መግቢያ
የሰው
ልጅ በጣም ብዙ ጭንብሎችን በውስጡ ይዞ ይንቀሳቀሳል፡፡ እኒህን ጭንብሎችም እንደ ቦታው፣ ጊዜው፣ ሁኔታው፣ ብቻውን እና ከሰው
ጋር ሲሆን እንዲሁም በገዛ አካሎቹም ጭምር እያቀያየረ ይጠቀማቸዋል፡፡ አሁን አሁን የሰው ልጅ ማንነት በጋሸበበት በዚህ ክፍለ
ዘመን ህይወታችንን እንደ አየሩ ጠባይ (እንደ ቦታው፣ ጊዜው እና ሁኔታው) መምራት እየተለመደ የመጣ የኑሮ ዘዴ ሆኗል፡፡
በዚህም የተነሳ አንዱ ሰው በህይወቱ በተለያዩ ቦታዎች፣ ጊዚያት፣ ሁኔታዎች፣ ብቻውን እና ከሰው ጋር ሲሆን እንዲሁም በገዛ
አካሎቹ ሳይቀር የተለያዩ እና ጭራሽ የማይገናኙ ባይተዋር የሆኑ ገጸ-ባህሪያትን ሲላበስ ይታያል፡፡ በእኔ አስተያየትም ይህንን
የአንድ ሰው በተለያየ ቦታ፣ ጊዜ እና ሁኔታ የተለያዩ ገጸ-ባህሪያትን መላበስ ህይወት በፈረቃ ብየዋለሁና በዝርዝር
እንመልከት፡፡
ህይወት በፈረቃ - ከቦታ አንፃር
በጣም ብዙዎቻችን በቤት እምነቶቻችን፣ በስራ ቦታችን እና በመኖሪ ቤታችን ውስጥ የምናሳየው ገጸ-ባህሪ (ልማድ፣ ምግባር፣ እምነት፣ አመለካከት እና
ተግባር) ሙሉ
በሙሉ በሚባል ሁኔታ የተለያየ ነው፡፡ ለምሳሌ ብዙዎቻችን በቤተ እምነቶቻችን ስንሆን በጣም መልካም እና ጥሩ የሆነ የማንነት ገጸ-ባህሪያትን እንላበሳለን፡፡ በዚያ ቦታ የምናሳያቸው ልምምዶቻችን፣ ምግባሮቻችን፣ እምነቶቻችን፣ አመለካከቶቻችን እና
ተግባሮቻችን ሁሉ
በጣም ደስ
የሚሉ እና
የሚያስቀኑ ናቸው፡፡ ይሁን እንጅ እኒህ መልካም ማንነቶቻችን ወደ ውስጣችን ዘልቀው በመግባት የማንነታችን አካል
ስላልሆኑ ይልቁንም በንቁ አእምሯችን ሆነ
ብለን እያሰብን ስለምናደርጋቸው ልክ ከቤተ እምነታችንን ቅጥር-ግቢ ስንወጣ የእውነኛው እና
ሌላኛው ገጸ-ባህሪ ማለትም በውስጣችን በልማድ፣ በምግብር፣ በእምነት፣ በአመለካከት እና በተግባር መልኩ ዘልቆ የገባው ማንነታችን ራሱን
መግለጽ ይጀምራል፡፡ ያ የአብዛኞቻችን ማንነትም በቤተ እምነት ውስጥ ከነበረው ጭራሽ የማይገናኝ እና ብዙ እንከኖች ያሉበት ነው፡፡
በጣም የሚገርመው ይህ ተቀያያሪው ማንነታችን በቤተ እምነት እና በቤታችን ውስጥ አያበቃም፡፡ ሌላም ሶስተኛና የተለየ ማንነት ያለው በስራ ቦታ ብቻ የሚገለጽ ገጸ-ባህሪ አለ፡፡ እንዴያውም ያገሬ ሰው በመኖሪያ ቤቱ እና በስራ ቦታ የሚያሳየው ምግባር የተለያየ የሆነበትን ሰው እርሱ እኮ የቤት አልጋ፣ የውጭ ቀጋ ነው ሲል ይገልጸዋል፡፡ ይህ ማለትም ከቤት ያለው ባህሪው ልክ እንደ አልጋ ለባለቤተሰቦቹ በጣም የሚመች ማለት ሲሆን፣ ከቤቱ ውጭ ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚያሳየው ባህሪው ደግሞ ልክ እንደ ቀጋ የሚዋጋ እና የማይመች ለማለት ነው፡፡ ባጠቃላይ አንድ ሰው ከቦታ አንፃር (በቤት፣ በስራ ቦታ እና በቤተ እምንት) ምንም የማይገናኙ እና ባይተዋር የሆኑ ማንነቶች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ ይንንም ዓይነት ያንድ ሰው በተለያየ ቦታ የተለያየ ገጸ-ባህሪያትን ማንጸባረቅ ህይወት በፈረቃ ብየዋለሁ፡፡ ጥቂት በሁለንተና ህይወታቸው ስኬታማ የሆኑ ሰዎችን የህይወት መርህ እና ልምምድ ስንመለከት ግን በየትኛውም ቦታ ቢሆኑ የሚያሳዩት ማንነት አንድ ወጥ ነው፡፡
ህይወት በፈረቃ - ከጊዜ አንፃር
በጣም ብዙዎቻችን ደግ እና ሃይማኖተኛ የምንሆነው በበዓላት ሰሞን፣ በህይወታችን ፈተና በገጠመን ጊዜ እና ጠዋት አሊያም በእርጅና ዘመናችን ነው፡፡ ብዙ ሰው ጠዋት ከእንቅልፉ እንደተነሳ ቤተ እምነቱ ሄዶ አምላኩን አመስግኖ እና በህይወቱ የሚፈልገውን ያደርግለት ዘንድ ተማጽኖ ይመጣል፡፡ በዚህ ጊዜም እጅግ ትሁት መንፈሳዊ ሰው ይሆናል፡፡ ይህ
በእውነት እጅግ
የሚበረታታ መልካም ልምምድ ነው፡፡ ይሁን እንጅ ያ ሰው
ወደ ቤተ
እምነት ከመሄዱ በፊት እና በኋላ በቤተቱ እና በስራ ቦታው ያለውን ማንነት እና አድራጎት ብንመለከት በጣም
በአብዛኛው ከቤተሰቦቹ፣ ከጎረቤቶቹ አሊያም ከባልደረቦቹ ጋር ተጣልቷል፡፡ ይቅርም አላላቸውም ይሆናል፡፡ ይባስም ብሎ ወደ ቤተ እምነት ሲሄድ እና ሲመለስም ሳይቀር ስለ ሰዎች ክፋት እና ስላደረጉበት ክፉ ነገር እያሰላሰለ ነው፡፡ ይህንን ሰው በስራ ሰዓት እና በምሽት ጊዜ ከባልደረቦቹ ወይም
ከጓደኞቹ ጋር
በመጠጥ ቤቶች
አካባቢ በመሄድ ሰዎችን ያማል፣ በሰዎች ላይም ሴራን ይዶልታል ሌላም ሌላም ያደርጋል፡፡ ይህን ዓይነቱን ሰውም የሃገሬ ሰው የጠዋት ቀዳሽ፣ የማታ ደናሽ ሲል ይገልጸዋል፡፡ እኔ
ደግሞ ህይወት በፈረቃ ብየዋለሁ፡፡
ሌላው አስገራሚው ነገር ደግሞ ሰው በወጣትነት ዕድሜው ኃይለኛ፣ ለስጋ ህይወቱ አብዝቶ የሚሮጥ፣ ታታሪ ሰራተኛ መሆን እንጂ ስለ ደግነቱ፣ ስለ መንፈሳዊነቱ ሲያረጅ እና ጉልበቱ ሲደክም እንደሚያደርገው የደግነት እና የመንፈሳዊነት ቀጠሮን ይይዛል፡፡ ይህ ዓይነቱ ሰው ከሞት ጋርም በእርጅና ዘመኑ ይመጣ ዘንድ ቀጠሮ የያዘ ይመስላል፡፡ እውነታው ግን ሰው በወጣትነቱ ጊዜ አምላኩን ማሰብ እና ማገልገልም አለበት፡፡ ሞትም ወደ ሰዎች መቸ እንደሚመጣ ከእርሱ ከህይወት ባለቤቱ ከፈጣሪ በቀር ማንም አያውቅምና ሰው ተዘጋጅቶ ይጠብቅ ዘንድ መልም ነው፡፡
ህይወት በፈረቃ - ከሁኔታ አንፃር
ብዙዎቻችን ሁኔታዎች በተመቻቹልን ጊዜ የተሻለ ማንነት ያለውን ገጸ-ባህሪ እንላበሳለን፡፡ ማለትም ሁኔታዎች በተመቻቹልን ጊዜ
ታታሪ፣ ተስፈኛ፣ መልካም እና መንፈሳዊ ሰው እንሆናለን፡፡ ሁኔታዎች እንደማንጠብቃቸው እና እንደማንፈልጋቸው በሆኑ ጊዜ ግን ደካማ፣ ተስፋቢስ፣ ነጭናጫ እና አመጸኛም እንሆናለን፡፡ ይሁን እንጅ የሰው ጥንካሬው የሚለካው በበተመቻቹልን ሁኔታ ውስጥ በሚያሳየው ማንነት ሳይን ሁኔታዎች ከባድ እና አስቸጋሪ በሆኑበት ጊዜ ነው፡፡ እናም በህይወታቸው ስኬታማ የሆኑ ሰዎች ሁኔታዎች ከባድ እና አስቸጋሪ በሆነ ጊዜ ከመቸውም በበለጠ ታታሪ፣ ተስፈኛ፣ መልካም እና መንፈሳዊ በመሆን ሰው በእርግጥም ከፈተናዎች ሁሉ በላይ መሆኑን በተግባር ያሳያሉ፡፡ ባጠቃላይም የውስጥ እና የእውነት የሆነ መልካ እና ጠንካራ ማንነት በቦታ፣ በጊዜ እና በሁኔታዎች የተገደበ አይደለም፡፡ ይልቁንም ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ እንዲሁ ሳንታገል ከውስጣችን የሚንጸባረቅ ነው እንጅ፡፡
በአጠቃላይ ለዚህ
በቦታዎች፣ በጊዜያት እና በሁኔታዎች መሰረት የተለያየ ገጸ-ባህሪያት ከማንጸባረቅ ይልቅ
አንድ ወጥ
መሆን ያለበትን ሰው መሆን የማንም ሰው ትልቅ ግብ መሆን ይችላል፡፡ ይህንን መሆን ያለብንን ወጥ ሰው ለመሆን በቅድሚያ ያን ልንሆን የፈለግነውን የተሻሉ የማንነት ገጽታዎች ማለጽም ልማዶቹ፣ ምግባሮቹ፣ እምነቶቹ፣ አመለካከቶቹ እና ተግባሮቹ በጥንቃቄ መምረጥ ያስፈልጋል፡፡
በመቀጠልም እኒህን የተመረጡ የተሻሉ የማንነት ገጽታዎች ሆነ ብሎ በእያንዳንዱ ቀን የምንለማመድበትን እና ገንዘባችን የምናደርግበትን መንገድ መቀየስ፡፡ ምናልባት ገና ስታስበው እና ከጀመርከው ጀምሮ
ለቀናት፣ ለሳምንታት እና ለወራትም ቢሆን ይህንን ማንነት መገንባት ከባድ መስሎ ሊታይህ ይችላል፡፡ ይሁን
እንጅ ልምምድህን በትዕግስት እና በተስፋ ስትቀጥለው ከምታስበው እና ስትጀምረው ካገኘኸው በታች በጣም ይቀልሃልና በልምምድህ ጽና፡፡
እርግጥ ነው ይህንን ማንነት ለመገንባት ጊዚያዊ ዋጋ ያስከፍላል፤ ነገር ግን ዘላቂ በረከት እና የህይወት ስኬትን ያስገኛል፡፡ በደንብ ልብ ልንለው የሚገባው ነገር ግን የፈረቃ ህይወትን መኖር ጊዚያዊ ምቾት እና ደስታን ይሰጣል፤ ዘላቂ ዋጋን ያስከፍላል፣ የህይወት ቀውስንም ያስከትላል፡፡ የቱ ይሻላል? ምርጫ ነውና በጥንቃቄ አስበህ ምረጥ፡፡
ህይወት በፈረቃ - ብቻችን እና ከሰው ጋር ስንሆን
ብዙዎቻችንን ከሰዎች ጋር ስንሆን በሰዎች ላለመተቸት እና ጥሩ ሰው ለመምሰል በንቁ አእምሯችችን ያለ የሌለ አቅማችንን ተጠቅመን ጥሩ እና ጠንካራ ባህሪያትን፣ ልማዶችን፣ ተግባርራትን፣ እምነቶችንና አመለካከቶችን እናንጸባርቃለን፡፡ ይሁን እንጅ የሰው የእውነተኛ የውስጥ ማንነቱ የሚገለጠው ብቻውን ሲሆን ነው፡፡ ያን ጊዜ የወስጡ የእውነተኛ ማንነታችን የሚገለጥበት እና የሚንጸባረቅበጽ ነው፡፡ እናም ብቻችንን ስንሆን ማንም ስለማያየን ያልተገቡ ባህሪያትን፣ ልማዶችን ተግባርራትን፣ እምነቶችንና አመለካከቶችን እናንጸባርቃለን፡፡ ይህም ለራስ ክብር ካለመኖር እና ለራስ ካለመታመን የመነጨ ነው፡፡ የፈረቃ ህይወት ይሉሃል ይህ ነው፡፡ ከሰዎች ጋር ስንሆን የሆነ ሰው፣ ብቻችንን ስንሆን ደግሞ ሌላ ሰው፡፡ ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ ብቻችንን የምንሆንበትን ጊዜ እና አጋጣሚ ሁሉ መሆን ያለብንን ሰው ለመሆነ የመለማመጃ አጋጣሚ አድርገን እጠቀም እላለሁ፡፡
ጥቂት ስኬታማ ሰዎች ግን ለራሳቸው ክብር ስላላቸው፣ ራሳቸውን ስለሚወዱ እና ለራሳቸውም ስለሚታመኑ በምድር ላይ ብቻቸውን ቢቀሩ እና ማንም ባያያቸው እንኳን ተገቢውን ባህሪያቸውን፣ ልማዳቸውን ተግባርራቸውን፣ እምነታቸውን እና አመለካከታቸውን ያንጸባርቃሉ፡፡ እኛም በህይወታቸን የእውነት ስኬታማ መሆን ከፈለግን ይህንን ልምምድ ልናደርግ ግድ ነው፡፡
ህይወት በፈረቃ - በአካሎቻችን
ሰው በቦታ፣ በጊዜ እና በሁኔታ በፈረቃ መኖር አልበቃው ብሎ በአእምሮው፣ በልቡ፣ በአንደበቱ እና በአካሉም ሳይቀር በፈረቃ መኖርን ተያይዞታል፡፡ እኛ ሰዎች በአእምሯችን የምናስበው አንድ ነገር፣ በልባችን የምናምነው፣ ሌላ ነገር (ምናልባትም ተቃራኒ)፣ በአንደበቱ የሚናገረው ሌላ ሶስተኛ ነገር እነዲሁም በአካሉ የሚተገብረው እና የሚገኘው ሌላ አራተኛ ነገር ይሆናል፡፡ በጣም አስገራሚው ነገር ሰው በንቁ አእምሮው አንድ ነገር ያስባል፣ በድብቁ አእምሮው ግን ሌላ ነገር፡፡ ከላይ በተጠቀሱት እና በገዛ አካሎቻችን ሳይቀር የፈረቃ ህይወት መኖር ልምምድ መሰረቶችም እኒህ የሁለቱ አእመሮዎቻችን አለመስማማት ነው፡፡
የመፍሄ
ሃሳብ
ስለዚህ ለፈረቃ ህይወት ዘላቂ መፍትሄ ሁላችንም ከዛሬ ጀምሮ ትልቁ የቤት ስራችን ማድረግ ያለብን ሁለቱን አእምሮዎቻችን (ንቁ
እና ድብቁን) በልምምድ ወደ ስምምነት ማምጣት ነው፡፡ ውጤቱን ትቶ መንስኤውን እንዲሉ ሁለቱን አእምሮዎቻችን ካስማማናቸው በማንኛውም ቦታ፣ ጊዜ፣ ሁኔታ፣ ብቻችንም ብንሆን እንዲሁም በአካሎቻችን መሆን ያለብንን ብቻ የመሆን አቅም እና ችሎታ እናገኛለን፡፡ የህይወታችን ዘላቂ ስኬትም የተደበቀው ይህንን ማድረግ ላይ ነውና በትኩረት እናስብበት፡፡
አንዴ ቆም ብለህ አስብ፡-
o ዛሬ አሁንኑ ልትተገብረው የምትችለው ከዚህ ጽሁፍ የተማርከው አንድ … ሁለት … ሶስት … ወዘተ ሃሳብ ምንድን ነው?
o ስላንድ ነገር ብዙ መረጃ መኖር ዕውቀት ነው፤ መረጃውን በተግባር መጠቀም ደግሞ ጥበብ ነው እና አሁንኑ ወደ ተግባር ግባ!
በጽሁፉ ላይ ተጨማሪ ሃሳብ፣ አስተያየት፣ ጥያቄ ካለ መነጋገር መርሃችን ነው፡፡
ጽሁፉ ይጠቅማል ብለው ካሰቡ ለሌሎች ያጋሩ፡፡
0 አስተያየቶች