መግቢያ

ልብ ብለን ካየን በጣም ብዙ አሰራሮች እና አስተሳሰቦች የተገላቢጦሽ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ሁኔታዎች ከፈቀዱልን እኒህን የተገላቢጦሽ አስተሳሰቦች እና አሰራሮች የማስተካከል ዕድል ይኖረናል፡፡ ምናልባትም ከእነዚህ የተገላቢጦሽ አስተሳሰቦች እና አሰራሮች አንዱ ወይም ጥቂቶች ላይ በማተኮር ማስተካከል እና ወደ ትክክለኛ አስተሳሰባቸው እና አሰራራቸው ማምጣት የህይወት ዓላማችን አድርገን ልንሰራ እንችላለንና ልብ ብለን እናንብባቸው፡፡ ለዚህም ነው እኒህን የተገላቢጦሽ አስተሳሰቦች እና አሰራሮች ጽሁፍ ያዘጋጀዋቸው፡፡ ስለሆነም በእኔ እይታ የተገላቢጦሽ ሆነው ያገኘዋቸውን ላካፍላችሁ፡፡ 

ውድ ነገሮች በነፃ ርካሽ ነገሮች በውድ ዋጋ መገኘታቸው

ህይወትህን፣ የህይወት መሰረት የሆነውን አየርን፣ በምድር ላይ ለህይወት መኖር መሰረት የሆነችዋን ፀሐይን፣ የአካል ክፍሎችህን አእምሮን ጨምሮ፣ ሃሳብ፣ በሰውነትህ ውስጥ የሚካሄዱ ስርዓቶች፣ ቅድስናን፣ መልካመነትን ወዘተ ውድ የሆኑ ነገሮችን በነፃ መሰጠታችን ሱስን፣ ስካርን፣ ዝሙትን ወዘተ ደግሞ ከፍለን ማግኘታችን የተገላቢጦሽ አይደለምን?  

ለህይወት ጠቃሚ የሆኑ ልማዶችን እና ምግባሮችን (ማንበብ፣ ስፖርት፣ ጠዋት መነሳት፣ ማመስገን፣ ታማኝነት ወዘተ) መልመድ ከባድ ለህይወት ጎጂ የሆኑ ልማዶችን እና ምግባሮችን (መዋሸት፣ መጠጥ፣ ሀሜት፣ ማማረር ወዘተ) መልመድ ግን ቀላል መሆኑ የተገላቢጦሽ አይደለምን?

ለህይወት ጠቃሚ የሆኑ ልማዶችን እና ምግባሮችን (ማንበብ፣ ስፖርት፣ ጠዋት መነሳት፣ ማመስገን፣ ታማኝነት ወዘተ) መልመድ ከባድ ለህይወት ጎጂ የሆኑ ልማዶችን እና ምግባሮችን (መዋሸት፣ መጠጥ፣ ሀሜት፣ ማማረር ወዘተ) መልመድ ግን ቀላል ነው። ይህ የሆነበትም ጎጂ የሆኑ ልማዶች እና ምግባሮች በብዙ ሰዎች የሚዘወተሩ እና ሰፊው መንገዶች ስለሆኑ ነው፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ብዙ ሰው የራሱን መንገድ ከመከተል ይልቅ ሰዎችን መምሰል ስለሚያዘነብል ጎጂ የሆኑ ልማዶችን እና ምግባሮችን በቀላሉ የህይወቱ ልምምዶች ያደርጋቸዋል፡፡ እንዲሁም ጎጂ የሆኑ ልማዶችን እና ምግባሮችን ገና ምንም ሳናውቅ በልጅነታችን ቤተሰቦቻችን እና ማህበረሰቡ ስለሚያስተጋቡብን ነው፡፡ ይህም የተገላቢጦሽ ነው

በአንፃሩ ደግሞ ለህይወታችን ጠቃሚ የሆኑ ልማዶችን እና ምግባሮችን (ማንበብ፣ ስፖርት፣ ጠዋት መነሳት፣ ማመስገን፣ ታማኝነት ወዘተ) መልመድ ከባድ የሆኑበት ምክንያት እኒህን ጠቃሚ የሆኑ ልማዶች እና ምግባሮች  ብዙ ሰው ሲተግባራቸው ስለማናይ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ግን በህይወታችን አንዴ ጎጅውን ልማድና ምግባር ከለመድን በኋላ ጠቃሚውን ልማድና ምግባር ለመልመድ ስንሞክርም ከባድ ስለሚሆንብን ነው።

በመስራት ቀርቶ ባለመስራት መመካት 

አስታውሳለሁ ተማሪ እያለን ሁላችንም ተማሪዎች በፈተና ሰሞን ካላጠናን ወይ ለጓደኞቻችን አለማጥናታችን በኩራት እና በደስታ እንገልጽ ነበር፡፡ ስናጠና ብናድርም እንኳን ለጓደኞቻችን በኩራ ማጥናታችንን ከመናገር ይልቅ ምንም እንዳላጠናን በማስመሰል በደስታ እና በኩራ እንናገራለን፡፡ ይህ ባለመስራት እና እንዳልሰሩ በመኩራት መግለጽ እርግጥም የዩኒቨርሲቲ መምህር ሆነን ሳይቀር ቀጠለ፡፡ ይህ ምን ያህል የተገላቢጦሽ መሆኑ ዛሬ ነው የገባኝ፡፡ እኔ ማውቀውን የተማሪዎች እና የዩኒቨርሲቲ መምህራን ባለመስራት መኩራት ገለጽኩ እንጅ በማንኛውም የስራ ዘርፍ ያለ ብዙ ሰው መስራቱን በኩራት ከመናገር ይልቅ አለመስራቱን መግለጽ ይቀለዋል፡፡ አሁን ሲገባኝ ይህ አይነቱ አካሄድ በቅድሚያ ራስን ቀጥሎም ሌሎችን መዋሸት እንደሆነ ዛሬ ልብ ስለው ገበኝ፡፡ ይህንን እውነታ ከተረዳሁም ጀምሮ በእውነት ካልሰራሁ ያለምንም ማጋነን አለመስራቴን በሃፍረት ከሰራሁ ደግሞ መስራቴን በኩራ እገልፃለሁ፡፡

በሰላም ጊዜ መጀገን፣ በከባድ ጊዜ መልፈስፈስ

በሰላም ጊዜ መጀገን ሁሉም ያደርገዋል ይህ ሰፊው መንገድ ነውና፡፡ ስኬታማ ሰዎች የሚለዩት ግን ሁልጊዜም ጠባቡን መንገድ ይከተላሉ፡፡ በከባድ ጊዜ ከሁልጊዜው በበለጠ ይጀግናሉ፡፡ ስለሆነም ህይወት ሁሉ በወደቀበት የእነርሱ ህይወት ወደ ላይ ይወጣል፣ ሰው ሁሉ ተስፋ በቆረጠበት እነርሱ ብዙ የወደፊት ታላላቅ ተስፋዎች ይታያቸዋል፣ ንግድ ሁሉ በከሰረበት እነርሱ ያተርፋሉ …

ራስን ከመካድ ይልቅ በራስ መመካት

አንዳች ነገር በሰው አይሆንም፡፡ የእግዚአብሔር ሃይል በሰው ተገልጦ እንጅ፡፡ በራሳችን እንመካ ከተመካንም እንኳ በእግዚአብሔር ባሪያነታችን ልክ ልንመካ እንችላለን፡፡ ሰው በራሱ አንዳች ነገርን ላላደረገ በራሱ ከተመካ፣ ዓለምን እና ሰውን የፈጠረ ብቻ ሳይሆን የሚያስፈልገውን ሁሉ ያዘጋጀ እግዚአብሔር ምን ያህል ይመካ? ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ በራስ መመካት ወይም በራስ መታበይ የውድቀት ሁሉ ምንጭ ነው፡፡ እናም በራሳችን ከመመካት ይልቅ ራሳችንን እንካድ፡፡ አንዳች ነገር ከእኛ እና በእኛ የሆነ ስለሌለና ወደ ፊትም ስለማይኖር፡፡ ይልቁን ራሳችንን እንካድ፣ በሁለንተናችን ባለቤት በእግዚአብሔር እንመካ፡፡ ራስን የመካድ ትሩፋቱም በምድራዊ ህይወታችን ብቻ ሳይሆን በሰማዩም ሕይወታችን ጭምር ልንሆነው፣ ልናገኘው እና ልንሰራው የምንሻው ሁሉን ነገር እንሆናለን፣ እናገኛለን፣ እንሰራለንም፡፡

ለህፃናት ተማሪዎች አነስተኛ ትኩረት

በእውኑ በትኩረት መያዝ ያለባቸው ህፃናት ተማሪዎች ወይስ ታላላቅ ተማሪዎች?

በጣም አሳዛኙ አውነታ ግን የመጀመሪያ ደረጃ /ቤቶች የህፃናት መማሪያ ሆነው ሳሉ ከሁሉም የትምህር ተቋማት ባነሰ መሰረተ-ልማት ባለበት /ቤት ውስጥ ይማራሉ፡፡ በዚህም ተነሳ ህፃናት በልጅነታቸው ማወቅ ያለባቸውን ዕውቀት፣ መልመድ ያለባቸውን ልማድ እንዲሁም መገንባት ያለባቸውን ምግባር እና እምነት ባለመገንባታቸው ለተንሻፈፈ ህይወት ይዳረጋሉ፡፡ በዚህም ወደ መሰናዶ እና ኮሌጅ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲ ሲደርሱ ያንኑ ህይወት እየደጋገሙ ይኖሩታል፡፡ የተገላቢጦሽ ይሉሃል ይህ ነው፡፡ እንድ ነጭ ወረቀት አለ፡፡ እንዲሁም ሌላ የተፃፈበት ነጭ ወረቀት አለ፡፡ ታዲያ ነጭ ወረቀቱ ላይ የምንጽፈውን ሃሳብ ተጠንቅቆ መፃፍ ይሻላል ወይስ እንዲሁ በዘፈቀደ ከፃፍነው በኋላ እነደገና ጽሁፉን ማስተካከል ይሻላል፡፡

1. የትኛው ይቀላል?

2. የትኛው የበለጠ ውጤታማ የመሆን ከፍተኛ እድል አለው?

3. የትኛው ትልቅ ዋጋ እና ጊዜን ይፈጃል?

እናስብበት

በትንሽ ጥፋት ብዙ መናገር

ብዙዎቻችን ሰዎች በሰሩት በትንሽ ጥፋት ብዙ እንናገራለን፡፡ ልብ ያላልነው ነገር ቢኖር የጠፋው ጥፋት ጥፋቱን በማጥፋቱ ከሚሰደበው ሰው እና ተሳዳቢውም በመናደዱ የሚከፍለው ዋጋ እጅጉን ብዙ ነው፡፡ ስለዚህ መድፌ ቢጠፋ በሬ እንደማንሳል ሁሉ በትንሽ ጥፋት ትልቁን የሰው ልጅ ራሳችንን ጨምሮ ያልተገባ ነገር በመናገር ማስቀየም የለብንም፡፡ ቀድሞ ነገር የሰው ልጅን የሚተካከል ምንም ዓይነት ጥፋት የለም፡፡ ደግሞም ቢቻለንስ ትልቅ ጥፋትም እንኳን ቢሆን ያልተገባ ነገርን ከመናገር ይልቅ መመካከርን እና ለቀጣይ ስህተታችንን ማረም ላይ ማተኮር የተገባ ነው፡፡ ምክንቱም ሰውየው ያጠፋውን ጥፋት ያልተገባው ነገር አይመልሰውም ከቶም ጥፋቱ ደግሞ ላለመከሰቱ ዋስትና አይሆንምና፡፡ ይልቁን የጥፋቱን ቀጣይነት መንገድ እንዳይተርግ መጠንቀቅ ያሻል፡፡ 

በእናንተ አይታ ልብ ያላችኋቸው አስተሳሰቦች እና አሰራሮች ካሉ በዚህ ድህረ-ገጽ ፃፉልን!

አንዴ ቆም ብለህ አስብ፡-

ዛሬ አሁንኑ ልትተገብረው የምትችለው ከዚህ ጽሁፍ የተማርከው አንድ … ሁለት … ሶስት … ወዘተ ሃሳብ ምንድን ነው?  

ስላንድ ነገር ብዙ መረጃ መኖር ዕውቀት ነው፤ መረጃውን በተግባር መጠቀም ደግሞ ጥበብ ነው እና አሁንኑ ወደ ተግባር ግባ!

በጽሁፉ ላይ ተጨማሪ ሃሳብ፣ አስተያየት፣ ጥያቄ ካለ መነጋገር መርሃችን ነው፡፡

ጽሁፉ ይጠቅማል ብለው ካሰቡ ለሌሎች ያጋሩ፡፡