መነሻ ሃሳብ
ልጅነት እጅግ በጣም ድንቅ የህይወት ክፍል ነው፡፡ ልጅነት የፈጣሪውን ማንነት የሚያነንጸባርቅ ድንቅ ማንነት ነው ማለትም መልካም፣ መጨነቅ የማያውቅ ይልቁንም ነፃና ደስተኛ፣ ሰዎችን ሙሉ ለሙሉ የሚያምን፣ ምንም ተንኮል፣ ክፋት፣ ቅናት ... ወዘተ ጨምሩበት የማያውቀው ድንቅ ማንነት ነው፡፡
ልጅነት ፈሳሽ ማንነት ነው፡፡ ፈሳሽ ልክ የመያዣ ዕቃውን ቅርጽ እንደሚይዝ ሁሉ ልጅነትም በቅርቡ ሆኖ የሚያየውን ሰው ሙሉ ማንነት ይሆናል፡፡ በቅርቡ ያሉት ሰዎች ማንነት ልክ ብርጭቆ የውሃን ቅርጽ እንደሚወስን ሁሉ እነሱም የልጆችን ማንነት በራሳቸው አምሳል ይቀርጹታል ማለት ነው፡፡ ይህንን እውነታ ወላጆች እና ማንኛውም ልጆችን በቅርብ ሆነው የሚያሰድጉ ሰዎች በሚገባ ሊረዱት ይገባል፡፡
ልጅነት እና ስኬት
ወደ ርዕሰ-ጉዳያችን ለመምጣት አንዴ ወደ ልጅነታችን ወይም ልጆች ካሉን ወደ ልጆቻችን ህይወት መለስ እንበል:: በህፃንነታችን ለመዳህ፣ ለመቆም፣ በእግራችን ለመሄድ፣ ለመሮጥ፣ ለመናገር፣ ት/ቤት ገብተን ፊደላትን ለመለየት፣ ለማንበብ፣ ለመፃፍ፣ ... ወዘተ ጨምሩበት ምን ያህል ጊዜ ወስዶብናል? መልሱን ሳምንታት፣ ወራት፣ ዓመታትም ጭምር እንደምትሉ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን የህይወት ልምምዶች ለማሳካት ምን ያህል ጊዜስ ሞክረናል?
መልሱን ለመቁጠር የሚያዳግት ያህል እጅግ በጣም ብዙ ጊዜ ግን ያን የፈለግነውን ነገር በአስተማማኝ ሁኔታ እስከምንችለው ድረስ እንደምትሉ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
የልጅነት ማንነትን መነጠቅ
ታዲያ ስናድግ እና ማገናዘብ ስንጀምር ያንን ድንቅ ማንነት ማለትም መልካም፣ ነፃና ደስተኛ፣ ቅን፣ ርህሩህ፣ ትሁት፣ ሃቀኛ፣ ታታሪ ምንም ደከመኝ እና ሰለቸኝ የማይለው እና ውድቀትን የማይፈራው የህፃንነታችን ለመዳህ፣ ለመቆም፣ በእግራችን ለመሄድ፣ ለመሮጥ፣ ለመናገር፣ ት/ቤት ገብተን ፊደላትን ለመለየት፣ ለማንበብ፣ ለመፃፍ፣ ... ወዘተ ተደጋጋሚ እና ያላሰለሰ ጥረታችንን ወዴት ጠፋብን?
የምንፈልገውን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ዓላማችን ግብ እስከሚመታ ድረስ የማንሞክር ስለምንድን ነው? ይህ ብቻም አይደለም፡፡ ያ መልካም፣ መጨነቅ የማያውቅ ይልቁንም ነፃና ደስተኛ፣ ሰዎችን ሙሉ ለሙሉ የሚያምን፣ ምንም ተንኮል፣ ክፋት፣ ቅናት … ወዘተ ጨምሩበት የማያውቀው የፈጣሪውን ማንነት ሙሉ በሙሉ የሚያንጸባርቀው የህፃንነት ማንነታችን ዛሬ ስናውቅ የት ሄደብንና ነው ተንኮለኛ፣ ክፉ፣ ቅናተና … ወዘተ የሆንነው? ይህንንስ ማንነት ከየት አመጣነው?
ብዙዎቻችን እኛ ሰዎች እያደግን ስንመጣ ባቅራቢያችን በነበሩ ሰዎች፣ በት/ቤቶች፣ በዙሪያችን እና አካባባቢያችን ባሉ ሰዎች
… ወዘተ የተነጠቅነው ትልቁን እና እንደ ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ያለውን ውብ እና ድንቅ ማንነታችን ነው፡፡ ትልቁ የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ግን ያንን የልጅነት ማንነታችን በማንሳት በናፍቆት ማሰብ እና መለያየት ሳይሆን ያንን እጅግ ውብ እና ድንቅ የህፃንነት ማንነት እንዴት ዛሬ መልሰን እናግኘው ነው እና ጽሁፉን እስከ መጨረሻው በትኩረት ያንብቡ፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ እንደተፃፈው እንደህፃናት ካልሆናችሁ መንግስተ-ሰማያትን አትወርሱም የሚለው የእግዚአብሔር ቃል መሠረትም ይህ ነው፡፡
የልጅነት ማንነትን መልሶ ማግኘት ወይም መሆን
ዛሬስ አሁን ላይ መሆን፣ ማግኘት እና መስራት በምንፈልገው ማንኛውም ነገር ላይ ያ የልጅነታችን የማወቅ፣ የመሞከር እና የመስራት ጉጉት፣ ያላሰለሰ ተደጋጋሚ ሙከራ እና ደግነት፣ አዎንታዊ አሳቢ፣ ቅንነት … ወዘተ ማንነት ... መልሰን ማግኘት ብችልስ?
ይህ ጥያቄ ከላይ ከላዩ ሲታይ ተራ ይመስላል፡፡ ልብ ላለው ግን እጅግ በጣም አስተማሪ እና ህይወት ቀያሪ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ አሁን ያንን ማንነት እንዴት መልሰን ማምጣት እንደምንችል ልንነጋገር ስለሆነ ይህንን ጽሁፍ በሙሉ ትኩረት ሆናችሁ ማንበብ ቀጥሉ፡፡
ያ ጥልቅ የመስራት፣ የመሞከር፣ ውድቀትን እንደምንም የማይቆጥር፣ ብሳሳትስ ሰዎች ምን ይሉኝ ብሎ የማይፈራ እንዲሁም ደግ፣ ቅን፣ አዎንታዊ ብቻ አሳቢ፣ የማይጨነቅ፣ ሁሌ ደስተኛ የሆነው የህፃንነት ማንነታችን ነበር፡፡ ዛሬ ወዳለው ፍልጎት አልባ፣ ምንም ሳይሞክር የሚደክም እና በቀላሉ ተስፋ የሚቆርጥ፣ መውደቁ እርሱን ከሚጎዳው በላይ ሰዎች ምን ይሉኝ ብሎ የሚጨነቅ፣ እንዲሁም ተንኮለኛ፣ ጨለምተኛ፣ በአብዛኛው አሉታዊ አሳቢ፣ ጭንቀታም... (ጥሩ ላልሆኑ ቃላቶች ይቅርታ እጠይቃለሁ፤ ብዙዎቻችንን ቢያንስ ራሴን የሚገልጽ ሆኖ ስላገኘሁት ነው) የሆነን የማንፈልገው ማንነት ከየት እና እንዴት ገነባነው ወይም እንዴት አገኘነው?
ይህ የማንፈልገው ማንነታችን ግንባታ ከላይ እንደገለጽነው መንስኤው ልምምድ ሲሆን ውጤቱ ድግሞ ልማድ ነው፡፡ ልምምድ እና ልማድ ከሰው ልጆች ህይወት ተነጥለው የማይታዩ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች እና ወሳኝ የህይወት መንስኤ-ውጤት ጥምሮች ናቸው፡፡ ስለሆነም ዛሬ ላይ የሆንነው የማንፈልገው ማንነታችን የተገነባው በቅርባችን በነበሩ ሰዎች (ወላጅ፣ አሳዳጊ፣ ተንከባካቢ)፣ በት/ቤቶች፣ በዙሪያችን እና አካባባቢያችን በነበሩ ሰዎች … በተደጋጋሚ በነገሩን፣ ባስተማሩን፣ ባሳዩን፣ ባሰሙን (ልምምድ-ልማድ) መሰረት ነው፡፡
ይህ የማንፈልገው ማንነታችን ባልታወቀ እና ባልታቀደ መልኩ በዚህ ደረጃ ከተገነባ በእውቀት ተመስርተን እና አቅደን የምንፈልገውን አዲስ ማንነት መገንባት እንችላለን፡፡ ሂደቱም ልክ ይህ የማንፈልገው የዛሬው ማንነታችን በመጣበት መንገድ ሌላ የምንፈልገውን አዲስ ማንነት መልሰን መገንባት ነው፡፡
በመጀመሪያ መሆን የምንፈልገውን ሌላ አዲስ ማንነት በጥንቃቄ መወሰን፡፡
በመቀጠልም ያኔ በቅርባችን፣ በዙሪያችን፣ ት/ቤታችን … የነበሩ ሰዎች በተደጋጋሚ በመንገር፣ በማሳየት እና በመሆን (በልምምድ እና በልማድ) የማንፈለገውን ማንነት እንደገነቡልን ሁሉ ዛሬ ደግሞ እኛ የምንፈለገውን ሌላ አዲስ ማንነት ራሳችን ለራሳችን በተደጋጋሚ በመንገር፣ በምናብና በማየት እና በአካል በመሆን (በልምምድ እና በልማድ) መገንባት ብችልስ?
ይህ እኛ የምንፈለገውን ሌላ አዲስ ማንነት ተደጋጋሚ ልምምድን እና ልማድ መገንባትን ቢፈልግም ግን መገንባት በጣም ይቻላልና እናስብበት፡፡ መሆን፣ ማግኘት እና መስራት የምንፈልገው ማንኛውም ነገር (ትንሽ ወይም ትልቅ) ከልምምድ እና ልማድ ሃይል በላይ የሆነ አንዳች ነገር የለምና መሆን የምንፈልገውን ሌላ አዲስ ማንነት በዝርዝር በመግለጽ የአዲስ የማንነት ግንባታውን ዛሬ አሁንኑ እንጀምር፡፡
ባጠቃላይም ስልታዊ ማሰብን ጨምረንበት የልጆችን ሙሉ ማንነት የእኛ ማንነት ማድረግ ከቻልን በህይወታችን በፈለግነው መጠን ስኬማ መሆን እንችላለን፡፡
እኔ በበኩሌ ይህንን ጽንሰ-ሃሳብ ከተረዳሁበት ዕለት ጀምሮ በእያንዳንዷየቀን ውሎየ እና ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ ሙከራ እና ልምምዴ የልጆችን ማንነት መላበስ ሆኗል፡፡ ማለትም መሻሻል በምፈልገው ነገር ላይ ብዙ ጊዜ መሞከር፣ ነፃ መሆን፣ ራስን መሆን፣ ባለኝ ነገር መደሰት፣ ለነገሮች ያለኝን አትኩሮት እና ጉጉት መጨመር፣ በማንኛውም ሁኔታ እውነትን መናገር፣ ሰዎችን እኩል ማየት፣ ባመንኩበት ጉዳይ ላይ እስከመጨረሻው መጽናት … የእናንተን ጨምሩበት እያደረኩ ነው፡፡
እናንተስ?
አንዴ ቆም ብለህ አስብ፡--
o አሁንኑ ልትተገብረው የምትችለው ከጽሁፉ የተማርከው አንድ ... ሁለት ... ሶስት ... ወዘተ ሃሳብ ምንድን ነው?
o ስላንድ ነገር ብዙ መረጃ መኖር ዕውቀት ነው፤ መረጃውን በተግባር መጠቀም ደግሞ ጥበብ ነው!
አስተያየት፣ ተጨማሪ ሃሳብ እንዲሁም ጥያቄ ካላችሁ በዚሁ ድህረ-ገጽ ፃፉልን!
2 አስተያየቶች
አሁን ወደ መሃል እየምጣህልኝ ነው፡፡
ምላሽ ይስጡሰርዝStep-1. በቅርባችን፣ በዙሪያችን፣ ት/ቤታችን … የነበሩ ሰዎች በተደጋጋሚ በመንገር፣ በማሳይት እና በመሆን (በልምምድ እና በልማድ) የማንፈለገውን ማንነት……………old software. Very very dangerous software. It is full of toxic data. Just I am trying to list down them, and then I will go to step-2
Step-2.የምንፈልገውን ሌላ አዲስ ማንነት በጥንቃቄ መወሰን, this will be my second activity. It needs detail outline and reading. It must be supported by different reading materials and model personal experts, and then I will go to step-3
Step-3. አዲስ ማንነት መገንባት፡፡ uploading new software. I will add very important data for the new software step by step. This is a challenging part. It is not easy as what write. It must be step by step. It needs perseverance. I am trying it
I am happy if you are able to come up with those important data needed for the new software. i am not saying that they are similar for all people, but there are commons.
በቅድሚያ ውድ አንባቢዎቻችን አዲስ ማንነትን ለመገንባት ሶሰቱን ሂደቶች ግልጽ አድርገው ስላስቀመጧቸው እና ተጨማሪ መረጃ ስለጠየቁን ከልብ እናመሰግናለን፡፡
ምላሽ ይስጡሰርዝበመቀጠል ምንም እንኳ ጥያቄዎትን በእንግሊዝኛ ቢያቅርቡም (የአንባቢዎች ጥያቄዎትን አስተያየቶች በእንግሊዝኛም ሆኑ በአማርኛ በጣም ደስተኛ ነን) የድህረ-ገጹ ዋና የስራ ቋንቋ አማርኛ በመሆኑ መልሱን በአማርኛ ማቅረብ ወደድን እና ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡
ካልተሳሳትኩ (ጥያቄዎን ባግባቡ ካላገኘሁት ማስተካከያ በሙሉ ልብ እቀበላለሁ) ከጥያቄዎት እንደተረዳሁት የሶስተኛው ሂደት ላይ ተጨማሪ ሃሳብ እንደሚፈልጉ ነው፡፡ ይህ የሶስተኛው ሂደት ልክ እንደገለጹት በህይወት መተግበሩ እንደ መፃፉ ቀላል አይደለምና ለከፍተኛ ጥረት ራስን ማዘጋጅት ይበጃል፡፡
ይህ በአንዲህ እናዳለ እንግዲህ እንደምናውቀው እና በዚህ ድህረ-ገጽ በመጀመሪያ በለቀቅነው ጽሁፋችን https://alebachew-tadie.blogspot.com/2022/10/blog-post.html እንደተገለጸው ማንነት ስዕብና፣ የልቦና ውቅር፣ እምነት እና ልማድ ወዘተ ሊገለጽ ይችላል፡፡
ስለዚህ አዲስ ማንነት መገንባት ማለት ከላይ የተገለጹትን የማንነት ዘርፎች ማለትም ስዕብና፣ የልቦና ውቅር፣ እምነት እና ልማዶቻችንን ወዘተ የምንፈልጋቸውን ዓይነት እና መጠን ማድረግ ማለት ነው፡፡ በእርግጥ እነዚህ የማንነት ዘርፎች እያንዳንዳቸው በእያንዳንዱ የህይወት ዘርፎቻችን (ቤተሰብ፣ ግንኙነት፣ ገንዘብ፣ ትምህርት፣ መንፈሳዊነት፣ ስራ …) አንፃር ሲታዩ እጅግጥልቅ እና ሰፊ ናቸው፡፡
ስለሆነም የምንፈልገውን አዲስ ማንነት ማለትም ስዕብና፣ የልቦና ውቅር፣ እምነት እና ልማዶቻችንን ለመገንባት እያንዳንዳቸውን ከህይወት ዘርፎቻችን አንፃር በመፈተሽ አሁን ላይ ያለንበትን ደረጃ መገምገም እና መገንዘብ ሂደቱን ቀላል እና ግልጽ ያደርገዋል፡፡
ጥያቄውን በግልጽ ለመመለስ ከተጠቀሱት የማንነት ዘርፎች በአንዱ (ስዕብና) ላይ እያደረኩ ያለሁትን የእኔን ግላዊ ተሞክሮ ላቅርብ፡፡
ስዕብና ባህሪያችንን፣ አስተሳሰባችንን እና ተግባራችንን ይወክላል፡፡ እናም የየቀን እና የየቅጽበት ባህሪየ ምን እንደሆነ ከገመገምኩ በኋላ ምን ዓይነት ባህሪ ሊኖረኝ እንደምፈልግ የስኬታማ ሰዎችን ባህሪ በመፈተሽ እወስናለሁ፣ እዘረዝራቸዋለሁም፡፡
በመቀጠል ዝርዝራቸው ብዙ ማለትም ከሶስት በላይ ከሆኑ በአንድን ጊዜ ማለትም ለመጀመሪያዎቹ ከሁለት-ሶስት ሳምንታት ከሶስት ያልበለጡ በቅድሚያ አስፈላጊ የሆኑ ባህሪትን በመምረጥ በመደበኘነት ልተኛ ስል ከ30 ደቂቃ በፊት እና ከምኝታዬ እንደተነሳሁ እንዲሁም ባገኘሁት ሁሉ አጋጣሚ በወረቀት ላይ በመፃፍ እነዚያ ባህሪያት ልማድ ባደርጋቸው በህይወቴ ምን ያህል ደስተኛ እና ስኬታማ ልሆን እንደምችል አስበዋለሁ፡፡
ሃሰቡም ወደ ስሜት እስኪቀየር ማሰላሰሉን እደጋግመዋለሁ፡፡ ትልቁ ቁልፍ እዚህ ላይ ነው፡፡ ሃሳብ ብቻውን ምንም ያህል ብናስበው ወደ ድብቁ አእምሯችን ገብቶ ምንነታችን ሊሆን አይችልም፡፡ ሃሳቡ ወደ ስሜት ሲቀየር ብቻ ነው፡፡ የፈለግነውን የማንነት ዘርፍ ለሳምንታት የመደጋገማችን እና የመታገሳችን ምስጢርም ይህ ነው፡፡ ከብዙ ልምምድ በኋላም ሃሰቡም ወደ ስሜት ስለሚቀየር ራሴን እነዚን ባህሪያት አስቤው ሳይሆን ሳላስበው ሳንጸባርቅ አገኘዋለሁ፡፡
ለዚህ ልምምድ በመደበኛነት ከመተኛታችን ከ30 ደቂቃ በፊት እና ከምኝታችን እንደተነሳን ያለው ሰዓት የተመረጠው በምክንያት ነው፡፡ በእነዚህ ሰዓታት አእምሯችን ቴታ ወደሚባለው ሞገድ ይወርዳል፡፡ ይህ የአእምሮ ሞገድ ሲኖረን ልክ አዲስ እንደተወለደ ጨቅላ ህፃን እንሆናለን፡፡ በዚህ አእምሯዊ ሁኔታ ላይ ባለን ጊዜ ድብቁ አእምሯችን የሰጠነውን ማንኛውም ሃሳብ በቀላሉ ተቀብሎ የማንነታችን አካል ስለሚያደርገው ነው፡፡ ይህ ለሁላችንም የሰው ልጆች ድንቅ ተፈጥሯዊ ነፃ የፈጣሪ ስጦታ ነው፡፡
አዲስ ማንነት መገንባት ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር ባንድ ጊዜ በትንሽቁጥር ማለትም ሶስተ እና ከዚያ በታች የሆኑ የማንነት ዘርፎችን በመምረጥ ሲወድቁም ራስን ሳይኮንኑ ይልቁንም ውድቀት የስኬት አካል መሆኑን ተረድቶ እንደገና ከወደቁበት መነሳት ነው፡፡ በትንሽ መጀመር እና ለረጅም ጊዜ መቀጠል የማንነት ግንባታ ስኬት የመሰረት ድንጋዮች ናቸው፡፡
እንግዲህ ውድ አንባቢየ ለናሙና ያህል ስዕብናን ወሰድኩ እንጅ ሌሎችም የማንነት ዘርፎች ማለትም የልቦና ውቅር፣ እምነት፣ ልማዶቻችንን … ወዘተ በአዲስ የሚገነቡት በዚሁ ተመሳሳይ መንገድ ነውና ከዚህ ሂደት ላይ ትኩረታችንን እናድርግ፡፡
አሁንም ግልጽያልሆነ ነገር ካለ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች በደስታ እንቀበላለን፡፡