትን ይዘህ ወደ ዚች ምድር የመጣህባት ዕለት ናት፡፡ እሷም በተለመደው እና በሰፊው መንገድ መሰረት በዓመት አንድ ጊዜ ትከበራለች፡፡ እያንዳንዷ ቀን አሁን ካለህበት የተሻለ አዲስ ማንነትን እንድትገነባባት የተሰጠችህ ልዩ እድል ናት፡፡ ስለሆነም ይሁን እንጅ ይልተለመደውን ነገር ግን እውነታ የሆነውን ጠባቡን መንገድ ስንከተል እያንዳንዷ ቀን ለሁላችንም የልደት ቀናችን ናት፡፡ የትኛውም የህይወት ስኬት ደረጃ ላይ ላለ ሰው ይህ ይሰራል፡፡ ምክንያቱም ስኬት ሁሌም የምንጓዘው ሂደት እንጂ መጨረሻ የለውምና፡፡

እያንዳንዷ ቀን የልደት ቀንህ አድርገህ በመቀበልህ የምታገኘው ትልቁ ጥቅም ተሆኖ የማያልቀውን የተሻለውን ማንነትህን ሁሌ በእያንዳንዷ ቀን ወደ ተሻለ አዲስ ማንነት የመሆኛ ዕለት አድርገህ ተግተህ ትጠቀምባታለህ፡፡ አለበለዚያ ሰፊውን መንገድ ተከትለህ ልክ እንደ ብዙዎቹ የልደትህን ቀንህን በዓመት አንድ ጊዜ የምታከብር ከሆነ የተሻ አዲስ ማንነት ለመፍጠር የልደት ቀንህ ገና ዓመቱን ጠብቆ እስኪመጣ ትጠብቃለህ ማለት ነው፡፡

ደግሞም እያንዳንዷ ቀን የልደት ቀናችን ካልሆነች ስለምን በየወሩ፣ 2 3 4 5 6 … 11 ወሩ ወዘተ አሊያም በየዓመቱ፣ 2 3 4 5 6 … ዓመት ወዘተ አናከብረውም? ማነው በዓመት አንድ ጊዜ ይከበር ያለን? ይህ በማህበረሰቡ ዘንድ የተለመደ ሰፊ መንገድ ከመሆኑ ውጭ ሌላ ትርጓሜ ያለው አይመስለኝም፡፡ ካለው ከእናንተው ከውድ አንባቢዎቸ ለማወቅ ዝግጁ ነኝ፡፡

ህይወት በእያንዳንዷ ቀን እና ቅጽበት የምትኖራት ክንውን ናት፡፡ ስለሆነም ለእያንዳንዷ ቀን እና ቅጽበት የሚገባቸውን ዋጋ ስጥ፡፡ በህይወትህ በጣም ተደስተህ እና ተሳክቶልህ ያሳለፍካት አንዲት ቀን ወይም ቅጽበት ካለህ ከዚያች ቀን ወይም ቅጽበት ላይ ትኩረትህን አድርግ፡፡ ትልቁ ስራህ የሚሆነው ያችን ቀን ወይም ቅጽበት ነገም፣ ከነገ ወዲያ እና መጪ ዘመንህን መኖር መለማመድ እና መንገድ መፍጠር ነው፡፡

ይን እጅ እንዳለመታደል ሆኖ ብዙዎቻችን በህይወታችን በጣም ያዘንባትን እና የወደቅንባትን ቀን በማሰብ የህይወት ሃሳባችን፣ ምርጫችን፣ እና ውሳኒያችን ሁሉ ያችን ክፉ ቀን በማሰብ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ በእግዚአብሔር ዘንድ ተስፈኞች እና ብንወድቅ እንኳን ታሪካችን ለበጎ የሚቀየር ሆኖ ሳለን በራሳችን መንገድ ከዚያች ክፉ ቀን አንፃር ስለምንኖር ተስፋ ቢሶች ሆነናል፡፡ ባጠቃላይ ነገ የሚባል የእውነት ጊዜ የለንምና በከንቱ አንቅጠር፡፡ ካለንም ሊመጣም ላይመጣም ይችላል፡፡ ዛሬ ግን በመዳፋችን ላይ ያለች የእውነተኛዋ ጊዜ ናት እና የሚገባትን ዋጋ እንስጣት፡፡

አንዴ ቆም ብለህ በማሰብ፡-

በእያንዳንዷ ዛሬ መስራት ያለብህን ቆም ብለህ አስብ

በእያንዳንዷ ዛሬ ነገ የጠምትሰራቸውን እወቅ

በእያንዳንዱ ዛሬ ለመቀየር ዕድልን ስለምትሰጥህ የልደት ቀንህ ናት

በእያንዳንዷ ዛሬ የወደፊት ህልምህን በማንበብ አመላለስበት

በእያንዳንዷ ዛሬ አስፈላጊ ያህል ጊዜ መድበህ ራስህን አዳምጥበት

በእያንዳንዷ ዛሬ የሰራሃቸውን ስራዎች ገምግም 


አንዴ ቆም ብለህ አስብ፡-

ዛሬ አሁንኑ ልትተገብረው የምትችለው ከዚህ ጽሁፍ የተማርከው አንድ … ሁለት … ሶስት … ወዘተ ሃሳብ ምንድን ነው?  

ስላንድ ነገር ብዙ መረጃ መኖር ዕውቀት ነው፤ መረጃውን በተግባር መጠቀም ደግሞ ጥበብ ነው እና አሁንኑ ወደ ተግባር ግባ!

በጽሁፉ ላይ ተጨማሪ ሃሳብ፣ አስተያየት፣ ጥያቄ ካለ መነጋገር መርሃችን ነው፡፡

ጽሁፉ ይጠቅማል ብለው ካሰቡ ለሌሎች ያጋሩ፡፡