መነሻ ሃሳብ
የእኛ የብዙ ወላጆች የልጆቻችንን
የትምህርት ፍላጎት እና ውጤታማነት መጨመሪያ ትልቁ ብልሃት ወይም ዘዴ ልጆቻችንን ከምናውቀው ጎረቤት ልጅ ጋር በማወዳደር
እንደእርሱ እነዲሆኑ መገፋፋት እና ማበረታታት ነው፡፡
እንደ ወላጅ
ልጆቻችንን በምንም ይህይወት ዘርፋቸው (ለትምህርት፣ ለአነጋገር፣ ለተክለ-ቁመና፣ ለአካሄድ እና አረማመድ ...)፣ ለምንም
ዓላማ እና በማንኛውም መስፈርት ቢሆን ለቅጽበትም ከማንም ጋር አወዳድረን እንደ እከሌ ወይም እንደ እከሌ ልጅ መሆን አለብህ
ማለት ፈጽሞ የለብንም፡፡
ከዚህ በፊት
ሳናውቅ ብለን ከሆነ ልጆቻችን ይህንን ሀሳብ በአእምሯቸው አስቀምጠውት ስለሚሆን እና ወደ ፊት ከባድ ዋጋ ስለሚያስከፍላቸው
አሁንኑ ባስቸኳይ ቀስ በቀስ በፊት ያልናቸውን በማያስታውስ መልኩ በሂደት የማስተካከያ እርምት ማድረግ ይኖርብናል፡፡
o
በመሰረቱ እዚህ
ላይ በአንድ ነገር ላይ ግልጽ እና ለራሳችን ሃቀኛ ልንሆን ይገባል፡፡ ልጆቹን ከሌሎች ልጆች ጋር
የሚያወዳድር ወላጅ በራሱም ህይወት ሳያውቀው ይሁን እያወቀም ቢሆን የዚህ ዓይነት የውድድር እና የቅናት ሀሳብ፣ ስሜት እና
ተግባር በቅርቡ ካለው ጓደኛው፣ የስራ ባልደረባው፣ ጎረቢቱ ወዘተ ይገለጣል፡፡ እኔ ይህንን የማወዳደር ከባድ አደጋ ከመረዳቴ
በፊት ይህ የውድድር እና የቅናት ሀሳብ እና ስሜት በህይወቴ በተግባር እጅግ በጣም በሰፊው ይንጸባረቅ ነበር
እና እናንተም እንዲሁ እንዳትሆኑ ራሳችሁን ገምግሙ፡፡
ያም ሆነ ይህ
የውድድር እና የቅናት ሃሳብ፣ ስሜት እና ተግባር በእውነት ትልቅ የእግዚአብሔርን ድንቅ አሰራር ክህደት ነው፡፡ ምክንያቱም
ልጆቻችንን እና ራሳችንንም ሳይቀር እያልን ያለነው እግዚአብሔር አንተን ሲሰራህ ተሳስቷል፣ የእከሌን ልጅ ግን የሰራው በትክክል
ነው እና እንደ እርሱ ሁን እያልን ነው፡፡
ይህም ብቻ
አይደለም፡፡ እንደ ወላጅ ልጆቻችንን ከሌሎች ልጆች ጋር በማወዳደር እንደ እከሌ ልጅ መሆን አለብህ ብለን መንገር እና
ሃሳብ ማቅረብ ማለት በግልጽ አማርኛ ሲገለጽ እጅግ በጣም የምንወደውን ልጃችንን አንተ አንተን ሆነህ መፈጠር
አልነበረብህም እንደ እከሌ ልጅ ሆነህ ነበር እንጅ መፈጠር የነበረብህ እያልን ነው፡፡
በጣም የሚያሳዝነው እና ያስደነገጠኝ ነገር ደግሞ ልጆች በተለይ 3 ዓመት እና በላይ ከሆናቸው በኋላ እንዲህ አይነት ንግግሮችን የተዘዋወሪ ወይም የጀርባ ትርጉም የመረዳት ፍላጎት እና አቅማቸው ከእኛ ከወላጆች ይበልጣል፡፡ እንደ እኛ በቋንቋ ከሽነው አውጥተው ባያወሩት እና ባያስቀምጡትም በውስጣቸው ይረዱታል፡፡ እንዴት አወክ ካላችሁኝ ይህንን 7 ½ ዓመተ እና 5 ዓመት በሆኑት ሁለቱ ሴት ልጆቸ ላይ በተግባር ሁሌ ልብ ብየ እመለከታለሁ፡፡
ለማንኛውም
እኔ ይህ የውድድር ሃሳብ፣ ስሜተ እና ተግባር በገባኝ ጊዜ ቤተሰቦቸ እኔን ምን ሲሉኝ እንደነበር እና አኔም የቤተሰቦቸን
ተቀብየ ለልጆቸ እያልኩት ያለሁት ሲገባኝ አዘንኩ፡፡ ሌሎችም እንዲሁ ሊያደርጉ እንደሚችሉ በመገመት
የተረዳኋትን በዚህ መልኩ ጻፍኩ፡፡ ከዚያ የመረዳት ጊዜ ጀምሮም ባገኘሁት ሁሉ አጋጣሚ ሁለቱን ሴት ልጆቸን እና
ሌሎችንም የጎረቢት ልጆች እንዲሁም ወላጅ ጓደኞቸን በምንም ጉዳይ ላይ፣ ለምንም ዓላማ እና በምንም መስፈርት ቢሆን ልጆቻችንን
እና ራሳችንን ከሌሎች ጋር ለቅጽበትም ማወዳደር እንደሌለብን በአጽንኦት እሞግታለሁ፡፡
ምናልባት
እንዳይምታታባችሁ ልብ በሉ:: ከሌሎች ጋር በልዩ ልዩ የህይወት ዘርፎቻችን (ስለቤተሰብ አያያዝ፣ ስለትምህርት፣
ስለገንዘብ ወዘተ) እውቀት እና ልምድ መለዋወጥ እና መረዳዳት እጅግ በጣም ጥሩ ነው፡፡ እኔ እያልኩት
ያለሁት ግን ራስንም ሆን ልጆቻችንን ከሌሎች ጋር ማወዳደር እጅግ በጣም መጥፎ ነው ነው፡፡
ባጠቃላይ
ራሳችንን እና ልጆቻችንን ከሌሎች ጋር ስናወዳደር ቢያንስ የሚከተሉት አስከፊ ውጤቶች በህወታችን እና በልጆቻችን
ሕይወት ይከሰታሉ፡-
o በሌሎ መቅናት (እከሌ ታድሎ፣ እሱን ብሆን ኖሮ የሚል መሻት)
o የአሸናፊነትን ወይም የበላይነት ስሜት (በሌሎች ህይወት ውድቀት
ወይም በሌሎች ህይወት በመረማመድ የራስን ጥቅም ማስከበር ፍላጎት)
o ወደ ራሳቸው ወይም ወደ ውስጣቸው አለመመልከት (ብዙ ጊዜን የሌሎችን
ማንነት በመኮረጅ መጠመድ እና የራስን ውብ ስጦታ መርሳትን)
o ለራስ ዝቅተኛ ግምት መስጠትን ሲከፋም ራስን መጥላትን (ችሎታ የማነስ እና ያለመታደልነት ስሜት
መሰማት)
o ወዘተ … ጨምሩበት … የመሳሰሉትን ዋጋዎች ያስከፍላል፡፡
ስለዚህ ምን እናድርግ?
አጭር እና
ግልጽ መልስ፡፡ ልጆቻችን በዚያ ልናወዳድር በፈለግነው ጉዳይ ላይ የራሳቸውን እምቅ አቅም፣ ችሎታ እና ክህሎት ተጠቅመው እኛም
ረድተናቸው የተቻለውን ሁሉ እንዲያገኙ ማድረግ ብቻ፡፡
ወላጆች
ለልጆቻችን በትምህርት ወይም በሌሎችም የህይወት ዘርፎች የተሻሉ እንዲሆኑ ካለን ያላግባብ የተጋነነ ፍላጎት እና ምኞት የተነሳ
እንደ እከሌ ልጅ ሁን ወደሚለው የተሳሳተ ምክር እንገባለን እንጅ አስፈላጊውን ድጋፍ ብቻ እያደረግን ብንተዋቸው ከምናስበው
በላይ እጅግ ውብ እና ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለብዙ ሽዎች እና መቶዎች የሚተርፍ ዋጋ ይዘው ይመጣሉ፡፡
ማጠቃለያ
ከዛሬ ጀምሮ
ልጆችዎን ለምንም ዓይነት ዓላማና በምንም መስፈርት ከሌሎች ልጆች ጋር አያወዳድሩ፡፡
ይልቁንም
ልጆችዎን ለቅጽበትም ሳይታክቱ በየቀኑ መርዳት ያለብዎትን ነገር ከመርዳት ወደ ኋላ አይበሉ፡፡
ካልሰነፉ
በስተቀር ትልቅ ደረጃ ያሉ ሰዎችን አማካሪ ባይሆኑም እንኳ ከዚህ ቅጽበት ጀምረው የልጆችዎ
ሁነኛ የህወት አማካሪ መሆን ይችላሉ፡፡
አንዴ ቆም ብለህ አስብ፡--
o ዛሬ አሁንኑ
ልትተገብረው የምትችለው ከዚህ ጽሁፍ የተማርከው አንድ … ሁለት … ሶስት … ወዘተ ሃሳብ ምንድን ነው?
o ስላንድ ነገር ብዙ መረጃ መኖር ዕውቀት ነው፤ መረጃውን
በተግባር መጠቀም ደግሞ ጥበብ ነው እና አሁንኑ ዕውቀቱን በተግባር በመጠቀም አንድ እርምጃ ወደ ፊት
አስተያየት ተጨማሪ ሃሳብ እንዲሁም ጥያቄ ካልህ በዚሁ
ድህረ-ገጽ ፃፉልን!
ልጆች ድንቅ
የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው!!!
መልካም ጊዜ
ከውድ ልጆዎ ጋር!
2 አስተያየቶች
በየቀኑ ልጆቼን ለመርዳት አቅድ ያስፈልገው ይሆን? ነው በተመቸኝ ? ምንስ ነው ይምረዳቸው? ልምዳችህን ኣካፍሉኝ።
ምላሽ ይስጡሰርዝውድ የድህረ-ገጻችን ተከታታይ ጽሁፋችንን ስላነበቡ ከልብ እያመሰገን፣ ለጥያቄዎ በጥቂቱም ቢሆን መልስ እነሆ፡-
ምላሽ ይስጡሰርዝበየቀኑ ልጆቼን ለመርዳት አቅድ ያስፈልገው ይሆን? ነው በተመቸኝ?
ዕቅድ የሚያስፈልጋቸውም አሉ ለምሳሌ፡-
o ለልጆች መንፈሳዊ እና ዓለማዊ ተረቶችን ማንበብ
o የት/ቤት ትምህርታቸውን ማስጠናት
o ከተቻለ ስለ ህይወት ስኬት የሳምንት የወር ትምህርት በቤት ውስጥ በራስ ተነሳሽነት ማስተማር
o ውይይት ከልጆች ጋር ማካሄድ
o ምንም ያልተሸራረፈ እና ጥሩ ጊዜ ለልጆች መስጠት/መመደብ
ዕቅድ የማያስፈልጋቸውም አጋጣሚዎች አሉ ለምሳሌ፡-
o ለልጆች ምንም አይነት መስፈርት ወይም ቅድመ-ሁኔታ የሌለው ፍቅር መስጠት
o ልጆች ስለ ነገሮች የተዛባ አመለካከት ባሳዩ አጋጣሚ ማስገንዘብ ለምሳሌ፡-
o የጾታን ልዩነት በተዛባ መልኩ ሲያንጸባርቁ ባየን አጋጣሚ እውነታውን ማስገንዘብ
o ራሳቸውን ሲኮንኑ/ሲወቅሱ/ሲያሳንሱ ባየን አጋጣሚ ራስን ስለመኮነን/መውቀስ/ማሳነስ ስላለው ጉዳት ማስረዳት
o ስህተታቸውን መቀበል ሲቸገሩ ስናይ፣ በቀላሉ ተስፋ ሲቆርጡ ስናይ፣ ለስራ ሲያመነቱ ስናይ ... ስህተት ለመማር መልካም አጋጣሚ መሆኑን፣ በማንኛውም ሁኔታ ተስፋ መቁጥ አማራጭ እንዳልሆነ ይልቁንም እንደገና ደግሞ መሞከር እና በጥረት ማመን እንዳለባቸው ማስገንዘብ ለዚህም እንደነ ቶማስ ኤድስን የኤሌክትሪክ መብራትን ለመስራት አንደ ሽ ጊዜ እንደሞከረ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ታሪኩን ማስገንዘብ፣ ስራን በርትቶ መስራ የልጆችም ሆነ የሰዎች የመሻሻያ መንግድ እንደሆነ ማስገንዘብ
o ... ወዘተ ሌሎችንም አጋጣሚዎች መጠቀም እኒህ የተዘረዘሩት ለናሙና ያህል እና ለማሳያ የህል ናቸው
ምንስ ነው የምረዳቸው? ልምዳችህን ኣካፍሉኝ።
o የግል ተሞክሮዎቻችን ከላይ የተዘረዘሩት በታቀደ እና ባልታቀደ መልኩ የተባባት ጥቂቶቹ ናቸው