የመነሻ ሃሳብ

ሰው በዚህ ምድር ሲኖር፣ በተለይም በአሁኑ ሰዓት ከተግዳሮቶች እና ከገጠመኞች ነፃ መሆን አይችልም፡፡ ይሁን እንጅ ሰው በህይወቱ ዘወትር የሚገጥሙትን ተግዳሮቶች እና ገጠመኞች ከፈለገ ለዕድገቱ ወይም ለህይወቱ መሻሻል አሊያም ለህይወቱ ውድቀት መጠቀም ሙሉ ፈቃድ፣ ነፃነት እና ችሎታ አለው፡፡ 

በመሆኑም ሰው ገጠመኞች በአግባቡ ለማስተናገድ እና ብሎም ለበጎ ለመጠቀም ትልቁ ትኩረት ተግዳሮቶች የሚያሳድሩት አሉታዊ ውጤት ላይ  ሳይሆን ከተግዳሮቶች ሊማር የሚችለውን ትምህርት ማስተወል፣ በተግዳሮቶች እና በገጠመኞች መካከል ተቋቁሞ የተሻለ ውሳኔ በመወሰን ወደ መልካም አጋጣሚ የመቀየር እና ተግዳሮቶች እና ገጠመኞችን የመቋቋም ክህሎቶችን ማዳበር መሆን አለበት፡፡

ሰው ማህበራዊ ፍጡር እንደመሆኑ ከሌሎች ሰዎች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ተጋምዶ መኖር የግድ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ዕለት ተዕለት ከሚገጥሙት ተግዳሮቶች እና ገጠመኞች ብዙዎች ከሰዎች ጋር ካለው ግንኙነቱ ይመነጫ፡፡

ለዚህ ማሳያ በጣም ቀላል ግን በጣም አስረጅ የሆነውን እና ዕለት ከዕለት የሚገጥመንን ስድብን አሉታዊ ትችትን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፡፡ ከላይ እንደተገለጽው ሰው ማህበራዊ ፍጡር እንደመሆኑ የየዕለት ውሎው ከባለቤቱ፣ ከቤተሰቦቹ፣ ከጎረቤቶቹ፣ ከባልደረቦቹ ... ወዘተ ያለው ግንኙነት ከህይወቱ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ከተጠቀሱት ሰዎች ጋር በተለያዩ ምክንያቶች አለመግባባት ይፈጠር እና ስድብ አሉታዊ ትችትን እንቀበላለን፡፡ በዚህም ጊዜ ለስድቡ እና ለትችቱ የተለያዩ ምላሾች እንሰጣለን፡፡

ልብ ልንለው የሚገባው ነገር ይህ ስድብ አሉታዊ ትችት እኛን የሚገልጽ ወይም እኛን የማይገልጽ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ስድቡ አሉታዊ ትችቱ የምንሰጠው ምላሽ የሚወሰ ስድቡና አሉታዊ ትችቱ እኛን በመለጹ እና ባለመግለጹ ሳይሆን እኛንም ሆነ ተሳዳቢውን በሚያስተምር መልኩ መሆን አለበት፡፡ ለዚህም ለስድቡና ለአሉታዊ ትችቱ በአእምሯችን ምንሰጠው ትርጉም ወሳኝ ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ ለተሰነዘረብን ስድብ አሉታዊ ትችት ምላሽ ለመስጠት ሁለት አማራጮች አሉን፡፡  

መጀመሪያ ስድቡ አሉታዊ ትችቱ የሚገልጸን ከሆነ መልካም፡፡

ትክክለኛው እና የጠበበው መንገድ ስድቡ አሉታዊ ትችቱ የሚገልጸን ከሆነ ይህንን ስድብና አሉታዊ ትችቱ ልክ እንደ ትምህርት እና መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ክፍተቶቻችንን ለማረም መወሰን፣ ማቀድ እና ማረም ነው፡፡ ምክንያቱም ክፍተታችንን ማንም ወዳጅ ጓደኛችን ቢሆን በመደበኛው አይነግረንም፡፡ ይልቁንም ይህ በእኛ የተናደደው ሰው እኛን ለማናደድ እና ለመጉዳት ብሎ ቢሆንም በዚያ አጋጣሚ በቀላሉ ከማንም የማገኘውን ትምህርት ስለራሳችን ክፍተት አስተማረን ብለን ብንወስደውስ? እንችላለን፣ ይህን ማድረግ ሙሉ በሙሉ የራሳችን ምርጫ ነው፡፡

የተለመደው እና ብዙዎቻችን የምናደርገውን የምንከተለው ሰፊው መንገድ ነው፡፡ አሉታዊ ትችቱን ስድቡን ወደ ውስጣችን በማስረጽ ስድቡ ትችቱን የሚገልጸን ከሆነ እከሌ እኮ እንዲህ አለኝ እያልን ለራሳችን፣ ለጓደኞቻችን ... ላገኘነው ሁሉ መወትወት ነው፡፡ በዚህም ከተተቸነው የበለጠ ራሳችን ትችቱን ለአእመሯችን በመደጋገምና በማስገንዘብ ራሳችን በራሰችን ላይ ንዴትን፣ በቀልን ዘንን፣ መቃጠልን እንፈጥራለን፡፡ ይሁን እንጅ አእምሯችንን በአግባቡ መጠቀም እና ስሜቶቻችንን ባግባቡ ማስተዳደር ከቻልን ማንም ሰው በምንም መንገድ እኛን ዝቅ ማድረግ አይችልም፡፡ ራሳችን እያወቅን በንቁ አዕምሯቸን ወይም ሳናውቅ በድብቁ አዕምሯቸን ካልፈቀድንለት በስተቀር፡፡  

የሁለተኛው ስድቡ አሉታዊ ትችቱ የማይገልጸን ከሆነ መልካም፡፡

ስድቡ አሉታዊ ትችቱ የማይገልጸን ከሆነ ደግሞ ልክ አንድ ስለ እኛ ምንም መረጃ የለው መንገደኛ ሰው ወይም ህፃን በሉት ... እንደተናገረ በመቁጠር ነው:: አንድ ገና የማያገናዝብ ህፃን ወይም ምንም የማታውቁት ሰው በመንገድ አግኝቷችሁ የፈለገውን ቢሰድባችሁ ምናልባት ጊዚያዊ ስሜታዊነት ይሰማችሁ ይሁናል እንጅ ከጠቂት ቆይታ በኋላ ልታስቡት እና ቂም ልትይዙ ግን አትችሉም፡፡ እናንተ የምታውቁት እና የሚያውቃችሁ ሰውም ቢሆን የፈለገውን ቢሰድባችሁ በእውነት እናንተ በምታውቁት እናንተን የማይገልጽ ከሆነ ተገቢውን ቃል ተጠቅማችሁ ጉዳዩ እንደማይገልፃችሁ አስረዱት፡፡ ከተረዳችሁ መልካም፡፡ ካልተረዳችሁ ግን ልክ ህፃኑ እና የማታውቁት መንገደኛ እንደሰደባችሁ ቁጠሩት እንጅ ከተሰደባችሁት በላይ ሃሳቡን ለራሳችሁ በማውጣ በማውረድ ራሳችሁን አትጉዱ፡፡ ይህንን እሳቤ ስትረዱ እና ስትተገብሩ የምታተርፉት ነገር ቢኖር ራሳችንን ላስፈላጊ ቁጣ፣ ንዴት፣ በቀል እና ከመሳሰሉት መጠበቅ ነው፡፡ ይህ ራስን መሸወድ ወይም ማታለል አይደልም፡፡ እውነታ ነው ምክንያቱም ስለ እኛ ስለራሳችን ከማንም የበለጠ ራሳችን እናውቃለን:: 

ማንም ሰው ስለ እኛ የተናገረው ሁሉ ትክክል ሊሆን አይችልም፡፡ በመሆኑም ማንም ሰው ስለ እኛ በተናገረ ቁጥር መናደድ፣ መቆጣት፣ ማዘን ግድ አይደለም የራሳችን ፈቃድ እንጅ፡፡ ይሁንና ይህ የሌሎችን ትች ወይም ስድብ ራስንም ሆነ ሌሎችን ሳይጎዱ በአግባቡ የማስተናገድ ስልት /ክህሎት/ በአንድ ሌሊት አይመጣም፣ በተደጋጋሚ እና ባላሰለሰ የዘወትር ጥረት እንጅ፡፡ ሮም ባንድ ቀን አልተገነባችምና፡፡ ስለሆነም ይህንን ክህሎት ከዛሬ አሁን ጀም በተግባር መለማመድ እንጀምር፡፡

በጣም የሚገርመው ብዙዎቻቸን ይህ ስድቡ አሉታዊ ትች የማይገልጸንም ሆኖ ሳለ እእኳን ሳይቀር የምንከተለው የተለመደውን እና ሰፊውን መንገድ ነው፡፡ ማለትም እከሌ እኮ ምንም በማይመለከተኝ ወይም ያልሆንኩትን እንዲህ ... አለኝ እያልን ለራሳችን መደጋገም፣ ለጓደኞቻችን ... ላገኘነው ሁሉ መወትወት ነው፡፡

በዚህም የተነሳ የተሰደብነው እና የተተቸነው እኛን የማይገልጽ መሆኑን እያወቅን ሳለ ጭራሽ ያንን ስድብ እና ትችን ለአእመሯችን በመደጋገምና በማስገንዘብ አንድም ስድቡ የማንነታችን መገለጫ እናደርገዋለን እንዲሁም ራሳችን በራሰችን ላይ ንዴትን፣ በቀልን፣ ሃዘንን፣ መቃጠልን እንፈጥራለን፡፡ በአእመሯችንም ስንት የሚጠቅመንን ሃሳብ ማሰላሰል እና ማሰብ ስንችል ይህንን የሚጎዳንን ሃሳብ እናወጣ እናወርዳለን፡፡ ለዚህም ነው ይቅርታ የሚያደርግ ምስጉን ነው የተባለው፡፡ በእርግጥ ባያደርግ ጉዳቱ ለራሱ ነው፡፡

በጣሊያን አገር፣ ሞሊሴ ከተማ ከሳምንት በላይ በቆየው የበረዶ ክምር (የካቲት 2014 ዓ.ም ለትውስታ)



በመሰረቱ ውድ አንባቢ ይህንን ስድብ እና አሉታዊ ትችት እንደተግዳሮት እና ፈተና ተቆጥሮ በዚህ ደረጃ ትኩረት ሰጠው ሊገርምህ ይችላል፡፡ ነገር ግን ልብ ካልነው ስንቶቻችን በባለጉዳዮቻችን፣ በደንበኞቻችን፣ በባለቤቶቻችን፣ በባልደረቦቻችን፣ ባለቆቻችን፣ በጓደኞቻችን ... ባለመግባባት ተሰድበን እና አሉታዊ በሆነ መንገድ ተተችተን በአእምሯችን ስናሰላስል እንደምንውል እግዚአብሔር ይወቀው፡፡ 

እኔ በራሴ ሙከራ አድርጌ ውጤቱን አይቸዋለሁ፡፡ የምፈልገውን ስራ እንዳልሰራ እና አእምሮየን ባግባቡ ከማልጠቀምባቸው የህይወት አጋጣሚዎች አንዱ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ለምሳሌ የተለያዩ የጥናት ጽሁፎች፣ ንድፈ ሃሳቦች ... ወዘተ በማቀርብበት ጊዜ የተሰጠዋቸውን አሉታዊ ትችቶች ከሳምንት በላይ ሳሰላስል ጊዜ እና ትኩረቴን ያጠሁባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉኝ፡፡ ይህንን ጉዳይ ተገንዝቤ አስፈላጊ ማስተካከያ እያደረኩ ካለሁበት ጊዜ ጀምሮ ምን ያህል ጊዜ እና ትኩረት እንዳተረፍኩ እና ምን ያህል ስዕብናየን እንዳስተካከልኩ እግዚአብሔር እና እኔ ነን የምናውቀው፡፡

ላንተም እስኪ የቤት ስራ ልስጥህ፡፡ ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ ሶስት ቀናት መድብ እና ሆነ ብለህ በመሰደብ፣ በመተቸት እና ባለመግባባት ምክንያት ያንን ስድብ እና ትችት በውስጥህ በማሰላሰል የቀንህ ምን ያህል ጊዜ እና ትኩረት እንደምታባክን እና ምን ያህል ስዕብናህን ክፉኛ እንደተቆጣጠረው ሙከራ አድርግና ያኔ መነጋገር እንችላን፡፡ ከምታደርገው የራስህ ሙከራ በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዚህ ምክንያት ምን ያህል ጊዜ እና ትኩረት በየቀኑ እንደሚባክን የጥናት ውጤቶችን ብታነብ ከዚያም ምን ያህል ትኩረት መስጠት እንዳለብህ መገንዘብ ትችላለህ፡፡ 

በህይወታችን ምንም ዓይነት ተድዳሮ ፈተና ቢገጥመንም ዋናው ነገር የገጠመን ፈተና ዓይነት እና ክብደት ሳይሆን እኛ ለፈተናው የምንሰጠው ውስጣዊ ትርጉም እና ምላሽ ነው፡፡ ይህም የሚያሰላስል አእምሮ ከተሰጠንበት ምክንያቶች አንዱ ነው፡፡

በመሆኑም ማንኛውንም ዓይነት ፈተናና ገጠመኝ ሲገጥመን በመጀመሪያ የፈተናውን ዓይነት እና ክብደት ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ማገናዘብ፣ ከፈተናው ልንማረው የምንችለውን ቁምነገር ልብ ማለት:: በመቀጠልም ብዙዎች የሚያደርጉትን እና በቀላሉ የመጣልንን ምላሽ ሳይሆን ለህይወታችን የሚጠቅመንን እና የመናተርፍበትን ምላሽ መምረጥ እና መከወን ሙሉ ለሙሉ በእኛ ምርጫ እና ቅጥጥር ስር መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው፡፡  

ይህን ማድረግ ልምምዳችን ካደረግን ልን እያደርን ለመለወጥና የተለ ሰው ለመሆን ምንም ዓይነት ፈተና እንደማያግደን እንገነዘባለን፡፡ ለመለወጥ እንደ ተግዳሮት አድርገን ያስቀመጥናቸው ነገሮችም ማናልባት ለጊዜው ሊገዳደሩን ቢችሉም ከመለወጥ ሊያግዱን እንደማይችሉና መቋቋ እንደምንችል፣ እንዲያውም ወደ መልካም አጋጣሚ መለወጥ እንደምንችል በተግባር ይገባናል፡፡ ስለሆነም ከዛሬ ጀምሮ በየቅጽበቱ ከሚገጥሙን ትናንሽ ከሚመስሉ ግን ህይወታችንን በሚወስኑ ፈተናዎች ልምምድ እናድርግ፡፡

ባጠቃላይም ይህን ልምምድ የዘወትር ተግባራችን ካደረግን ምንም ዓይነት ፈተና ይሁን መሆን፣ ማድረግ እና እንዲኖረን የምንፈልገውን ነገር ከመሆን፣ ከማግኘት እና ከመስራት የሚያግደን አንዳች ፈተና አይኖርም፡፡ እኛ ከፈተናዎች ሁሉ በላይ ነንና፡፡ፈተናዎች አያድጉም እኛ ግን በሚገጥሙን ፈተናዎች መሰረት የተለ ልምድ፣ አስተሳሰብ፣ ስዕብና ... በማዳበር እንፈታቸዋለን:: 

በአጠቃላይ በህይወታችን ፈተና ሲገጥመን የሚከተሉትን ልብ እንበል፡-

ሰው ከማንኛውም ተድዳሮና ፈተና በላይ መሆኑን መረዳት፡፡

ሁል ጊዜ ተድዳሮት እና በፈተና ውስጥ የማደግ እና የመሻሻል ዕድል እንዳለ ማስተዋል፡፡ 

የማንኛውም ተድዳሮት እና ፈተና መፍትሄ እንዳለው ለራሱ ማስገንዘብ፡፡

በእውኑ ፈተናው ከአቅ በላይ ከሆነ እግዚአብሔር በፈተናው የምናልፍበት በብና ማስተዋል እንደሚሰጠው ማመን፡፡

የማጠቃለያ ሃሳቦች

ሰው ከህይወት ፈተናና እና ገጠመኞች ነፃ መሆን አይችልም፣ ሊያደርግ የሚችለው ፈተናናዎችን ባግባቡ መያዝ እና ብሎም እንደመልካም አጋጥሚ መጠቀም ነው፡፡

ምንም ዓይነት ፈተናና ገጠመኝ ቢገጥመንም ዋናው ነገር የገጠመን ፈተናና ገጠመኝ ዓይነት እና ክብደት ሳይሆን እኛ ለፈተናው የምንሰጠው ውስጣዊ ትርጉም እና ምላሽ ነው፡፡


አስተያየት ተጨማሪ ሃሳብ እንዲሁም ጥያቄ ካላችሁ በዚሁ ድህረ-ገጽ ፃፉልን!