መነሻ ሃሳብ
ብዙዎቻቸን አሁን ስላለንበት የማንወደው የህይወት ሁኔታ ብዙ ምክንያቶችን እንደረድራለን፡፡ ከነዚህም ምክንያቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ ቤተሰቦቻችን፣ አስተዳደጋችን፣ መንግስት፣ ትምህርት ቤቶቻችን እና አስተማሪዎቻቸን፣ ሰይጣን፣ ሃይማኖታችን፣ የተወለድንበት አገር ወይም አካባቢ፣ የአካባቢው ማህበረሰብ … ወዘተ ናቸው፡፡
እርግጥ ነው ከላይ የተጠቀሱት ምክንያቶች በአንድም በሌላም መንገድ በህይወታችን ስኬታማ እንዳንሆን የራሳቸውን ተፅዕኖ አሳድረውብናል፣ ያሳድሩብናል፣ ይገዳደሩናልም፡፡ ይሁን እንጅ በህይወታችን ስኬታማ ከመሆን ሊያስቀሩን አይችሉም፡፡ ለዚህም ለራሳችን ታማኝ እና ሃቀኛ ሆነን ማስተዋል ከቻልን እኛ ባለንበት ተመሳሳይ ሁኔታ እንዲያውም የባሰ የህይወት ሁኔታ የነበሩ ጥቂት ጓደኞቻችን ስኬታማ ሆነው ስናይ ከላይ ያሉ ምክንያቶች በእውንም ከህይወት ስኬታማነት የማያስቀሩ መሆኑን በተግባር ያሳዩናል፡፡
ስለዚህ አሁን በዚህ ቅጽበት ለዚህ ምሳሌ የሚሆንህ አንድ እንዳንተ ወይም በባሰ የሀይወት ሁኔታ ላይ የነበረ አሁን ግን ካንተ በተሻለ የህይወት ስኬት ላይ ያለ ጓደኛህን አስብ፡፡ እንደምታገኝ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ካላገኘህ ደግሞ ያኔ ከዓመታት በፊት አብረውህ የነበሩ ጓደኞችህ ዛሬ ላይ በህይወታቸው የት እንደደረሱ መረጃ የለህም ማለት ነው፡፡
ለማንኛውም ልብ ብለን ካየናቸው ካላይ ለህይወታችን አለመሳካት ምክንያት ብለን የደረደርናቸው ነገሮች ሁሉም ስኬታማ እንድንሆን የተቀመጡልን ቅድመ-ሁኔታዎች ናቸው፡፡ እስኪ ማናችን ነን ዛሬ ላይ የራሳችን ሃሳብ በራሳችን መወሰን በምንችልበት ደረጃ ላይ ሆነን ከላይ ከተጠቀሱት ምክንያቶች አንዱ፣ ሁለቱ፣ ሶስቱ … ወይም ሁሉም ስኬታማ (ማለትም ጥሩ አባት፣ ጥሩ በተሰማራውበት የስራ ዘርፍ ባለሙያ፣ ጥሩ ሃይማኖተኛ፣ መልካም ስነ-ምግባር ያለው ሰው፣ ጊዜ እና ሃይሉን በአግባቡ የሚይጠቀም ሰው… ወዘተ) እንዳልሆን በገመድ አስረውኛል የሚል እጁን ያውጣ፡፡ ማንም ማን የለም፡፡
ካለም ምናልባት እነዚያ ነገሮች ስኬታማ እንዳንሆን አድርገውናል ብለን በአእምሯችን አስበናል፣ በልባችንም አምነናል ማለት ነው፡፡ እውነትም ይሁን ሃሰት፣ ጠቃሚም ይሁን ጎጂ በአእምሯችን ያሰብነውና በልባችን ያመነው ሁሉ ይሆንልናል ይደረግልናልና፡፡ለዚህም ነው አምላካችን ራሱ ሁሉ ተፈቅዶላችኋል፣ ሁሉ ግን አይጠቅማችሁም ሲል የነገረን፡፡ ይሀንንም ያለበት ምክንያት በአእምሯችን የምናስበውን እና በልባችን የምናምነውን በጥንቃቄ እንመርጥ ዘንድ ሲነግረን፡፡
ልዩ ልዩ ምክንያቶች በህይወታችን ስኬታማ እንዳንሆን አድርገውናል ብለን በማሰባችን እና በማመናችን እንቅፋት ሆነውናል፣ እየሆኑንም ናቸው ማለት ነው፡፡ እውነታው ግን ለህይወታችን ስኬትም ሆነ ውድቀት ብቸኛው ምክንያት እኛው ራሳችን ነን፡፡ ይህንን አምኖ መቀበል ብቻ በራሱ ቀላል ወደማይባል የህይወት ስኬት ጉዞ ይወስደናልና እናስብበት፡፡
ለመሆኑ ከላይ የተዘረዘሩት ነገሮች ባይኖሩ ኖሮ ሰው ስለምን እና የማንን ችግር እና ፈተና ለመቅረፍ ይበረታ ነበር?
ከላይ ተዘረዘሩት ለህይወት ስኬታማነታችን እንቅፋት ናቸው ብለን የፈረጅናቸው ነገሮች ሁሉም ለህይወት ስኬታማነታችን ወሳኝ ነገሮች ናቸው፡፡ ይህንንም በተጨባጭ ለመረዳት ጥቂት ጥያቄዎች እናንሳ፡-
እስኪ ማናችን ነን
ከላይ ያሉት የህይወት ፈታኝ ነገሮች በሌሉበት በህይወታችን ስኬታም ልንሆን የምንታትረው እና ስኬታም ልንሆን የምንችለው?
እስኪ ማናችን ነንስ ከቤተሰቦቻችን፣ ከመንግስት፣ ከትምህርት ቤቶቻችን እና ከአስተማሪዎቻቸን፣ ከሰይጣን፣ ከሃይማኖታችን፣ ከተወለድንበት አገር ወይም አካባቢ፣ ከአካባቢያችን ማህበረሰብ … ወዘተ ፈተና ሙሉ በሙሉ ነፃ ብንሆን በህይወታችን ሌት ተቀን የምንበረታው እና ስኬታማ ልንሆን የምንችለው?
ቶማስ ኤድሰን የማንን ጨለማ ለመግፈፍ መብራትን ለመፍጠር ይተጋ እና ይታትር ነበር?
ሁለቱ ዎንድማማቾች ኦርቪል እና ዊልበር (ራይት) የማንን ረጅምና አሰልች ጉዞ ለማሳጠር አውሮፕላን ለመፍጠር ይተጉ እና ይታትሩ ነበር?
ቲም በርነርስ ሊ የማንን የመረጃ እና ግንኙነት ችግርን ለማቃለል ኢንተርኔትን ለመፍጠር ይተጋ እና ይታትር ነበር?
ዝርዝሩ አያልቅም ... እናንተም ጨምሩበት፤ ለጥያቄዎቹም መልሱን ልብ እያላችሁ ...
በህይወታችን ያሉብንን ችግሮች የሚረዳ እና መፍትሄ የሚያመጣ ከእራሳችን በላይ ማንም የለም
እንደሚታወቀው ስለራሳችን የህይወት ችግር ከራሳችን በላይ ማንም ሊያውቅ የሚችል የለም፡፡ የቀን ውሏችን ምን እንደሚመስል፣ በውስጣችን ስለ ስኬት፣ ስለ ራሳችን፣ ስለ ሰዎች፣ ስለ ትዳር፣ ስለ ህይወት፣ ስለ ገንዘብ … ወዘተ ያለን ሃሳብ እና እምነት፣ ስለ ልማዶቻችን፣ ስለ ስዕብናዎቻችን፣ ስለ ባህሪያቶቻችን …
ወዘተ ከራሳችን በላይ ማንም አያውቅም፡፡
ከዚህም ሃቅ የተነሳ ከላይ ለተጠቀሱት የህይወታችን ክፍሎች ላሉብን ማንኛውም ግለሰባዊ ችግሮች የተሻለ መፍትሄ ከራሳችን በላይ ማንም ሊያመጣልን አይችልም፡፡ ስለሆነም የራሳችንን ግለሰባዊ ችግሮች መርምረን ማወቅ ያለብን እኛው ነን:: መፍትሄ ማስቀመጥ ያለብንም እኛው መሆናችንን በሙሉ ልብ አምኖ መቀበል የስኬትን ግማሽ መንገድ የመሄድ ያህል ነው፡፡ ምክንያቱም ይህንን ሃሳብ አምነን ከተቀበልንበት ቅጽበት ጀምሮ ጣቶቻንን የምንቀስረው ወደ ማንም እና ወደ ምንም ሳይሆን ወደ ራሳችን ስለሚሆን ያለንን ጊዜ እና ታኩረት ሁሉ በትክክለኛው የችግሩ እና የመፍትሄው ብቸኛ ባለቤት ወደ ሆነው ወደ ራሳችን ሆነ ማለት ነውና፡፡
ይህ ሲሆን ውጤቱ ላይ ሳይሆን መንስኤው ላይ እየሰራን ስለሆነ የተሻለ ስኬታማ መሆናችን አይቀሬ ጉዳይ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ከዚህ በኋላ ስለ ራሳችን ህወት ስኬት ምንም ያህል ጥቂት ጊዜ እና ትኩረት ከላይ የተዘረዘሩትን ምክንያቶች በመመርመር እና በማማረር ልናጠፋ አይገባም ማለት ነው፡፡ እንግዲህ በዚህ መልኩ ጊዜ እና ትኩረታችንን በሚገባው ነገር
(በራሳችን) ላይ አዋልን ማለት ህወታችንን ወደ ሚገባው አቅጣጫ እየወሰድን ነው ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም የእያንዳንዳችን ህይወት መገለጫው በጊዜ እና በትኩረት አጠቃቀማችን ሁኔታ የተመሰረተ ነውና፡፡
የራስን ህይወት ሙሉ ኃላፊነት መውሰድ
ሰው ሁለት የህይወት ምዕራፎች አሉት፡፡ የልጅነት የህወት ምዕራፍ (ሁሉም ምርጫዎች እና ውሳኔዎች በሌላ አካል የሚደረጉበት) እና ከልጅነት የዕድሜ ክልል ውጭ ያለው ያህይወት ምዕራፍ (ሁሉም የግል ምርጫዎች እና ውሳኔዎች) ሙሉ በሙሉ በራሱ የሚወስንበት ናቸው፡፡
እንደ እኛ ከልጅነት የዕድሜ ክልል ውጭ የህይወት ምዕራፍ ያለ ሰው በህይወቱ ስለሚሆነው ማንኛውም ነገር (ስኬት ወይም ውድቀት) ሙሉ ተጠያቂው ራሱ ነው፡፡ ምክንያቱም ከላይ እንደተገለጸው ሁሉም ግለሰባዊ ምርጫዎች እና ውሳኔዎች የሚደረጉት በራሱ ነው፡፡
ስለሆነም በህይወቱ የሚሆኑት ማንኛውም ነገሮች በሙሉ የራሱ ምርጫዎች እና ውሳኔዎች ውጤቶች ናቸው፡፡ ይህንን ማንም በህይቱ ስኬታማ መሆን የፈለገ ሰው ለአፍታም ሊዘነጋው የማይገባው ትልቅ የህይወት ፍልስፍናና ተጨባጭ እውነታ ነው፡፡ በመሆኑም ሁላችንም በህይወታችን በየትኛውም የህይወት ዘርፋችን የማንወዳቸው ውጤቶች፣ ክስተቶች ወይም ሁኔታዎች ካሉ ልብ ልንለው የሚገባው ሃቅ ሁሉም የራሳችን ምርጫዎች እና ውሳኔዎች ውጤቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ ሙሉ ኃላፊነቱን በራሳችን ወስደን ውጤቱን ወዳመጡት ትክክለኛ የእኛ ስዕብና፣ ባህሪ፣ ልማድ፣ አስተሳሰብ፣ እምነት … ወዘተ ልብ ብለን መመርመር እና መፍትሄ መሻት ላይ ማተኮር አለብን፡፡
አንተን የገጠሙህ ፈተናዎች የብዙ ሽ፣ ሚሊዮን እና ቢሊዮኖች ችግር ነው
ብዙዎችቻን አንድ ችግር በህይወታችን ሲገጥመን እኛ ብቻ የዚያ ችግር ብቸኛው ተጠቂ አድርገን እናስባለን እናምናለንም፡፡ በዚህም ምክንያት የደረሰብን ችግር ከሚያደርስብን አውናዊ ጫና ባልተናነሰ አንዳንዴም በበለጠ በዚህ ለምን እኔ ብቻ …
በሚል የራስን በራስ ማዳከም ወይም ማጥቃት አስተሳሰብ አዙሪት ውስጥ እንገባለን፡፡ በመሆኑም ለችግራችን መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ የችግሩ ተጠቂነታችንን በራሳችን አምነን በመቀበል በችግሩ ውስጥ እንኖራለን፡፡
በአንደኛ ደረጃ መታወቅ ያለበት አንድ እውነታ በተለይም በዚህ ዘመን ህይወት ከፈተና ውጭ ሆና አታውቅም፡፡ እንዲያምውም ታላላቅ ሰዎች ፈተና የሌለበት ህይወት ጨው የሌለው አልጫ ወጥን ይመስላል ይላሉ፡፡ እንዲሁም ሌላ አንድ አባቶቻችን ሚያዝወትሩት ትልቅ እና ደስ የሚለኝ አባባል አለ፡፡ ህመም ወይም ችግር አትግጠመኝ አይባልም፡፡ ይልቁንም ህመሙን ወይም ችግሩን የምቋቋምበትን እና የማልፍበትን ጥበብን፣ ትዕግስትን እና ማስተዋልን ስጠኝ እንጅ፡፡ ይህ አባባል በእውነት እጅግ ጥልቅ አባባል ነው፡፡ እንደ እኔ እይታ ለሰው ልጅ የራሱን ችግር በጥበብ፣ በትትዕግስት እና በማስተዋል ከመፍታት በላይ ስኬት ያለ አይመስለኝም፡፡ ስለዚህም ከዚህ በኋላ ማንኛውም ችግር በህይወታችን ሲገጥመን ትኩረታችን ወደ መፍትሄው እና መፍትሄውን በመፈለግ ሂደት ስለምንገነባው ችግር-ፈች ጠንካራ ማንነመት ላይ መሆን አለበት፡፡
በሁለተኛ ደረጃ መታወቅ ያለበት ወሳኝ ነገር አንተ የምትሰቃይበት ችግር ምናልባትም የብዙ ሽ፣ ሚሊዮን እና ቢሊዮኖች ችግር ሊሆን ይችላል፡፡ ስለሆነም መጽሐፍትን በማንበብ፣ የራስህን እና የሰዎችን የህይወት ተሞክሮ እና የተለያዩ ምንጮችን ብትመረምር እና ብታጠና ያንን ችግርህን ሌሎች ሰዎች ምናልባትም በቀላል መንገድ ፈትተውት ታገኛለህ፡፡ በዚህም አጋጣሚ ለመግለጽ ያህል ማንበብ ከቀለም ትምህርት አልፎ በህይወትህ በተግባር እና በጠጨባጭ የሚያገለግልበትም መልካም አጋጣሚ ይህ ነው፡፡ ልብ በል ሌሎች ችግራቸውን ከፈቱ አንተም ችግርህን መፍታት ትችላለህ፡፡
በጣም ደስ የሚለው ዜና እና የትኛውም ዓይነት የህይወት ሁኔታ ላይ ላለ ማንናውም ሰው ትልቁ ተስፋው (የጎዳና ተዳዳሪም ቢሆን፣ ሱሰኛም ቢሆን … ብቻ ማንም ሰው) ማንም ጎበዝ፣ ማንም ሰነፍ የለም፡፡ ይልቁንም ሁላችንም ያለምንም ልዩነት እኩል ሆነን በፈጣሪያችን በእግዚአብሔር አምሳከል የተፈጠርን ትልቅ ፍጡር ነን፡፡ ልዩነታችን በተሰጠነው መክሊት ብቻ ነው:: እናም ችግር ሲገጥምህ ችግሩን በውስጥህ ይዘህ እየተሰቃየህ ለመኖር መወሰን ሳይሆን ሌሎች ይህንን የገጠመህን ችግር እንዴት እንደቀረፉት አንብብ፣ ጠይቅ፣ መርምር …
አንዴ ቆም ብለህ አስብ፡--
o አሁንኑ ልትተገብረው የምትችለው ከጽሁፍ የተማርከው አንድ ... ሁለት ... ሶስት ... ወዘተ ሃሳብ ምንድን ነው?
o ስላንድ ነገር ብዙ መረጃ መኖር ዕውቀት ነው፤ መረጃውን በተግባር መጠቀም ደግሞ ጥበብ ነው!
አስተያየት፣ ተጨማሪ ሃሳብ እንዲሁም ጥያቄ ካላችሁ በዚሁ ድህረ-ገጽ ፃፉልን!
መልካም ዕለተ ሰንበት
2 አስተያየቶች
keep it on
ምላሽ ይስጡሰርዝOk! And thank you so much for the constructive comment.
ምላሽ ይስጡሰርዝ